«ሕዝብ ለመብቱ በአንድነት መቆም እንዲጀምር» ኢሕአፓ ጥሪ አደረገ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 17 2017
በገዥው ፓርቲ ይስተዋላል ያለው "ጦረኝነት እና ማን አለብኝነት ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ እንዲጋረጥባት" አድርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ከሰሰ። ፓርቲው 11ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ካከናወነ በኋላ ባወጣው መግለጫ የመንግሥት አካሄድ "ኢትዮጵያውያን የዜግነት እና የሰውነት ክብራቸው እንዲገፈፍ ምክንያት ሆኗል" ሲል እርምት ጠይቋል ። ኢሕአፓ ላለፉት ሦስት አመታት ፓርቲውን ሲመሩ የቆዩ አመራሮችን በአዲስ ምርጫ ማዋቀሩን ጠቅሶ በዚህም ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሃም ሃይማኖትን የፓርቲው ፕሬዘዳንት አድርጎ መምረጡን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ከሐምሌ 14 እስከ15 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ሐዋሳ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤውን ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ "ዓላማቸው የገዢውን ሥልጣን መጠበቅ ብቻ የሆኑ" ያላቸው "ጦርነቶች እና አለመረጋጋቶች በሁሉም ክልሎች ላለፉት ሰባት ዓመታት ቀጥለዋል" ብሏል፡፡
በትግራይ፣ ቀጥሎም በአማራ ክልሎች የነበሩ እና የቀጠሉ ጦርነቶችን እና በኦሮሚያ ክልል ያለውን ሰላም እጦት የጠቀሰው ፓርቲው "ውል አልባ ግለሰባዊ ግንኙነት" ያለውና ከኤርትራ መንግስት ጋር ምክንያቱ በማይታወቅ መልኩ "ግንኙነቱ በመሻከሩ የግል ጸብን ወደ ሀገር በማምጣት በተለይ ለሰሜኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳግም የእልቂት እና የጥፋት ድግስ ተደግሶለታል" ሲል ሥጋቱን ገልጿል።
ኢሕአፓ እንዳለው እነዚህ ማሳያዎች እንጂ "በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እና ግጭት የሌለበት ቦታ አለ ለማለት አይቻልም" ሲልም ደምድሟል፡፡ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት ይህንን አክለዋል።
"ሀገሪቱ ያለችበት የጦርነት ኹኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ነው፣ የእርስ በርሱ ግጭት። አብዛኛው አካባቢ ምንም ዋስትና የለም ማለት ይቻላል። የንፁሐን እልቂቶች አሉ"።
ብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን መንግሥት ከኢሕአዴግ በባሰ "ዘረኛነት፣ ሙሰኛ እና እኔ ብቻ ባይነት" አለበት ሲል የፈረጀው ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ "ታይቶ የማይታወቅ የእርስ በእርስ ግጭት በሀገሪቱ ውስጥ" እንዲካሄድ አድርጓም በሚል ወንጅሏል። መንግሥት "የዜጎችን ሕይወት ማክበርም ማስከበርም አልቻለምም፣ አልፈለገምም" ይህም በመሆኑ "የዜግነት መብት ቅንጦት ወደመሆን ወርዷል" ብሏል፡፡
ኢሕአፓ ከማን እንደሆነ ባይጠቅሰውም መንግሥት "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገፉ የውጭ ፖሊሲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበሉ" የአገሪቱ ኢኮኖሚ በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል ብሏል።
በመንግሥት በኩል ይታይል ያለው "የጦረኝነት እና የማን አለብኝነት መንፈስ ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ እንዲጋረጥባትና ኢትዮጵያውያንም የዜግነት እና የሰውነት ክብራቸው እንዲገፈፍ ምክንያት ሆኗል" ሲልም ከስሷል፡፡
"ኢትዮጵያ ከባድ አደጋ ውስጥ ናት። በሕዝብ መሃል አለመተማመን አለ። ሀገሪቱ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባታል ማለት ይቻላል። የሰላማዊ ትግሉ ላይ ርብርብ ያስፈልጋል፣ ምህዳሩን ማስፋት ያስገልጋል » ብለዋል
በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግሥትን ምላሽ ለማካተት ወደ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። ኢሕአፓ "ሕዝብ ለመብቱ በአንድነት መቆም እንዲጀምር" በመግለጫው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን "ተቃዋሚ በመሆናቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በማንነታቸው ምክንያት "ለዓመታት በግፍ እሥር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ" አሳስቧል።
አዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መሰየሙን የገለፀው ፓርቲው ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ መሪነታቸውን በፈቃዳቸው በማስረከባቸው አብርሃም ሃይማኖት የፓርቲው ፕሬዘዳንት ሆነው መመረጣቸውንም ገልጿል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ