1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

መተከል ዞን፤ ቡሌን ወረዳ የ«ሸኔ» ጥቃትና የነዋሪዎች ሥጋት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 3 2017

የቡሌን ወረዳ እና አካባቢው ነዋሪዎች ከ20 በላይ ሰዎች ከተገደሉበት እና ከተማዪቱ ላይ ጥፋት ካደረሰው የዐርቡ ጥቃት ወዲህ ሥጋት ውስጥ እንዳሉ ተናገሩ ። መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ትናንት ማታም ሦስት ቀበሌያትን ሊቆጣጠሩ ነው በመባሉ ነዋሪዎች በሥጋት ከቤት ውጪ ማደራቸው ተገልጧል ።

በበኒሻንጉል ክልል፤ መተከል ዞን መልከዓምድር
በበኒሻንጉል ክልል፤ መተከል ዞን መልከዓምድርምስል፦ Negasa Dessalegn/DW

የ«ሸኔ» የተባሉት ታጣቂዎች ሥጋት እንዳዣበበ ነው

This browser does not support the audio element.

በኒሻንጉል ክልል፤ መተከል ዞን፤ የቡሌን ወረዳ እና አካባቢው ነዋሪዎች 20 በላይ ሰዎች ከተገደሉበት እና ከተማዪቱ ላይ ጥፋት ካደረሰው የዐርቡ ጥቃት ወዲህ ሥጋት ውስጥ እንዳሉ ተናገሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) ታጣቂዎች ትናንት ማታም ሦስት ቀበሌያትን ሊቆጣጠሩ ነው በመባሉ ባጫረው ሥጋት ነዋሪዎች ከቤት ውጪ ማደራቸው ተገልጧል  

በመተከል ዞን  ቡሌን ወረዳ እና አጎራባች ቀበሌያት ነዋሪዎች ሰሞኑን የሸኔ ታጣቂዎች አደሩሰት ከተባለው መጠነ ሰፊ ጥቃት ወዲህ ሥጋት ላይ መሆናቸውን ዛሬ ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ ። የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው የሚባሉት ኃይላት ዐርብ ቡሌን ከተማ እና ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ ዐሥራ አምስት የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ከሃያ በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገልጧል ።

በትናንትናው ዕለትም እነኚሁ የኢትዮጵያ  መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) ታጣቂዎች፦ ዶቢ፣ ማጣና በኩጂ የተባሉ ሦስት ቀበሌዎችን ሊቆጣጠሩ መሞከራቸው ተገልጧል ።  ነዋሪዎች በሥጋት ከቤት ውጪ ማደራቸውን አክለዋል ።  «ማታ ይገባሉ፤ እንገባለን በሚል ሥጋት ማኅበረሰቡ እቤቱ አልተኛም አጋጣሚ ሁኖ ደግሞ ሳይገቡ አደሩ በአሁኑ ሰአት ጠቅላላ ማኅበረሰቡ ወረዳው በአጠቃላይ ቀበሌው ደግሞ ትልቅ ሥጋት ውስጥ ነው ያለው »

በዞኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በተደጋጋሚ ተፈጽሟል

ዐርብ ዕለት የቡሌን ከተማ ፖሊስ ጣቢያን አጥቅተዉ፥ በጣቢያዉ ዉስጥ የነበሩ ጦር መሣሪያዎችን ዘርፈዉ ብርቱ ጥፋት አደረሱ የተባሉት የኦነሠ ታጣቂዎች በትንሽ ግምት ቁጥራቸው ከአራት መቶ በላይ መሆናቸውን አንድ የዐይን እማኝ ተናግረዋል ። ከንጋቱ ዐሥራ አንድ ሰአት ከአምሳ ደቂቃ የጀምረው ጥቃት የተጠናቀቀው ከረፋዱ አራት ሰአት ከአርባ ደቂቃ አካባቢ ተጨማሪ ኃይል ከበለሳ አካባቢ ሲመጣ እንደሆነም ገልጠዋል ። «አድማ ብተናዎች ከግልገል በለስ አካባቢ ኃይል ጨምረው ነበር፤ ያው እስከዛ ድረስ ነበሩ ከዛ መጥተው የሽፋን ድምፅ ሲያሰሙ ነው ከተማውን ለቅቀው የወጡት ከዛም በኋላ ያው ሥጋቶች ነበሩ፤ ትናንትና አሁን ቀበሌዎችን ለመቆጣጠር ሞክረው ነበር » 

በኒሻንጉል ክልል፤ የመተከል ከተማ ምስል፦ Negassa Dessakegen/DW

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው  የቦሮ ዴሞክራሴያዎ ፓርቲ  የውጭ ዓለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ ዐርብ ዕለት ጥቃት አደረሱ የተባሉት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ አሁንም በበርካታ ቀበሌዎች መኖሩን ገልጠዋል ። «አሁን ባለኝ መረጃ  የሸኔ ሽብር ቡድን  ምሥራቅ ወለጋ አካባቢ በፀጥታ ኃይል ሲመታ ብዙ ቁጥር ያላቸው ኃይሎች ዐባይን ወንዝ ተሻግረው ነው ወደ መተከል የገቡት፤ ወደ ድባጤ ወረዳ ብዙ ቀበሌዎች ውስጥ አሁን በብዛት የሸኔ እንቅስቃሴ አለ »

እነኚሁ ታጣቂዎች ወደ መሀል ከተማ ከመዝለቃቸው አስቀድሞ ጥቃት ያደረሱት የአድማ በታኝ ፖሊሶች ካምፕ ላይ መሆኑም ተገልጧል ። ታጣቂዎቹ ባንኮችን እንደመዘበሩ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማትን እንደሰባበሩ፤ በርካታ የመንግሥት ተቋማት ላይ ብርቱ ጥፋት እንዳደረሱ፤ የግል የንግድ ቤቶች እና ንብረቶችን እንደመዘበሩም ነዋሪዎች ገልጠዋል ። «ወደ ዐሥራ አንድ አድማ በታኞችን ገድለዋል፤ ወደ ሦስት አራት ፖሊሶችን ገድለዋል   ወደ አራት አምስት ፖሊስ ቆስለዋል ንጹሐን ግለሰብ ተጎድቷል፤ ብዙ ንብረት ተዘርፏል፤ እና በጣም ዘግናኝ ጊዜ ነው ያሳለፍነው »

ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል

በዐርቡ ጥቃት 6 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው፤ ሴቶች መደፈራቸው እና የወርቅ ጌጦቻቸው መዘረፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል ። በዛሬው ዕለት ቃለ መጠይቁን ባደረግነበት ከሰአት አካባቢ ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል ወደ ከተማዪቱ እየገባ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል ። «የመከላከያ ሠራዊት አሁን በዚህ ሰአት ደርሷል አሁን አሁን አሁን ዕያየናቸው አቀባበል እያደረግንላቸው ነው » 

ታጣቂዎች በአካባቢው ላይ ጥቃት ለማድረስ ቀደም ሲል ይዝቱ ስለነበር ከመንግሥት ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ አልተደረገም ሲሉ ግን ነዋሪው ቅሬታቸውን አሰምተዋል ። «ወረዳው ላይ ትንሽ የጥንቃቄ ጉድለትም ያለ ይመስለኛል ያሉት አድማ በታኞችም ከዐርባ ከሠላሳ አይበልጡም ያንን አስተካክለው ጥበቃ መደረግ እያለበት በቸልተኝነት ሳይደረግ ቀረ »

ቡሌን ከተማ ከመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ 100 ኪሎ ሜትር ግድም ትርቃለች ምስል፦ Negassa Desalegn/DW

ቡሌን ከተማ ከመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ  100 ኪሎ ሜትር ግድም ትርቃለች ። ዶ/ር መብራቱ ታጣቂዎቹ ጥቃት ያደረሱት  የኮማንድ ፖስትን አልፈው ነው ብለዋል ።

በአካባቢው «የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የኮማንድ ፖስት አለ»

«የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ኮማንድ ፖስት አለ፤ ጋሌቻ የሚባል ቦታ ላይ እሱን አልፈው ነው እንግዲህ የመጡት በዙሪያው በሙሉ በሸኔ ተከብቦ ነው ያለው እዛ ያለው ኮማንድ ፖስት ራሱ እንዴት እንደሆነም ማኅበረሰቡ ራሱ ጥያቄ እያነሳ ነው እነሱ እያሉ እንዴት እዛ ያለው ማኅበረሰብ ይጎዳል የሚሉ ጥያቄዎች አሉ »

ጥቃቱን አደረሰ ከተባለው ታጣቂ ኃይል በኩል ስለ ጥቃቱ በይፋ የተባለ ነገር የለም ።  የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቶ ጋር ደውለን ስብሰባ ላይ መሆናቸው በመግለጥ ቆይተን እንድንደውል ነግረውን ነበር ፤ ሆኖም ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስላካቸው አይነሳም ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW