1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንገድ ዳር ያሉ የሱዳን ስደተኞች አቤቱታ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23 2016

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ከመጠለያ ጣቢያቸው ወጥተው በመንገድ ዳር ያሉ የሱዳን ተፈናቃዮች ለተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረት ተጋልጠናል አሉ ። አዲስ በተሠራው እና «አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ» በተባለው ሥፍራ የገቡት ደግሞ የተሻለ ፀጥታ ቢኖርም የውኃ እጥረት አለብን ብለዋል ።

Äthiopien | Flüchtlingscamp vertriebener aus dem Sudan
ምስል UNCHCR

የሱዳን ስደተኞች የፀጥታና የመሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረቶች አጋጥሞናል ብለዋል

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ከመጠለያ ጣቢያቸው ወጥተው በመንገድ ዳር ያሉ የሱዳን ተፈናቃዮች ለተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረት ተጋልጠናል አሉ ። አዲስ በተሠራው እና «አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ» በተባለው ሥፍራ የገቡት ደግሞ የተሻለ ፀጥታ ቢኖርም የውኃ እጥረት አለብን ብለዋል ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በበኩሉ በቅርቡ በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ አካባቢው መድረስ እንዳልቻለ አመልክቷል ።

ካለፈው ግንቦት ወር 2016 ዓ.ም መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ  ከ1ሺህ 300 በላይ የሱዳን ስደተኞች የፀጥታና የመሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረቶች አጋጥሞናል በሚል ከአውላላና ኩመር መጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው መንገድ ዳር ላይ ናቸው፡፡ ስደተኞቹ እንደሚሉት በአሁኑ ሰዓት ለከፍተኛ የርሀብ፣ የደህንነትና የህክምና መጓደሎች አጋጥሟቸዋል፡፡

የመንገድ ዳር ስደተኞች አስተያት

አብዱሰመድ አብደላ የተባለ ስደተኛ ለመሰረታዊ አገልግሎቶች ችግር ከተጋለጡ 3 ወራት እንዳለፈ ነው ለዶይቼ ቬሌ የገለፀው ፡፡ "ዋናው ችግራችን የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ችግር ነው፣ ምግብ የለም፣ ውሀ የለም፣ የፀጥታ ችግር አለብን፣ መጠለያውን ማንም አይጠብቀውም” ብሏል፡፡

ሀሰን ኡመር የተባለ ሌላ  መንገድ ዳር ካሉ ስደተኞች መካከል  የሚገኝ ስደተኛ በቅርቡ ታጣቂዎች ሁለት ስደተኞችን ከገደሉና ሌሎችን ካቆሰሉ ጀምሮ ማንም መጥቶ የጠየቀን አካል የለም ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፣ የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት ችግርም ተባብሶ መቀጠሉን ተናግረሯል፡፡

ተፈናቃዮች ለመሰረታዊ አገልግሎቶች ችግር ከተጋለጡ 3 ወራት እንዳለፈ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋልምስል UNCHCR

ምግብ እርስበርሳቸው እየተበዳደሩ የሚገልፀው ሀሰን፣ የርሀብና የህክምና ችግሩ ከፍተኛ እንደሆነ አብራርቷል፣ ህክምናም ቢሆን ስደተኛ ሀኪሞች ከሚያደርጉት ርዳታ ውጪ ምንም ነገር እንደሌለ ነው የገለፀው፣  በቅርቡ ባልታወቁ ታጣቂዎች ጉዳት ደርሶባቸው ቆሰሉ ስደተኞች በመድኃኒት እጥረት ከቁስላቸው ሊያገግሙ እንዳልቻሉ አስረድቷል፡፡

በ"አፍጥጥ”መጠለያ የሚገኙ ስደተኞች አስተያየት

ከአውላላና ኩመር ከ1ሺህ 500 በላይ ስደተኞች ወደ አዲሱ አፍጥጥ ወደተባለው የስደተኞች መጠለያ መግባታቸውን ደግሞ በዚሁ በአፍጥጥ በተባለው አዲሱ መጠለያ ጣቢያ የሚገኝ ሞሐመድ ኑር የተባለ ስደተኛ አመልክቷል፣ የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ በአዲሱ መጠለያ መኖሩን ያመለከተው ሞሐመድ የውሀ ችግር ግን እንዳጋጠማቸው ተናግሯል፡፡

ወደመጠለያው ከገቡ ስደተኞች መካከል  እንደሆነ የሚገልፀው ሞሐመድ፣ በቅርቡ በአጠቃላይ 26 ሙሉ ተሸከርካሪዎች ወደ 1ሺህ 500 ስደተኞችን ይዘው ወደ አዲሱ መተለያመድረሳቸውን ተናግሯል፡፡ በመንገድ ዳር ካሉ ስደተኞች መካከል በጣም ጥቂቶቹ እንደተመለሱ ሞሐመድ ጠቁሞ እነርሱም ይመጣሉ በሚል እየተጠበቁ እንደሆነም አመልክቷል፡፡

በመንገድ ዳር ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አዲሱ መጠለያ ጣቢያ የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ ካለ፣ ለምን ወደዚያ መዛወር እንዳልፈለጉ ጠይቀን ነበር፣ "ፍላጎታችን ወደ አገራችን መመለስ ነው" ብሏል፡፡

1ሺህ514  ስደተኞችም ወደ አዲሱ መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን የተመድ (UNHCR) በደብዳቤው አመልክቷልምስል UNCHCR

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ምላሽ

የተነሱ  የመሰረታዊ ጉዳዮች እጥረቶችን በተመለከተ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለዶይቼ ቬሌ በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ በየጊዜው መንገድ ዳር ያሉትን ጨምሮ በኩመርና አውላላ ያሉ ስደተኞችን በቅርበት እንደሚከታተል አመልክቷል፡፡  አስፈላጊ የሆኑ የምግብ፣ የውሀ፣ የህክምና አገልግሎቶችንም ያለማቋረጥ ሲቀርብ እንደነበረም አክሏል፡፡ "በቅርቡ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከመተማ ጎንደር ባለው መስመር ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሁኔታ ስለፈጠረብን በጊዜያዊነት ተንቀሳቅሶ ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት አላስቻለም” ብሏል፡፡

መንገድ ዳር ያሉ ስደተኞች ደህንነታቸው በተሻለ ሁኔታ ወደሚጠበቅበት ወደ አዲሱ መጠለያ ጣቢያ "አፍጥጥ” እንዲገቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አሳስቧል፡፡ 1ሺህ514  ስደተኞችም ወደ አዲሱ መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በደብዳቤው አመልክቷል፡፡ ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግስትንና የሀገሪቱን ሕግጋት አክብረው እንዲኖሩ ጠይቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW