1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቐለ ለቀድሞ የጦር ጉዳተኞች ሊሰጥ የታቀደው የመኖርያ መሬት እንዲታገድ ተጠየቀ

ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2017

በትግራይ ክልል፥ መቐለ ከተማ ሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ሌሎች ወንጀሎች አሳሳቢ ሆነዋል ሲል ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ የተባለው ተቃዋሚው ፓርቲ ዐሳወቀ ። ፓርቲው ሕገወጥ የመሬት ወረራ በመቐለ እየተፈፀመ ነው ብሏል ።

Äthiopien | Straßenszene in Mekelle
ምስል Million Haileselassie/DW

ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ፥ ሕገወጥ የመሬት ወረራ በመቐለ እየተፈፀመ ነው አለ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል፥ መቐለ ከተማ  ሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ሌሎች ወንጀሎች አሳሳቢ ሆነዋል ሲል ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ የተባለው ተቃዋሚው ፓርቲ ዐሳወቀ ። ፓርቲው ሕገወጥ የመሬት ወረራ በመቐለ እየተፈፀመ ነው ብሏል ።

በ2015 ዓመተምህረት በአዲስአበባ ተመስርቶ፥ በቅርቡ በመቐለ ጽሕፈት ቤት የከፈተው ተቃዋሚ ፓርቲ ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ትላንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ሕገወጥ ያለው የመቐለ ከተማ አስተዳደር  ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ የቀድሞ የጦር ጉዳተኞች ሊሰጠው ያቀደው የመኖርያ መሬት እንዲታገድ ጠይቋል ። በመቐለ ዙርያ ካሉት የእንደርታ ገጠር አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች መሬታቸው እየተነጠቁ፣ ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ ለዓመታት መዝለቃቸውን የሚገልፀው ይህ ፓርቲ፥ የዚህ ተቀጥያ የሆነ ተግባር ደግሞ አሁንም ተስፋፍቶ መቀጠሉን በመጥቀስ የክልሉና እና የመቐለ ከተማ አስተዳደር በግልፅ በመሬት ወረራ እና ሕገወጥ የመሬት ማደል ሥራ ላይ መጠመዳቸውን በማንሳት ወቅሷል።

የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃም ፅጌ "በመቐለ የተሰጠ ሁሉም መሬት በማጭበርበር የተወሰደ፣ ከመሬቱ ለሚነሳ ገበሬ ተገቢ ካሳ ያልተከፈለበት፣ በርካታ አባቶች እና እናቶች አይናቸው እያዩ መሬታቸው በእንቁላል ዋጋ እየተሸጠ ለስደት እና ልመና እየተዳረጉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። አሁን እየተናገርን ያለነው፥ የምንተነፍስበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንጂ ከዚህ በፊት ይህ ያጋለጡ ወንድሞቻችን የት እንደገቡ አይታወቅም፣ ፀረ ሕዝብ ተብለው መብታቸው ተገፏል" ብለዋል።

የመቐለ ከተማ አስተዳደር በክልሉ ላሉ  ለ1028 የጦር ጉዳተኞች በመቐለ ቤት መሥርያ መሬት ለማደል ማቀዱን  ከቀናት በፊት ዐሳውቆ የነበረ ሲሆን፥ ትላንት የተሰራጨው የአስተዳደሩ ደብዳቤ እንደሚያሳየው ደግሞ የተያዘው እቅድ ላልተወሰነ ግዜ መራዘሙ አመልክቷል።

በትግራይ ክልል፥ መቐለ ከተማ የሚገኘው የሰማእታት መታሰቢያ ሐውልትምስል Million Haileselassie/DW

ተቃዋሚው ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ እንደሚለው ግን የመቐለ ከተማ መሬት በፖለቲካዊ ውግንና ለታማኝ ካድሬዎች እየተሰጠ ነው ሲል ይከሳል። የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አብርሃም ፅጌ "የመቐለ መሬት የልማት ጉጅሌና የካድሬዎች ማባበያ ተደርጎ እየተወረረ መሆኑ ህዝባችን ተረድተህ፥ ይህ ለማስቆም እንድትታገል ጥሪ የምናቀርብ ሲሆን ለዚህ ጥሪ ምላሽ የማይሰጠው ከሆነ በቅርቡ ሰላማዊ ህዝባዊ ሰልፍ እንደምንጠራ እና ለዚህ እንድትዘጋጅ፥ መሬትህም እንድትጠብቅ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር  የሚጠበቅበትን ሰላም እና መረጋጋት የማስፈን ሥራ እየከወነ እንዳልሆነ እና በዚህም በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት እና ሌሎች ወንጀሎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ጨምሮ ገልጿል። በዚህ የፓርቲው ክስ ዙርያ ከከተማው አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW