ሕገ ወጥ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ በትግራይ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6 2017
በትግራይ ክልል በሕገወጥ መንገድ የሚካሄድ የወርቅና የሌሎች ማዕድናት ማውጣት ስራን ለማቆም እየጣረ መሆኑን የክልሉ አስተዳደር አስታወቀ። የማዕድናትን ማውጣት ሕገ ወጥ ከመሆኑ በተጨማሪ የአካባቢ ዓየር ብክለትን የሚያስከትልና ሐብቱ የጥቂቶች መጠቀሚያ መሆኑን አስተዳደሩ አስታዉቋል።የትግራይ ማዕድን ቢሮ በመጥቀስ መንግስታዊ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትላንት ያሰራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት 189 ኩንታል ወርቅ ከትግራይ ክልል ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉ ይገልፃል። በባህላዊ እና ዘመናዊ መንገድ የሚደረገው የወርቅ ማውጣት ስራ ለበርካታ ዜጎች የገቢ ምንጭ ሆኖ እንዳለ የሚነገር ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ሕገወጥ የወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት በትግራይ መንሰራፋታቸው ተከትሎ የአካባቢ ተፈጥሮ ሀብት ውድመት እና ብክለት በስፋት እየተስተዋለ ስለመሆኑም ተገልጿል።
የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር በትግራይከወርቁ ማውጣት በተገናኘ ያሉ ሕገወጥነቶች ለማስቀረት በሚል የወርቅ ማውጣት ስራው በግዚያዊነት እንዲቆም ይህ ለማስፈፀም ደግሞ ግብረሀይል አዋቅሮ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የሚፈለገው ስራ አለመከወኑ በክልሉ አስተዳደር ተገልጿል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ "የትግራይ የማእድን ሀብት ፀጋ መሆኑ ቀርቶ፥ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚመዘበር፣ ሀብት የሚባክንበት" ሆንዋል ያሉ ሲሆን "በአጠቃላይ በትግራይ የሚደረግ የማዕድን ማውጣት እና ዝውውር ስራ ከሕግና ስርዓት ወጥቶ ወደከፋ ሁኔታ የተገባበት ሁኔታ ተፈጥሮ ይገኛል" ሲሉም አክለዋል።
ይህ በቢልዮን የሚቆጠር ሀብት የሚያንቀሳቅስበት የወርቅ ማውጣት ስራ በብልሹ አሰራሮች፣ ዘላቂ ተፈጥሮአዊ መዛባት በሚፈጥሩ አካሄዶች የሚከወን በማለት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገልፁ ሲሆን፥ በዚሁ ስራም የትግራይ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች እጅ እንዳለበት ሲሉም ቆይተዋል። የክልሉ አስተዳደር ጥቂቶች ብቻ የሚበለፅጉበት በርካቶች በብክለት የሚጎዱበት በተባለው ዘርፍ ላይ ሕግ ለማስከበር እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑ ገልጿ፥ በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በዚሁ የወርቅ ቁፋሮ የነበሩ ማሽነሪዎች መያዙም ይገልፃል። አቶ አማኑኤል ከ440 በላይ የሚሆኑ ማሽነሪዎች ከማእድን ማውጫ አካባቢዎች ወጥተው በማቆያ ተይዘው እንዲቆዩ ተደርጓል። ይህ እንቅስቃሴ ህዝብም ተስፋ ጥሎበታል" ብለዋል።
በተለይም ከጦርነቱ በኃላ ሕገወጥነት የተበራከተበት በትግራይ ያለው የወርቅ ሀብት የማውጣቱ ስራ በስርዓት ለመምራት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከዚህ በፊት መደናቀፋቸው ያነሱት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው፥ አሁን ላይ በተለየ ትኩረት ወደ ስራ መገባቱ ይገልፃሉ።
የክልሉ አስተዳደር አካላት የጥቂቶች መጠቀሚያ ሆነ በተባለው የትግራይ ማዕድን ዘርፍ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ የሚገልፅ ቢሆንም፥ አሁንም ድረስ ተጨባጭ ነገሮች እንደሌሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ