የሳውዲ ስደተኞች እሮሮ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11 2014መንግስት ዜጎቹን ለማውጣት የጀመረው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በሳምንት ሦስት ጊዜ ብቻ በረራ በማድረግ የተጀምረው የማስመለስ ሂደት ካለው የስደተኛ ቁጥር አንጻር በቂ አደለም ብሏል።
በሳውዲ እስርቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሁንም ሰቆቃቸው እንዳላበቃ ይናግራሉ። አስተያየታቸውን ለDW የሰጡ ስደተኞች እንደሚሉት በተለያዩ የሳውዲ እስርቤቶች በቀን አንዴ ምግብ እየተሰጣቸው በተፋፈጉ እስርቤቶች የስቃይ ኑሮ እየኖሩ ነው። አቶ ሙሃጂር መሐመድ በማሕበራዊ መገናኛ አውታሮች መለያቸው አቡከውስር ስለሳውዲ ስደተኞች መብት ተከራካሪ ናቸው። ኢትዮጵያውያን በእስርቤቶች ህመም፣ ርሃብ እንዲያም ሲል ሞት እጣፈንታቸው ሆኗል ይላሉ።
አቶ ሰይድ መሐመድ ለበርካታ አመታት በሳውዲ ኖሯል። የእድል ጉዳይ ሆኖ ባይታሰሩም ከእስርቤት ውጭ ያሉ ዜጉችም የገፈቱ ቀማሽ እንደሁኑ ነግረውናል።መንግስት ዜጎቹን ለማስመለስ የሚያስችል ግብረሃይል አቋቁሞ በጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት እስካሁን ከ7ሺ በላይ ዜጎችን ወደ ሃገርቤት መመለሱን የውጭጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። አሁን በሳምንት 3ቴ በእያንዳንዱ ቀንም እንዲሁ 3ቴ በረራ በማድረግ ከ102 ሺ በላይ ዜጎችን ለማውጣት የተያዘው እቅድ ስኬት ይጠራጠራል አቶ ሙሐጂር ወይም አቡከውስር።
በሳውዲ በሚገኙ ኤምባሲና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የሚሰጠው አገልግሎትም ያለውን የስደተኛን ቁጥር የሚመጥን አደለም ይላሉ አቶ ሰይድ መሐመድ
የማሕበረሰብ አነቃቂና የሳውዲ ኢትዮጵያውያን ስደተኞስ መብት ተከራካሪው አቶ ሙሐጂር ወይም አቡከውስር ይህንኑ የአቶ ሰይድን ሐሳብ ይጋራሉ።በጉዳዩ ላይ በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንላ ጽሕፈት ቤት፣ የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይና በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ከሳምንት በላይ የዘለቀ ሙከራ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካልንም።
ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ