1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"መለያየት እና መገፋፋት" ለኢትዮጵያውያን አያዋጣም አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26 2011

በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በደም አፋሳሽ ግጭቶች የተቋረጠውን የንግድ ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለስ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ-መስተዳድር ሙስጠፋ መሐመድ ተናገሩ። የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ "መለያየትና መገፋፋት" ለኢትዮጵያውያን አያዋጣም ብለዋል።

Äthopien - Oromo und Somalier treffen sich
ምስል DW/M. Teklu

በሶማሌ፣ኦሮሞና ሐረር ሕዝቦች ግንኙነት ላይ ውይይት ተካሒዷል

This browser does not support the audio element.

በሀገሪቱ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ ክልሎችና ክልሎቹ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን ማረጋጋትና ወደ ነበረበት መመለስ ዛሬም የቤት ስራ እንደ ሆነ ቀጥሏል። ከለውጡ ጋር ወደ ስልጣን የሚመጡ ሹማምንት የተፈናቀሉ ዜጎችን ማደራጀት፣ የተቋረጡ የህዝቦች የእርስ በእርስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ወደ ቀድሞ ማስመለስ በሚል አጀንዳ የሚከውኑት ተግባር ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሰሞኑን የኦሮሚያ ፣ ሶማሌ እና ሀረሪ ክልላዊ መስተዳድሮች እና የህብረተሰቡ ተወካዮች የተገኙበት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በዚህ መድረክ በተለይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ከህዝብ ለህዝብ ትስስሩ በተጨማሪ ተቋርጠው የነበሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ መጀመር እንዳለባቸው በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡

አቶ ሙስጠፋ በንግድ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ የሚሆነው አንድ ወገን ብቸ አለመሆኑን ጠቁመው በክልሉ በኩል ለንግድ እንቅስቃሴ መጀመር ዝግጁ መሆናቸውና በእንቅስቃሴውም ምንም ዓይነት ገደብ ሊኖር እንደማይገባ አስታውቀዋል፡፡ በሀገሪቱ በተካሄደው ለውጥ ዋነኛ መሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ለማ መገርሳ በመከላከያ ሚንስትርነት መሾምን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሰረተዳድር ሆነው በመሾም ሀላፊነት የተረከቡት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከበዓለ ሲመታቸው ማግስት ጀምሮ ማካሄድ የጀመሩት የህዝብ ልህዝብ አንድነትን የማጠናከር ጥረት በክልሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚሁ መድረክ ጠቁመዋል። 

በሀረር በተካሄደው በዚሁ መድረክ ተጎራባች በሆኑት አካባቢዎች መካከል ያለውን የቆየ አንድነትና ትስስር በማጞልበት በኩል የሀረሪ ክልል የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ የክልሉ ርእሰ መስደዳድር አቶ ኡርዲን በድሪ ተናግረዋል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW