ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2011ለችግሩ መባባስ ሕገወጥ የጥቅም ትስስር፤ በሀገሪቱ የሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት፤ ጠንካራ ሕግን የማስከበር ሥራ አለመኖር እና የኅብረተሰቡ ቸልተኝነት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች ፡ ምሥራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ችግሩ በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ ፡ የቅባት እህሎች ፡ የቀንድ ከብት እና የመሳሰሉት ከኢትዮጵያ ሲወጡ ፡ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች ፡ የታሸጉ ምግቦች ፡ ሃሽሽ ፡የጦር መሣሪያ፡ የመዋቢያ ቁሳቁሶች እና ሞተር ሳይክልን ጨምሮ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ታውቋል። ድርጊቱ ከጥቅም ተጋሪዎች እና ከአንዳንድ የመንግሥት አካላት ሳይቀር ሽፋን እና ከለላ እንደሚደረግለት ነው የተገለጸው ። መንግሥት በተለያዩ የሀገሪቱ ጠረፍ አካባቢዎች ተመሳሳይ ባህል፣ ወግ እና አኗኗር ላላቸው የጎረቤት ሃገራት ህዝቦች የፈቀደው ፍራንኮ ቫሎታ የተሰኘ የነጻ የመሠረታዊ ሸቀጦች ግብይት አላማውን ስቶ ለሕገ ወጥ ንግድ መጋለጡ ለችግሩ መባባስ ሌላኛው ምክንያት ሆኖ ተቀምጧል። ኮንትሮባንድ ሕጋዊ ነጋዴዎች ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እያሳረፈ ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ መሄዱ ን የገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ የሚሆን የጉምሩክ ፖሊስ እንዲደራጅ ውሳኔ ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡
ሰለሞን ሙጨ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ