1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቋጫ ያጣው የሕወሓትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍጥጫ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ረቡዕ፣ መስከረም 15 2017

የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር የትግራይ ታጣቂ ኃይሎችን ማዘዝ ይሁን መምራት አይችልም ሲል ሕወሓት ገለፀ ። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ የትግራይ ኃይሎች በአስተዳደሩ ስር ሆነው እየተመሩ ተልእኮ ይፈፅማሉ ብሎ ነበር።

Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

የሕወሓት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍጥጫ

This browser does not support the audio element.

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የትግራይ ታጣቂ ሐይሎችን ማዘዝ ይሁን መምራት አይችልም ሲል ሕወሓት ገለፀ። ጉባኤ ያደረገው ህወሓት ባወጣው መግለጫ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጦርነት ላይ የነበሩት የትግራይ ሐይሎች፥ በትጥቅ መፍታት፣ ተሃድሶ እና ወደ ማሕበረሰብ የመቀላቀል ሂደት ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ ሊመለስ እየጠበቀ ያለ እንጂ እንደ ፖሊስ እና ሚሊሻ በአስተዳደር ስር ሆኖ ተልእኮ የሚፈፅሙ አይደሉም ብሏል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ የትግራይ ኃይሎች በአስተዳደሩ ስር ሆነው እየተመሩ ተልእኮ ይፈፅማሉ ብሎ ነበር።

በተለያዩ ጉዳዮች እየተነታረኩ ያሉት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሰሞኑን ደግሞ ከትግራይ ታጣቂ ሐይሎች ባለቤትነት፣ የማዘዝ እና መምራት አጀንዳ ዙርያ የተለያዩ አቋሞች እያንፀባረቁ ይገኛል። ትላንት ማታ መግለጫ ያሰራጨው በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ጉባኤ ያደረገው ህወሓት፥ በቅርቡ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያወጣው መግለጫ በመቃወም፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ታጣቂ ሐይሎችን የማዘዝ ይሁን የመምራት ስልጣን የለውም  ብሏል። ህወሓት በመግለጫው ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጦርነት ላይ የነበሩት የትግራይ ሐይሎች፥ በትጥቅ መፍታት፣ ተሃድሶ እና ወደ ማሕበረሰብ የመቀላቀል ሂደት ወደ ሰላማዊ ህይወቱ ሊመለስ እየጠበቀ ያለ እንጂ እንደ ፖሊስ እና ሚሊሻ በአስተዳደር ስር ሆኖ ተልእኮ የሚፈፅም የመንግስት ተቀጣሪ አካል አይደለም ሲል ገልፆታል። የትግራይ ሐይሎች በግዚያዊ አስተዳደሩ የራሳቸው ውክልና ያላቸው ናቸው ያለው ህወሓት ከዚህ ውጪ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት ወደሆነው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ለመጠቅለል መሞከር አደገኛ እና ሰራዊቱ በሰንሰለታዊ አሰራር ለመቆጣጠር የወጣ ተቀባይነት የሌላው አካሄድ ብሎታል።

ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤ ያደረገው ህወሓት፥ በሕወሓት መካከል ክፍፍል እንዳለ አስመስሎ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እየቀረበ ያለው ሐሳብ አጣጥሏል። ህወሓት ልዩነቶቹ ለመፍታት ጉባኤ አድርጎ፣ ችግሮቹ የፈታ መሆኑ የጠቆመው መግለጫ፥ ይህ ትግል ያልተከተለ ቡድን ደግሞ በመንገድ ላይ ቀርቷል በማለት ከፓርቲው ውጭ መሆኑ ጠቁሟል። አሁን ያለው ትግል በህወሓት እና ህወሓትና የትግራይ ሐይሎች ለማፍረስ በግዚያዊ አስተዳደሩ ውስጥ መሽጎ ካለ ሐይል ጋር ነው ሲል ገልጿል።

የህወሓት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍጥጫ እንደቀጠለ ነውምስል Million Hailesilassie/DW

በዚህ የሁለቱ ቡድኖች ክፍፍል እና በተለይም በትግራን ሐይሎች ጉዳይ ዙርያ የያዙት የተራራቀ አቋም አስተያየታቸው ያጋሩን የሕግ ምሁር አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፥ ሁሉ ነገር ከፕሪቶርያ ስምምነት አንፃር እና በስምምነቱ መንፈስ መሰረት ሊታይ እንደሚገባ ያነሳሉ። በህወሓት ውስጥ ስላለው ክፍፍል ዙርያም የሕግ ምሁሩ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ አስተያየታቸው ያስቀምጣሉ።

በህወሓቱ መግለጫ ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም። ይሁንና እሁድ ዕለት መግለጫ አውጥቶ የነበረው ጊዜዊ አስተዳደሩ በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ችግር በሕወሓት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መካከል የተፈጠረ አለመግባባት አድርጎ ማቅረቅ የተሳሳተ ነው፣ ችግሩ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረ ነው ብሎ የነበረ ሲሆን ግዚያዊ አስተዳደሩ የዚህ ውዝግብ አካል እንዳልሆነ አስታውቆ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ሐይሎች በአስተዳደሩ ስር ሆነው እየተመሩ እና ከፖለቲካዊ አጀንዳዎች ገለልተኛ ሆነው ተልእኮአቸው እንደሚፈፅሙ ጠቅሶ እንደነበረ ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
ታምራት ዺንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW