1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህወሓት በረዥም ስብሰባ ተጠምዷል

ማክሰኞ፣ ጥር 7 2016

በትግራይ ክልል የከፋ ሁኔታ ባለበት የህወሓት አመራር በረዥም ስብሰባ ተጠምዶ ይገኛል በማለት ተቃዋሚዎች ተቹ። የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት፣ ነባር የፓርቲው አመራር፣ የትግራይ ወታደራዊ መሪዎች እና ሌሎች እየተሳተፉበት የሚገኘው ሰብሰባ እስካሁን መቋጫ አላገኘም። የክልሉ አስተዳደር የሚሰነዘርበትን እነዚህን ክሶች ውድቅ አድርጓል ።

ትግራይ ክልል ኅብረተሰቡ ችግር ላይ ነው ተባለ
ትግራይ ክልል ሕወሓት የተራዘመ ስብሰባ ላይ ተቀምጦ ኅብረተሰቡ ችግር ላይ ነው ተባለምስል Million Hailesilassie/DW

ሕወሓት በረዥም ስብሰባ ተጠምዶ፦ ትግራይ ክልል መንግስታዊ አገልግሎቶች እየተስተጓጎሉ ነው ተባለ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል የከፋ ሁኔታ ባለበት የህወሓት አመራር በረዥም ስብሰባ ተጠምዶ ይገኛል በማለት ተቃዋሚዎች ተቹ። የክልሉ አስተዳደር የሚመራው ህወሓት በረዥም ስብሰባ ላይ መጠመዱን ተከትሎ መንግስታዊ አገልግሎቶች እየተስተጎጎሉ ነው ተብሏል። የክልሉ አስተዳደር የሚሰነዘርበትን እነዚህን ክሶች ውድቅ አድርጓል ።

ሕዳር ወር መግቢያ ላይ መጀመሩ የተገለፀው እና የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት፣ ነባር የፓርቲው አመራር፣ የትግራይ ወታደራዊ መሪዎች እና ሌሎች እየተሳተፉበት የሚገኘው ሰብሰባ እስካሁን መቋጫ አላገኘም። ስለስብሰባው ይዘት ይሁን አጀንዳ በይፋ የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን፤ 'ስትራቴጂካዊ' በተባሉ ጉዳዮች ዙርያ ምክክር እየተደረገ መሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል። ይሁንና የዚህ አብዛኛው የትግራይ ሲቪል እና ወታደራዊ አመራር እየተሳተፈበት ያለው ስብሰባ መራዘም፥ በህወሓት ውስጥ ያለ ክፍፍል ማሳያ ነው ብለው በርካቶች ይገልጻሉ። ከዚህ በዘለለ በስብሰባው ምክንያት መንግስታዊ አገልግሎቶች መደናቀፍ እየገጠማቸው መሆኑን በማንሳት ትችቶች ይሰነዘራሉ።

በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ ወይም ባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ኪዳነ አመነ እንደሚሉት፥ ግልፅነት የጎደለው እና ረዥም ባሉት የሕወሓት ማእከላይ ኮሚቴ እና የትግራይ ወታደራዊ አመራር ሰብሰባ ምክንያት መንግስታዊ አገልግሎቶች ተደናቅፈዋል።

አቶ ኪዳነ "እኛ እየተደረገ ያለው ስብሰባ የማን ነው ብለን ስናስብ፥ ግልፅነት የለዉም። የሆነ ፓርቲ ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል። ፓርቲ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ አመራር ይመርጣል፣ ሥራው ይከውናል። አሁን እያየነው ያለነው ስብሰባ ግን መደበኛ የሚባል ስብሰባ አይደለም። በስብሰባው ከህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ በተጨማሪ የሰራዊት አመራሮችም አሉ። የሰራዊት መሪዎቹ ወደስብሰባው የገቡት ከሰራዊቱ ጋር መክረው፣ እውቅና ተሰጥቷቸው አይደሉም ወደ ስብሰባው የገቡት። ሌላ የግዚያዊ አስተዳደሩ የቢሮ ሐላፊዎች፣ የዞን ሐላፊዎች፣ የተለያየ የህዝብ ሐላፊነት ያላቸው አካላት የመንግስት መሥርያ ቤቶች ዘግተው፣ የሕዝብ አገልግሎት አቋርጠው ስብሰባው ላይ ናቸው" ይላሉ።

እንደ አቶ ኪዳነ ገለፃ በስብሰባው የህወሓት ከፍተኛ አመራር በሁለት ጎራ ተቧድነው ፍጥጫ ላይ መሆናቸው ያነሳሉ። ሌላው ፖለቲከኛ አቶ ክብሮም ተክላይ የትግራይ ህዝብ በከፋ ችግር ላይ ባለበት አመራሮቹ በግድ የለሽነት ረዥም እና መፍትሔ ይዞ በማይመጣ ስብሰባ ላይ ተጠምደዋል ይላሉ። አቶ ክብሮም በትግራይ ያሉ የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት ከአንድ ፓርቲ አመራር የዘለለ የሁሉም አቅም የሚሰበስብ አካሄድ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

አቶ ክብሮም "የትግራይ ህዝብ እየጠፋ ነው ያለው፣4 ነጥብ 2 ሚልዮን ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ ይፈልጋል። በትግራይ የምግብ ጥያቄ ነው ያለው። ህዝቡ ሕክምና ይሻል። ችግሮች እየተደራረቡ ነው። ምሁሩ የሰው ሐይል እየተሰደደ ነው ያለው። ወጣቱ እግሩ ወደመራው እየሄደ ነው። ታጋዮች ከባድ ችግር ላይ ነው ያሉት። እነዚህ ነገሮች ያሉን ማሕበራዊ አቅም ሁሉ እያሳጡን ነው። አካሄዳችን ችግር የሚፈታ አይደለም። ለሁሉ የምትሆን ትግራይ መፍጠር አለብን" ይላሉ።

ትግራይ ክልል ውስጥ ዘርፈ ዙ ችግሮች ኅብረተሰቡን ማሕበራዊ አቅም እያሳጡን ነው ተባለ ምስል Million Hailesilassie/DW

ህወሓት ተመሳሳይ ረዥም የማእከላይ ኮሚቴ ሰብሰባ ሲያደርገ ይህ ለመጀመርያ ግዜ አይደለም። ተሃድሶ፣ ጥልቅ ተሃድሶ በሚሉ መፈክሮች ከወር በላይ ስብሰባ የሚቀመጡበት አጋጣሚ በርካታ ነው። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከህወሓት ፅሕፈት ቤት በቀጥታ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም። ይሁንና የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እና የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባሉ አቶ ረዳኢ ሐለፎም ከቀናት በፊት እንደገለፁልን፥ የትግራይ አመራራር ከስራ ይልቅ በስብሰባ ተጠምዷል የሚል ከተለያዩ አካላት የሚሰነዘር አስተያየት አይቀበሉትም። የመንግስት አመራር ማለት ከክልል እስከ ቀበሌ ያለ ሁሉም ነው የሚሉት አቶ ረዳኢ ሐለፎም፥ አሁን ላይ ስብሰባ የተቀመጠው ግን ጥቂት እና ስትራቴጂካዊ ግምገማ የሚያካሂድ ነው ብለዋል።

ክልላዊ መድረክ ተብሎ የተገለፀው ይህየህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ እና ወታደራዊ አመራሮች ስብሰብ ተጀመረ ብሎ የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች የገለፀው ከሁለት ወር በፊት ሕዳር 2 ቀን 2016 ዓመተ ምህረት ነው።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW