1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዲዛነር ሀናን አህመድ

ዓርብ፣ ኅዳር 4 2013

ከዲዛይነር ሀናን አህመድ የቅርብ ሥራዎች መካከል በተለይ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚጠቅም ጭምብል ይገኝበታል። ሀናን ከዚህ ቀደም በተለይ የሙስሊም ሴቶች አልባሳትን በባህላዊ መልኩ እያዘጋጀች በማቅረብ ትታወቃለች።

ዲዛይነር ሀናን አህመድምስል Hanan Ahmed

ዲዛይነር ሀናን አህመድ

This browser does not support the audio element.

በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች የምንገኝ ሰዎች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የዕለት ከዕለት ግዴታችን መሆን ከጀመረ ወራቶች ተቆጠሩ። የኮሮና ስርጭቱ ስላልተገታም ጭምብል አለማድረግ እንዲህ በቶሎ የሚቀር አይመስልም። 
ታድያ ይህንን ወደንም ሆነ ተገደን የምናጠልቀውን ጭምብል በተለያየ አይነት እና ቀለም ገበያ ላይ እናገኛለን። የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን ዲዛይነር ሀናን አህመድ ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከሰት ጭምብል መስፋት ከጀመሩት ሰዎች አንዷ ናት። የወጣቷን ጭምብል ግን ለየት የሚያደርገው አንድ ነገር አለ። መስማት የተሳናቸው ሰዎች የከንፈር እንቅስቃሴን እንዲያነቡ « ትራንስፓረንት በሆነ ላስቲክ አድርጌ ነው የሰራሁት» ትላለች ሀናን። ወረርሽኙ ሲከሰትም «በአቅሜ ሀኪሞቻችንን ወደ መርዳት ነበር የገባሁት» የምትለው ሀናን ጭምብል ሰፍታ ለዶክተሮች ማህበር አስረክባለች። በመቀጠል ደግሞ ለንግድ የሚሆኗት የዚህ አይነት እና ሌሎች ባህላዊ ጥበቦችን ተጠቅማ የምትሠራቸው ጭምብሎች ላይ ትኩረቷን አድርጋለች።

ዲዛነር ሀናን መስማት ለተሳናቸው የሠራችው ጭምብል ምስል Hanan Ahmed

የ 35 ዓመት ወጣቷ ግን ከኮሮና በፊትም ለባህላዊ ሥራዎች ልዩ ፍቅር ነበራት። በተለይ የሙስሊም ሴቶች አልባሳትን በባህላዊ መልኩ እየሠራች ታስተዋውቃለች፤ ትሸጣለችም። « ብዙዎቻችን የምንለብሰው ከሳውዲ የመጣ ነው። ብዙ አይነት ብሔር እያለን እኛ የምንለብሰው የራሳችንን ባህል የሚያንፀባርቅ አልነበረም። እና ለዚህ ነው አባያው ላይ ጥለት አድርጌ ያካተትኩት።» ትላለች። አባያ ማለት ሙስሊም ሴቶች ሰውነታቸውን ለመሸፈን የሚለብሱት ጥቁር ወጥ የአለባበስ አይነት ነው። ሂጃብ ደግሞ ፀጉርን የምንሸፍንበት ነው ትላለች ሀናን።
እነዚህንም አባያ እና ሂጃቦች ላይ የተለያዩ ባህላዊ የጥበብ ጥልፎችን በማካተት ኢትዮጵያዊ መልክ የምትሰጣቸው ሀናን ሌሎች በደማማቅ ቀለሞች ያሸበረቁ ልብሶችንም ትሠራለች። እነዚህ ደግሞ ካስታን ይባላሉ። አልባሳቱ ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያ ሞቃታማ ከተሞች ሀረር እና ድሬደዋ የተለመዱ ናቸው ። « ካስታኑ ላይ መሀል ላይ ነው ጥለት የተጠቀምኩት።» አልባሳቱም ምንም አይነት ሀይማኖትን የማይወክሉ በመሆናቸው በሁሉም ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተውላታል።
ሀናን ከሙስሊም እና ክርስትያን ቤተሰብ ነው የተወለደችው። የመጀመሪያ የአልባሳት ሥራዋ የሆነው አባያ ላይ ጥለት እንድትጨምር ያነሳሳትም እናቷ የሚለብሱት የሀበሻ ቀሚሶች እንደነበር ትናገራለች። « በጣም ጥለቶች እወዳለሁ፤ እና ለምን አልሞክርም ብዬ ህልሜን ለማሳካት የሞከርኩበት ነው« ትላለች።  
ሀናን በዚህ ሙያ ላይ መሥራት ከጀመተች ሁለት ዓመት ሆናት። ዛሬ ሰባት ሰዎችን ቀጥራ እየሠራች ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥራለች።  « በጣም ለመማር ጉጉት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ልክ እንደ ቤተሰብ ሆነን ነው የምንሰራው»
ምንም እንኳን የወጣቷ ሥራዎች ለሴቶች አልባሳት እና ማስዋቢያዎች ትኩረት ቢሰጥም የወንዶች አልባሳትን በባህላዊ  መልኩ ማዘጋጀት መጀመሯን አጫውታናለች። « የወንዶቹ ረዘም ብለው ጉልበት ላይ የሚደርሱ ከላይ የሚለበሱ ልብሶች ናቸው። እነሱም ላይ አንገቱ ጋር ጥለት ተጠቅሜያለሁ» ። በኮሮና ምክንያት ግን ሀናን ይህንን ስራዎቿን አውደርዕይ ላይ ማሳየት አልቻለችም።  ከዚህ በፊት ወደ ህንድ እየሄደች ልብሶቹን ታሰራ የነበረችው ሀናን ከአሁን በኋላ ሁሉንም ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጨረስ አቅዳለች። ሀናንም እንደ ሌሎች ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች ሁሉ የስኬቷ ምሥጢር  በራስ መተማመን ነው። « አላማ እና ግቤን ሁሌ እጽፋለሁ እና እንቅፋት ሲገጥመኝ እነዚህን መለስ ብዬ አያቻዋለሁ።»  ሀናን ከዚህ በፊት የበረራ አስተናጋጅ ሆና ትሰራ ነበር። የዲዛይነርነት ሙያዋ ግን ልትገፋበት የምትፈልገው ነው። ህልም እና እቅዷም በዚሁ አያበቃም ። « ገና ብዙ ህልም አለኝ» ትላለች ወጣቷ ዲዛይነር ሀናን አህመድ። ብዙ የስራ እድል ለሴቶች ከመፍጠር ባሻገር ትላልቅ የተባሉ መድረኮች ላይ ባህላዊ የሆኑ ስራዎቿን ማስተዋወቅ ትሻለች። 

ልደት አበበ

አባያ እና ካስታንምስል Hanan Ahmed

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW