1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“የአንቅስቀሰሴ ገደብ” በኦሮሚያ ክልል

ረቡዕ፣ ጥር 22 2016

“ያው ሰውም እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪም የለም፡፡ የጸጥታ ኃይሎች እያስገደዱ ብቻ ሰው መናሃሪያ አከባቢ ስሰባሰብ በግዳጅ ከሚሄዱት አንድ ሁለት ተሸከርካሪዎች ውጪ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡“ ከምዕራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ

ባልታወቁ አካላቶች ተጥሏል የተባለu የእንቅስቃሴ ገድብ በኦሮምያ ክልል
ባልታወቁ አካላቶች ተጥሏል የተባለu የእንቅስቃሴ ገድብ በኦሮምያ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

“የአንቅስቀሰሴ ገደብ” በኦሮሚያ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች ተጥሏል በተባለው የዝዉዉር  ገደብ የማህበረሰቡን እለታዊ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ እየተነገረ ነው፡፡ ከተለያዩ አከባቢዎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት እሁድ አመሻሽ 12፡00 ሰኣት የጀመረው የእንቅስቃሴ ገደብ ከአከባቢ አከባቢ የመሚንቀሳቀስ ማህበረሰብም ሆነ ተሽከርካሪዎች እንደማይስተዋሉ ነው የሚነገረው፡፡

የተሽከርካሪዎች መቃጠል

መች እና ከየት እንደሚተላለፍ ባይታወቅም ተጠርቷል የተባለው የእንቅስቃሴ ገደቡ ከእሁድ 12 ሰኣት ምሽት እንደጀመረ ነው የሚነገረው፡፡ በዚሁም ከቦታ ቦታም ሆነ ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደረገው ጉዞ በነዚህ ሶስት ቀናት ተቀዛቅዞ ስለማለፉም ተስተውሏል፡፡ ከዚህ በፊት ሌሊት ላይ በርካታ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው በተነገረለት የወሊሶ-አዲስ አበባ መንገድ ላይ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ከሰዓትም አንድ ‘አይሱዙ’ የተባለ እቃ ጫኝ ተሽከርካሪ ቱሉ ቦሎ ከተማ አቅራቢያ ስለመቃጠሉ ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የአይን እማኝ ገልጸውልናል፡፡

ከቱሉ ቦሎ ከተማ 5 ኪ.ሜ ገደማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ሰኞ 10 ሰኣት ገደማ የእንቅስቃሴ ገደቡን ጥሶ የሚሄድ ያሉት አንድ አይሱዙ ተሽከርካሪ መቃጠሉን ያነሱት አስተያየት ሰጪው፤ የእንቅስቃሴ ገደቡ ከእሁድ 12 ሰዓት ጀምሮ  መጣሉን ገልጸዋል፡፡ ለእንቅስቃሴ ገደቡ ጥሪውን ያስተላለፈውን አካል ማንነት እንደማያውቁ የገለጹት አስተያየት ሰጪው “ጥሪው በማህበራዊ ሚዲያም ይተላለፍ ወይም በሌላ መንገድ ተጥሏል የተባለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ሁሉም ማህበረሰብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያውቃል” ሲሉም ነው ያስረዱት፡፡ በዚህ መስመር አልፎ አልፎ ሲሄዱ መንገድ ላይ ከሚታዩት ውስን ተሽከርካሪዎች ውጪ የትራንስፖርትም ሆነ አጠቃላይ የንግድእንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ መሰንበቱንያመለከቱት የቱሉ ቦሎው ነዋሪ፤ ገደቡስ እስከ መቼ ይቀጥላል ለሚለው መልስ የላቸውም፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የወሊሶ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ካለፉት ሁለት ቀናት በተሻለ በዛሬው እለት ውስን የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ከአዲስ አበባ እና ወልቂጤ-ጅማ መስመር ሲንቀሳቀሱ መስተዋሉን ገልጸዋል፡፡ “ህዝብ የጫኑ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ወደ ወልቂጤና ጅማ ያልፋሉ፡፡ ከወሊሶ የሚሰማሩ ተሽከርካሪዎች ግን እየተንቀሳቀሱ አደለም” ብለዋል፡፡

እንቅስቃሴ አልባ መንገዶች በኦሮሚያ ክልልምስል Seyoum Getu/DW

የእቅስቃሴ ገደቡ በዘርፉ የሚተዳደሩትን ስለመጉዳቱ

በሾፌርነት የሚተዳደሩ አንድ  ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አስተያየት ሰጪም የእንቅስቀሰሴ ገደቡ የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙበትን ስራ ፈተና ውስጥ ማስገባቱን አስረድተዋል፡፡ “ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ትነስም ትብዛም በዚሁ ስራ በምናገኘው ነው የእለት ኑሮአችን ስንገፋ የነበረው፡፡ አሁን ግን ገደቡ በዚህ ከቀጠለ የት ነው የምንገባው የሚለው አስግቶናል፡፡ አንድ አንድ ታርጋቸውን እየፈቱ ከሚንቀሳቀሱ ውጪ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወድቀናል” ነው ያሉት፡፡

ሌላው ከምዕራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም እንቅስቃሴው እጅጉን ተመናምኖ መስተዋሉን አንስተዋል፡፡ “ያው ሰውም እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪም የለም፡፡ የጸጥታ ኃይሎች እያስገደዱ ብቻ ሰው መናሃሪያ አከባቢ ስሰባሰብ በግዳጅ ከሚሄዱት አንድ ሁለት ተሸከርካሪዎች ውጪ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ አሁን ዛሬ እሮብ የገቢያ ቀን ነበር እኛ ጋ፤ ግን ገቢያው ቆሟል ለማለት እራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም የለም፡፡”

በዚህ ወረዳ ዳንጎተሬ ሲሞንቶ ፋባሪካ እና ሙገር ሲሚንቶን ጨምሮ የተሽከርካሪዎችን ምልልስ የሚጠይቁ በርካታ እለታዊ ስራዎች ቢኖሩም እንቅስቃሴ ሁሉ ተስተጓጉሎ መታየቱንም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡ ስለጉዳዩ ለኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ቢሮ እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ደውልን መረጃውን ለማጥራት ያደረግነው ጥረት ግን ኃላፊዎቹ ስልካቸውን ሳያነሱልን በመቅረታቸው ጥረቱ አልሰመረም፡፡

ስዮም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW