«መሰናክሎችን በማስወገድ ድልድዮችን መገንባት» የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ተጠናቀቀ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1 2017
«መሰናክሎችን በማስወገድ ድልድዮችን መገንባት» የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ተጠናቀቀ
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የሄደውን የፖለቲካ አለመረጋጋት በተጨባጭ መረጃ በተደገፈ የሚዲያ ስራ ሚዛን መጠበቅ እንደሚገባ ተጠየቀ። ዶቼ ቬለ ያዘጋጀው እና ከበርካታ የዓለም ሃገራት የተጋበዙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ለሁለት ቀናት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተጠናቋል። መድረኩ ነጻ የመገናኛ ብዙኃን ተገቢው የፋይናንስ ድጋፍ ካላገኙ መረጃ ፈላጊው ህብረተሰብ ለተዛባ እና ትክክለኛ ላልሆነ መረጃ ሊጋለጥ እንደሚችል አሳስቧል
የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዶይቸ ቬለ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተጋበዙበት ለሁለት ቀናት የቆየ ውይይት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መክሯል ። በመቶዎች የሚቆጠሩ እነዚሁ የሚዲያ ባለሙያዎች በዚህ መሰናክል በበዛበት ጊዜ ውስጥ ህዝቦችን ማቀራረብ በሚያስችሉ ስልቶች ላይ በመወያየት ተጠናቋል።
«መሰናክሎችን በማስወገድ ድልድዮችን መገንባት» በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ዛሬ የተጠናቀቀው የዘንድሮው የዶቼ ቬለ የዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ በተለይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ወደፊት በዴሞክራሲ እና የመረጃ ተደራሽነት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በአንክሮ ተመልክቷል።
መድረኩ በመንግስት የሚደገፉ ነጻ የመገናኛ ብዙኃን በምዕራባዉያን ሃገራት ጭምር ሳይቀር አለባቸው ያላቸውን ጫናዎች አንስቷል። በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከተመለሱ በኋላ ከወሰዷቸው ርምጃዎች መካከል በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ እና በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርግላቸው የአውሮጳ ነጻ ራዲዮን ከስርጭት እንዲወጡ ማድረጋቸው ተጠቃሾች ናቸው ።
ዶቼ ቬለ ባዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የነጻ ራዲዮ አውሮጳ ፕሬዚዳንት ስቲቭ ካፑስ ርምጃው ለአስርት ዓመታት አሜሪካን ከአውሮጳ ያስተሳሰረውን የአትላንቲክ ምሰሶ እንደመናድ ነው ብለውታል።
ፕሬዚዳንቱ በተጋበዙበት መድረክ የመክፈቻ ንግግራቸው በተለይ በራዲዮ ነፃ አውሮጳ እና ለሌሎች ተዛማጅ የመገናኛ ብዙኃን ይደረጉ የነበሩ የገንዘብ ድጋፎችን ማቆም «ፕሬስ አፋኝ» ላሏቸው ሩስያ እና ቻይና አሳልፎ እንደመስጠት ነው ብለዋል።
«መፍትኄዎችን መጋራት» የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ መሪ ቃል
“ ህልውናችንን ማስጠበቅ መቻል አለብን ። ይህ ካልሆነ ግን ዓለምን ጨለማ ውስጥ መተው ለሚፈልጉት ለእንደነ ሩሲያ እና ለቻይና ላሉት ሁሉ ትልቅ ስጦታ ነው ።”
በመድረኩ ከተጋበዙ እንግዶቹ ውስጥ የብሪታንያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪድ ቢቢሲ ዓለማቀፍ ስርጭት ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ሙርኖ አንዱ ናቸው ። እንደ ዮናታን በዓለማቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የመገናኛ ብዙኃኑን መረጃ ለሚጠብቀው አድማጭ ተመልካች ለተሳሳቱ መረጃዎች እንዲጋለጥ እያደረገ መምጣቱን ነው ።
“የፖለቲካ አለመረጋጋት በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች እየጨመረ ነው። ይህ ደግሞ ለአድማጭ ተመልካቹ የሚያስከትላቸው መዘዞች እጅግ በጣም ብዙ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ባልደረቦች ነፃ ሚዲያቸውን እንዲዘጉ ወይም እንዲገድቡ ተገደዋል። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ። ይህ ደግሞ በተለይ የተሳሳቱ እና የተዛቡ መረጃዎች በአለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድጉ ምክንያት እንዲሆኑ እያደረገ ነው ።”
ለ18ኛ ጊዜ ዶቼ ቬለ ያስተናገደው የዘንድሮው 18ኛው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ጥራት ያለውን ጋዜጠኝነት ለማረጋገጥ የፋይናንስ ድጋፍ ዘላቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ የተጠየቀበትም ነበር። ወቅቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎ የተደገፉ መረጃዎች እንደ አሸን እየፈሉ ያሉበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ ተከትሎ የሚከሰቱ የሀሰተኛ መረጃዎች በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ማሳደራቸው በግልጽ እየታየ ነው ተብሏል። ለዚህ ደግሞ የመሰል ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎችን «መቆጣጠር» አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ተነስቷል።
ሳዴግህ ዚባካላም የመናገር ነፃነት ሽልማት አሸነፈ
በተጨማሪም መድረኩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እንደምን በአምባገነን መንግስታት የሚታነጹ የዲጂታል ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ማለፍ እንደሚችሉ በየፈርጁ መክሮበታል።
የዚህ ዓመት የዶቼ ቬለ የመናገር ነጻነት አሸናፊዋ ጆርጂያዊቷን ጋዜጠኛ ታማር ኪንዙራሽቪል በመድረኩ ላይ ስጋቷን እና ተስፋዋን ባጋራችበት ንግግሯ ዜጎች ነጻነታቸውን ለማስጠበቅ መንግስታቸው መቆጣጠር እንዳለባቸው ነው የጠቆመችው። ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን በተለይ ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ባይ ናት። ለዘህ ደግሞ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ መምስረት እንዳለበት ትመክራለች።
«ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ ተዓማኒነት ያለው መረጃ ሊኖርዎት ይገባል፣ ይህ ዲሞክራሲ የሚሰራበት መንገድ እና መረጃ ሃይል መሆኑን ነው የሚያሳየው። ኃያላን ተቋማት እና መንግስታት ደግሞ በራሳቸው መንገድ የህዝቡን አስተያየት ለመቆጣጠር መሞከራቸው አይቀርም።»
8ኛው የዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ
አሁን ማምሻውን የተጠናቀቀው ዓለማቀፉ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ የመካከለኛ ምስራቋን ሶሪያ ከበሽር አልአሳድ መንግስት መወገድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንፎርሜሽን ሚንስትሩን ጋብዞ አሳትፏል። ሚንስትሩ ሃምዛ አል ሙስጠፋ ባደረጉት ንግግር ሃገራቸው ሶሪያን መልሶ በመገንባት ሂደት የመገናኛ ብዙኃን የሚኖራቸውን ሚና አንስተዋል። በተለይ ለረዥም አመታት በጦርነት ውስጥ ያለፈችውን ሶሪያን ጨምሮ አሁንም ድረስ በጦርነት በሚታመሰው የመካከለኛው ምስራቅ የመገናኛ ብዙኃኑ የጦርነት ክፍፍልን አርቀው እርቅን ሊሰብኩ በሚችሉበት አግባብ መቃኘት አለባቸውም ብለዋል።
መድረኩ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን ልምድ እና ተሞክሮ አጋርቶ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ