«ሕወሓት» እና «ኦነግ ሸኔ» በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2013ማስታወቂያ
በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበባቸው ሕወሓት እና 'ሸኔ' ውሳኔው ከፀና በረጅም ጊዜ ሂደት የሕዝብ ፀጥታ ፣ የአገር ሠላም ሥጋት መሆናቸው ይቀንሳል ተባለ።ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቡን የሚያፀናውና ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ፍርድ ቤቶች ብዙ ሰዎች ያለአግባብ እንዳይንገላቱ በሕግ እና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ጥንቃቄ የተሞላበት ተጠያቂነት እንዲያስከትሉ ጠይቀዋል።ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳቡን ከማፅደቁ በፊት ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮና ማስረጃዎችን ጠይቆ ኃላፊነት የተሞላው ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።እንደ የሕግ ባለሙያዎቹ ገለፃ ፣ይህ ካልተደረገ ቀደም ሲል የተሻረው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ላይ የተስተዋለው፣ሕጉን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋልን ሊያስከትል ይችላል።የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ «ሕወሓት እና ሸኔ የተባሉት ድርጅትና ቡድን ሕዝብን ስጋትና ፍርሃት ውስጥ በመጣል በመንግሥት ላይም እምነት በማሳጣት የሀገረ መንግሥቱን ኅልውና አደጋ ላይ ጥለዋል» ሲል ከሷቸዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ