መንግሥት የበጀት ጉድለት ለመሸፈን በዘጠኝ ወራት 194.6 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ተበድሯል
ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የመንግሥት የፋይናንስ ሥርዓት የገጠሙትን ተደራራቢ ችግሮች ተቋቁሞ "ጤናማ" ሆኖ መዝለቁን ለማስረዳት ቢጥሩም በሪፖርታቸው የተካተቱ ቁጥሮች የአገሪቱ ኤኮኖሚ ብርቱ ቅርቃር ውስጥ መግባቱን የሚያሳብቁ ነበሩ። አቶ አሕመድ ግንቦት 9 ቀን 2015 ለቋሚ ኮሚቴው የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት ሲያቀርቡ መንግሥታቸው እና የአገሪቱ ኤኮኖሚ የገጠሟቸውን ችግሮች አልሸሸጉም።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተያዘው የበጀት ዓመት 446.5 ቢሊዮን ብር ገቢ የመሰብሰብ ዕቅድ እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። "የፌድራል መንግሥት በዘጠኝ ወራት በቀጥታ በጥሬ ገንዘብ ማዕከላዊ ግምዣ ቤት 266.4 ቢሊዮን ብር ገቢ የሆነ ሲሆን በአንጻሩ 459 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል" ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። አቶ አሕመድ የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ከአገር ውስጥ 194.6 ቢሊዮን ብር መንግሥት መበደሩንም አስረድተዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምጣኔ-ሐብታዊ ዳፋ
የገንዘብ ሚኒስትሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና "ያስከተላቸው ተያያዥ ጫናዎች" የመንግሥት ወጪ በማናር "የሀገር ውስጥ ብድር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር" ማድረጋቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል። ይህም "በመንግሥት በጀት እና በማክሮ ኤኮኖሚው ላይ ጫና አሳድሯል።"
"በሀገራችን አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ምክንያት ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች በመፈጠራቸው በኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊገኝ የታሰበው ገቢ በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘቱ ለፌድራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለ2015 በጀት ዓመት የተፈቀደውን በጀት በሚፈለገው መጠን ፋይናንስ ማድረግ ላይ ጫና ተፈጥሯል" ያሉት አቶ አሕመድ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዓለም አቀፍ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ በማደጉ ምክንያት "የዋጋ ግሽበት ጫና በከፍተኛ ደረጃ" መፈጠሩንም ገልጸዋል። ሚኒስትሩ በመንግሥት በጀት ላይ ተጽዕኖ ፈጥረዋል ካሏቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች ጋር የነበራት ግንኙነት በጦርነት ምክንያት በመሻከሩ የተከሰተ ነው።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጥቅምት 23 ቀን 2015 በደቡብ አፍሪቃ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት ቢገታም የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ከዳፋው እንዳልተላቀቀ የአቶ አሕመድ ያቀረቡት ሪፖርት ይጠቁማል። መንግሥታቸው "በዘጠኝ ወራት ከልማት አጋሮች በዕርዳታ እና በብድር 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት" አቅዶ የነበረ ቢሆንም የተሳካለት ግን "በዕርዳታ 1.4 ቢሊዮን ዶላር በብድር 404.4 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 1.8 ቢሊዮን ዶላር" ነው።
በጦርነቱ ምክንያት "አንዳንድ የልማት አጋሮች ያልተገባ ጫና በማድረጋቸው እና የሚሰጡትን የልማት ትብብር ፋይናንስ" በመለወጣቸው መንግሥት ያቀደውን ማግኘት ሳችል እንደቀረ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አቶ አሕመድ በማብራሪያቸው "ያቀዱትን ገንዘብ" ያልሰጡ የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት አጋሮችን "ኃላፊነታቸውን" አልተወጡም ሲሉ ተችተዋል። የሁለት ዓመታቱ ጦርነት በተካሔደባቸው ክልሎች ተግባራዊ ይደረጉ የነበሩ ፕሮጀክቶች መቋረጥ እና መንግሥት ከአጋሮቹ ያገኝ የነበረው የበጀት ድጋፍ መቆምም ተጨማሪ ተጽዕኖ የፈጠሩ ናቸው።
አቶ አሕመድ "በዘጠኝ ወር ከልማት አጋሮች በዕርዳታ እና በብድር 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲፈስ ታቅዶ፤ በዕርዳታ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የፈሰሰ ሲሆን በብድር 426.3 ሚሊዮን ዶላር፤ በድምሩ 1.8 ቢሊዮን ዶላር የፈሰሰ ሲሆን አፈጻጸሙም ከዘጠኝ ወር ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር 70.1 በመቶ ነው" ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል። በገንዘብ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መሰረት "አንዳንድ የልማት አጋሮች ከሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት ጋር በተያያዘ በተለይ በበጀት ድጋፍ መልክ ለመስጠት የታቀደውን ድጋፍ በማቆማቸው" የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀደውን ገንዘብ አላገኘም።
የገንዘብ ሚኒስቴር ያካሔደው "የጦርነት እና ግጭት ጉዳት እና ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት" የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 20.4 በመቶ ወይም 22 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጉዳት እና 5.5 በመቶ ወይም 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኤኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዳስከተለ ይፋ አድርጓል። ኤኮኖሚው በአጠቃላይ የደረሰበት ኪሳራ በሰነዱ መሠረት 28 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ነው። በሪፖርቱ መሰረት "ግጭት እና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ወደ ከፋ ድህነት" ገብተዋል። ኢትዮጵያ በጦርነቱ የወደመውን መልሶ ለመገንባት እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል። አቶ አሕመድ ለመልሶ ግንባታው ከልማት አጋሮች ጠንከር ያለ ዕገዛ እንፈልጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በዘጠኙ ወራት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ግዢ እንዲያዘገዩ ታዘዋል፤ መንግሥትም "ያልተጀመሩ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን" ወደሚቀጥለው ዓመት ለማስተላለፍ ተገድዷል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት 29 ቢሊዮን ብር ለውጭ፤ 59.4 ቢሊዮን ብር ለአገር ውስጥ ዕዳ መንግሥታቸው እንደከፈለ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የፌድራል መንግሥቱ "ጥገኛ" የተባሉት ክልሎች የበጀት ፍላጎት
የአቶ አሕመድ ሽዴን ሪፖርት ያደመጠው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት "አንዳንድ ክልሎች የተደለደለላቸውን በጀት ቀድሞ በነበረው የማዳበሪያ ዕዳ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስለማይተላለፍላቸው የሠራተኛ ደመወዝ እንኳን መክፈል አልቻሉም" ብለዋል።
"በአዳዲሶቹ ክልሎች ላይ ብቻ ሳይሆን ነባሮቹም ክልሎች አካባቢ ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ እንኳን ለመክፈል" ችግር መታየቱን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አብርሐም አለማየሁ "አንዳንዱ ጋ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ ላልተፈለገ ኹከት ክልሎች እየተዳረጉ ያለበት ሁኔታ" መኖሩን ጠቁመው ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
የክልሎች የበጀት ጥገኝነት ከኤኮኖሚው አወቃቀር፤ በፌድራል መንግሥት እና በክልሎች መካከል ካለው የታክስ አሰባሰብ ኃላፊነቶች ጋር የተገናኘ መሆኑን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ "ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳይ" መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል። ይሁንና አቶ አሕመድ "አንዳንድ" ያሏቸው አዲስ እና ነባር ክልሎች በእርግጥም የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ ለመክፈል "ጫና ውስጥ መውደቃቸውን" አረጋግጠዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሲዳማ ክልሎች ችግሩ እንደገጠማቸው ጠቅሰዋል። ለክልሎቹ የፌድራል መንግሥት በቀጥታ ብር መስጠት እንደማይችል የገለጹት አቶ አሕመድ "ለተወሰኑት በተለይ የከፋ ችግር ላለባቸው ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ" ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል። ችግሩን "የማስታመም እና የማስታገስ ሥራ መስራት እንችላለን" ያሉት አቶ አሕመድ "በተለይ በክልሎች እየተፈጠሩ ያሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች እና የሰው ኃይል ስብጥር እጅግ በጣም ገዝፏል" ሲሉ ተደምጠዋል።
"የወረዳ መዋቅር በስፋት ይፈጠራል፤ የዞን መዋቅር በስፋት ይፈጠራል። በእያንዳንዱ የወረዳ መዋቅር ያለው የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ብዛት በጣም ብዙ ነው። የተሿሚ ብዛት በጣም ብዙ ነው። የሚቀጠረው የሰው ኃይል በጣም ብዙ ነው። የሲቪል ሰርቪስ መጠኑ በአገር ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ያበጠው በክልሎች ምክንያት ነው" በማለት የችግሩን ምንጭ ዘርዝረዋል። "ክልሎች መዋቅራቸውን መልሰው መፈተሽ አለባቸው። አቅማቸውን ያገናዘበ መንግሥታዊ መዋቅር የወረዳ እና የዞን አስፈጻሚ አደረጃጀት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በቀጣይ ሪፎርም መደረግ ይኖርበታል" የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ