1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሕወሃት» የሽብርተኝነት ፍረጃው ተነሳለት

ረቡዕ፣ መጋቢት 13 2015

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው አንደኛ ልዩ ስብሰባ በአሸባሪነት ፈርጆት የነበረውን የሕዝባዊ ወያነ ኃርነት ትግራይ ( ሕወሓት) ን የአሸባሪነት ፍረጃ በአብላጫ ድምጽ አነሳ።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሃትን ከሽብርተኝነት መዝገብ ሰረዘ

This browser does not support the audio element.

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው አንደኛ ልዩ ስብሰባ በአሸባሪነት ፈርጆት የነበረውን የሕዝባዊ ወያነ ኃርነት ትግራይ ( ሕወሓት) ን የአሸባሪነት ፍረጃ በአብላጫ ድምጽ አነሳ። ሰፋ ያለ ጠንካራ ውይይት በተደረገበት በዛሬው ልዩ የምክር ቤቱ ጉባኤ ከተገኙ 280 አባላት መንግሥት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ 61ዱ ሲቃወሙት ፣ 5 ድምፅ ተዐቅቦ ተመዝግቦ በአብላጫ ድምጽ የድርጅቱ የአሸባሪነት ስያሜ ተነስቷል። 
«ሕወሓት የሽብር ድርጊትን አላማው አድርጎ በመንቀሳቀሱ ፣ የድርጅቱ የሥራ አመራሮች ወንጀልን በአሠራርም ሆነ በተግባር የተቀበሉት በመሆኑና አፈፃፀሙን እየመሩ በመሆኑ እንዲሁም የሽብር ተግባር የድርጅቱ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ» በአሸባሪነት ተፈርጆ ነበር ያሉት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ሕወሓት "በሰላም ስምምነቱ መሠረት ወደ ሕጋዊነት ለመመለስ በመስማማቱ" መንግሥት ይህንን የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቡን ገልፀዋል። 
"እስካሁን ያለው የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገር በሚያበቃ አበረታች ደረጃ ላይ መሆኑ በመረጋገጡ በቀጣይ የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለማሳለጥ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት በፖለቲካ እና በውይይት እየተረጋገጠ እንዲሄድ ማስፈለጉ" የውሳኔው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል። 
ከምክር ቤቱ አባላት የድጋፍም የተቃውሞም አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበዋል። ለተነሱ ጥያቄዎች የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሀሴን ምላሽ እንዲሁም ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህ መደረጉ ግን ከአንድ የምክር ቤት አባል የሥነ ሥርዓት ጥያቄ አስነስቶ ነበር።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባው የሕወሓት የሽብርተኝነት ስያሜ እንዲሰረዝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል። ይህንን ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ልዩ ስብሰባው የመንግሥትን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍም ፣ በመቃወምም ለ3 ሰዓታት የተጠጋ ጊዜ ተወያይቷል።
ከምክር ቤቱ በተነሱ ጥያቄ እና አስተያየቶች ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ በዋና ዐፈ ጉባኤ እድል ተሰጥቷል። ይህ አካሄድ ግን ከአንድ የምክር ቤት አባል የሥነ ሥርዓት ጥያቄ አስነስቷል። በዛሬው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ውስን የመገናኛ ብዙኃን ብቻ ናቸው ዘገባ እንዲሰረ ጥሪ የተደረገላቸው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትን ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነበር በሽብርተኝነት የፈረጀው።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW