መራሒተ መንግሥቷ አዉስሽቪትስን ጎበኙ
ዓርብ፣ ኅዳር 26 2012
የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አዉስሽቪትስ የተባለዉን በደቡባዊ ፖላንድ የናዚ አስተዳደር አይሁዳዉያንን ያጉርበት እና ያሰቃይበት የነበረን ቦታ ለመጀመርያ ጊዜ ዛሬ ጎበኙ። መራሒተ መንግሥትዋ ይህን ጉብኝት ዛሬ ያደረጉት በናዚ አገዛዝ 1,1 ሚሊዮን ሕዝብ በተለይ ደግሞ አይሁዳዉያን በግፍ እየተያዙ ይገደሉበት፤ ይቃጠሉበት የነበረ ቦታ ከናዚ እጅ የተላቀቀበትን 75 ዓመት ዓመታዊ መታሰብያ ከመድረሱ ከሳምንታት በፊት ነዉ ተብሎአል።
«በአዉሽቪትስ በጋዝ ታፍነዉ፤ በረሃብ ፤ በብርድ በመርዝ የተገደሉ ሰዎች ስቃይን፤ ሰዉ በድካምና ረሃብ እስኪወድቅ ድረስ የግዳጅ ስራ ማሰራት ሁሉ የሰዉ ልጅ ማመን የሚያቅተዉ ድርጊት ነዉ። በጀርመን በተለይ ፀረ ሴማዊነት እንቅስቃሴን በተመለከተ ነቅተን ነዉ የምንጠብቀዉ ። በአይሁዳዊያን ኑሮ በጀርመን በአዉሮጳ ብሎም በተቀረዉ አለም ስጋት ላይ የወደቀ ነዉ። በቅልጽ ለመናገር ለፀረ ሴማዊ እንቅስቃሴ ምንም አይነት ትዕግስት የለንም። በጀርመን ብሎም በአዉሮጳ ማንኛዉም ሰዉ ደህንነቱ እንደሚጠበቅ ሊሰማው ይገባል።»
ሜርክል በጉብኝታቸዉ ሚሊዮኖች በግፍ የተገደሉበት ቦታ ላይ የአበባ ጉንጉን አኑረዋል። ሜርክል ይህን አሳዛኝና ታሪካዊ ቦታ ዛሬ መበጎብኘታቸዉ የአይሁዳዉያን ማዕከላዊ ምክር ቤት ጥሩ ርምጃ ሲል ማወደሱ አወድሶታል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ