1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

መቀመጫውን ካይሮ ያደረገው አዲሱ የአፍሪቃ የህዋ ኤጀንሲ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 29 2017

በጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም የአፍሪቃ ህብረት፤የአህጉሪቱን የህዋ ሳይንስ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የነደፈ ቢሆንም፤እንደ ሌሎቹ አህጉሮች የህዋ ሳይንስ ኤጀንሲ በአፍሪቃ ደረጃ ለማቋቋም ግን ሳይችል ቆይቷል። በቅርቡ ግን ለበርካታ አመታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ሰምሮ፤ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ የአፍሪቃ የህዋ ኤጀንሲ በይፋ ተመርቋል።

 የአፍሪቃ የህዋ ኤጀንሲ
የአፍሪቃ የህዋ ኤጀንሲ ፤በጎርጎሪያኑ ሚያዝያ 20 ቀን 2025 ዓ/ም በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በይፋ ተመርቋል።ምስል፦ Tinsae Alemayehu/DW

መቀመጫውን ካይሮ ያደረገው አዲሱ የአፍሪቃ የህዋ ኤጀንሲ

This browser does not support the audio element.

የህዋ ሳይንስ  ምርምር ለአዳጊ ሀገራት በጤና፣ በግብርና ፣በኢንዱስሪ፣ በማዕድን ምርት እንዲሁም የበይነመረብ አና የግንኙነት መስኮችን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ  አለው።ያም ሆኖ በአፍሪቃ ይህ ቴክኖሎጅ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በአህጉር ደረጃ ይህንን ዘርፍ የሚያስተባብር እና የሚደግፍ ተቋም አለመኖሩ ደግሞ ፤ቴክኖሎጅው በሚፈለገው ደረጃ ላለማደጉ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል።
በጎርጎሪያኑ ጥር  2016 ዓ/ም የአፍሪካ ህብረት ምክር ቤት፤ የአህጉሪቱን የህዋ ሳይንስ  ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የነደፈ ቢሆንም፤እንደ ሌሎቹ አህጉሮች የአፍሪቃን የህዋ ሳይንስ ኤጀንሲ በአህጉር ደረጃ ለማቋቋም ግን ሳይችል ቆይቷል።
በጎርጎሪያኑ ያለፈው ሚያዝያ 20 ቀን 2025 ዓ/ም ግን ለበርካታ አመታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ሰምሮ፤  በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ  የአፍሪቃ የህዋ  ኤጀንሲ በይፋ ተመርቋል። 

በሰሞኑ የኤጀንሲው ምረቃ የታደመው እና ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው ኩዩቢክ ስፔስ የሳተላይት ሲስተም የሽያጭ መሀንዲስ ሆኖ የሚሰራው ወጣቱ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ  ትንሳኤ አለማየሁእንደሚለው፤ የኤጅንሲው ምስረታ የአፍሪቃ ህብረት የ2063 አጀንዳ ዕቅድ አንዱ አካል ሲሆን፤ ምስረታው የዘገየውም በርካታ ተዋናዮች ያሚሳተፉበት በመሆኑ  ነው።

ትንሳኤ አለማየሁ፤ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው ኩዩቢክ ስፔስ የሳተላይት ሲስተም የሽያጭ መሀንዲስምስል፦ Tinsae Alemayehu/DW

የህዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ለአፍሪቃ ዘላቂ ልማት  

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ስር የተቋቋመው የአፍሪካ የህዋ ኤጀንሲ የዋና መሥሪያ ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ካይሮ  ሲሆን፤ አህጉራዊ የጠፈር እንቅስቃሴዎችን የማስተባበር፣ የአፍሪካ የጠፈር ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ እና በምርምር፣ ፈጠራ እና በህዋ ሳይንስ ትግበራ የአህጉሪቱን የልማት ግቦች የመደገፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። አህጉሪቱ የህዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ለዘላቂ ልማት ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው የተባለው፤ የአፍሪካ ስፔስ ኤጀንሲ (AfSA)  ከአውሮፓ፣ እስያ እና ከሌሎች አህጉራዊ የጠፈር ኤጄንሲዎች ጋር ሲነፃጸር ምስረታው የዘገዬ እና አመታትን የወሰደ በመሆኑ አህጉሪቱ ከዘርፉ መጠቀም የነበረባትን ዕድል አጥታለች። ያም ሆኖ ትንሳኤ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት ሊተኮር የሚገባው የኤጀንሲውን ግቦች፤ ውጤታማ በሆነ መንገድ ወደ መሬት ማውረድ ላይ ነው።

ከምረቃው በኋላ የህዋ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች እና ፖሊሲ አውጭዎች የተሳተፉበት እና የአፍሪካን የጠፈር ኢንዱስትሪ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርፅ የአፍሪካ የህዋ ሳይንስ (ሚያዚያ 21-24, 2025) መድረክ ተካሂዷል። በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት . የኬንያ የጠፈር ኤጀንሲ (KSA) ዋና ዳይሬክተር ሂላሪ ኪፕኮስጌይ እንዳሉት የድርጅቱ ምስረታ ፤የአፍሪካን የጠፈር ሥነ-ምህዳር በመገንባት አጋርነት እና ክልላዊ ቅንጅትን ለመፍጠር  ጠቀሜታው የጎላ ነው።ትንሳኤ በበኩሉ በአፍሪቃ እንዲህ ያለ ተጠሪ ተቋም መኖሩ ለአፍሪቃ ሀገራት በዘርፉ የሚያስገኘው ጠቀሜታ በርካታ መሆኑን  ያስረዳል።«ትልቁ ነገር ተጠሪ ተቋም መኖሩ ነው።ለምሳሌ ኢትዮጵያም ትሁን ፣ ደቡብ አፍሪቃ ፣ ጋና ወይም ናይጄሪያ ግብፅ ለየራሳቸው የሚያደርጉት ሙከራ ይኖራል።ሁሉንም የሚያስተሳስር አቅጣጫ የሚሰጥ አንድ ላዕላይ የሆነ ተቋም ሲኖር ደግሞ በጣም የበለጠ ያበረታል።»በማለት ገልጿል።በተጨማሪም የስልጠና ፣ገንዘብ ድጋፍ እና  ከሌሎች ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የቤተሙከራ እና የቴክኖሎጅ መሰረተ ልማቶችን ለማግኘት ኤጀንሲው እንደሚጠቅም ገልጿል።

ሀገራት ከመሬት ውጭ በጠፈር ላይ ለሚያደርጉት ምርምር እና ለሚያገኙት ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈቅድም ሆነ የሚከለክል ህግ የለም።ከዚህ አኳያ አፍሪቃም ልክ እንደሌሎቹ የበለፀጉ ሀገራት በህዋ ላይ  የሀብት ድርሻ ለማግኘት ምርምር ማካሄድ ትችላለች። ሆኖም ግን ትንሳኤ እንደሚለው ፤አህጉሪቱ አሁን የሚያስፈልጋት እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የህዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሬት ላይ ያሉ ሀብቶቿን በአግባቡ በመጠቀም እድገት ማምጣት ነው። 

በአፍሪቃ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የህዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሬት ላይ ያሉ ሀብቶቿን በአግባቡ ማልማት ነው።ምስል፦ Dirk Shadd/Tampa Bay Times/TNS/ABACAPRESS.COM/picture alliance

የተበታተኑ የአፍሪካ የጠፈር ምርምር ጥረቶችን ለማስተባበር  

በሌላ በኩል ፤እስካሁን የአፍሪካ የጠፈር ምርምር ጥረቶች  በአብዛኛው የተበታተኑ ናቸው። በጣት የሚቆጠሩ አገሮች ማለትም እንደ ደቡብ አፍሪቃ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ እና ኢትዮጵያ ብቻ  ብሔራዊ የጠፈር መርሃ ግብሮች አሏቸው።ስለሆነም፤ የአፍሪቃ የህዋ ኤጀንሲ በአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት መካከል የህዋ ሳይንስ ውጥኖችን ለማስተባበር ፣የጋራ ሀብቶችን ለማረጋገጥ ፣በተናጠል የሚያደርጉትን የጥረት ድግግሞሽን ለመቀነስ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የመደራደር አቅምን ለመፍጠር ያግዛል።
«ቢዝነስ ኢንተለጀንስ» የተባለው የአፍሪካ ገበያ ጥናትና ምርምር ፤በ2023 ባወጣው ዘገባ መሰረት በአፍሪቃ 15  ሀገራት  ከግንቦት 2023 ጀምሮ ሳተላይቶችን አምጥቀዋል። እንደ AfSA ያለ አህጉራዊ ኤጀንሲ መመስረት ደግሞ፤ የሕዋ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽነት እንደሚያሰፋ ይጠበቃል፣ ይህም ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በህዋ ላይ የተመሰረተ አቅም እንዲኖራቸው ያደርጋል። ከኢትዮጵያ አንፃርም የተለዬ ጠቀሜታ ይኖረዋል።«በኢትዮጵያ የፀደቀ የስፔስ ፖሊሲ አለ።በትግበራ ደረጃ ምን ላይ እንደደረሰ አናውቅም።ስለዚህ ይህንን ለማፋጠን ይረዳል።በግል ተቃማት ደረጃ  የ«ኮንሰልታንሲ» እና የ«ሪሰርች»  ወይም የዩንበርሲቲዎች በገንዘብም ይሆን በኔትወርክም ይሁን በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ስር ያሉ እንቅፋቶችን ወይም የሚጋጥሙ እክሎችን በአፍሪቃ እፔስ ኤጀንሲ በኩል ማሳለጥ ይችላሉ።የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን መምህራንን በተለያዩ የልምድ ልውውጦች የሚያሳትፉበትን መንገድ ይፈጥራል። እዚያም ሄደው መጎብኘታቸው ትልቅ እድል ነው።የኢንተርንሽፕ ፕሮግራሞች ይኖራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።በተረፈ የራሳቸውን አዲስ ቢዝነስ መፍጠር የሚፈልጉ ወጣቶችም የበለጠ የሚያሳልጥላቸው አንድ ኤጄንሲ አለ ማለት ነው። » በማለት አብራርቷል።

የመግባቢያ ስምምነት  ከአዲሱ የአፍሪቃ የህዋ ኤጄንሲ ጋር


በግብፅ አረብ ሪፐብሊክ አስተናጋጅነት የተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ፣የአለም አቀፍ የህዋ ኤጀንሲዎች እና አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል። በዚህ የምረቃ ሥነስርዓት ከተገኙት መካከል የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ (ESA) አንዱ ሲሆን፤ከአዲሱ የአፍሪቃ የህዋ ኤጄንሲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ተፈራርሟል።ይህም ወደፊት በመሬት ምልከታ፣ በሳተላይት ልማት፣ በመረጃ መጋራት እና አቅም ግንባታ ላይ ትብብር ለማድረግ መሰረት የሚጥል ነው ተብሏል። ስምምነቱ አፍሪቃ ከዓለማቀፉ የጠፈር ማህበረሰብ ጋር ያላትን ትብብር የሚያፋጥን እና የልምድ ልውውጥን እና ፈጠራን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማorቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
 
ፀሐይ ጫኔ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW