በጥቃቱ 10 ሲገደሉ፣ከአስር የሚበልጡ ቆሰለዋል
ረቡዕ፣ መስከረም 4 2015
ማስታወቂያ
ትግራይ ርዕሠ ከተማ መቀሌ ዉስጥ ዛሬ በደረሰ የሰዉ አዉልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ።ከአስር የሚበልጡ ቆሰሉ።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ እንደዘገበዉ ዳግም አምባሳል የተባለዉ የመቀሌ መንደር ዛሬ ጠዋት ሁለቴ በድሮን ተደብድቧል።የመቀሌ የጤና ፅሕፈት ቤት፣ የሆስፒታሎች ባለስልጣናትና ባለሙያዎች እንዳሉት አብዛኞቹ ሰዎች የተገደሉና የቆሰሉት በመጀመሪያዉ ጥቃት የተጎዱትን ለመርዳት በአካባቢዉ የተሰባሰቡ ሰዎች በሁለተኛዉ ጥቃት ተመትተዉ ነዉ።የመጀመሪያዉ ጥቃት የደረሰዉ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከአርባ ግድም ሲሆን ሁለተኛዉ የደረሰዉ 3 ሰዓት አካባቢ ነዉ።የአይደር ሆስፒታል የበላይ ኃላፊ ክብሮም ገብረስላሴ እንዳሉት ከሟቾቹ 5ቱ የሞቱት ጥቃቱ በደረሰበት ስፍራ ሲሆን ሌሎቹ ወደ ሆስፒታል ሲጓዙ ነዉ።በጥቃቱ ከቆሰሉት መካከል አንዱ በመጀመሪያዉ ጥቃት የተጎዱትን በመርዳት ላይ የነበረ ሐኪም፣ ሌለኛዉ ደግሞ የካሜራ ባለሙያ ነዉ።የመቀሌ ከተማ የጤና ፅሕፈት ቤትም በሁለቱ ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸዉንና 13 መቁሰላቸዉን አረጋግጧል።ትናንት መቀሌ ዉስጥ በደረሰ ተመሳሳይ ጥቃት አንድ ሰዉ መቁሰሉ ተዘግቦ ነበር።የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እስከ ዛሬ ቀጥር ድረስ ስለጥቃቱ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ