መንግሥት 125 ኢትዮጵያውያንን ከሊባኖስ መለሰ
ሰኞ፣ ጥቅምት 18 2017መንግሥት 125 ኢትዮጵያውያንን ከሊባኖስ መለሰ
ትናንት እና ዛሬ 125 ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ ወደ ሃገራቸዉ መመለሳቸዉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በመካከለኛው ምሥራቅ እየበረታ የመጣውን ጦርነት ትከትሎ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የቆዩ እና ወደ አገራቸው ለመመለስ ሰነድ አሟልተው እና ተመዝግበው የነበሩ 125 ኢትዮጵያውያን ከቤይሩት እንዲወጡ ስለመደረጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
"ይሄ የማስወጣቱ ሂደት እጅግ ውስብስብ ነው። የአገሪቱ መንግሥት መፍቀድ አለበት"
"መመዝገብ ብቻ ለመውጣት በቂ አይደለም ያሉት ቃል አቀባዩ ቤይሩት ከሚገኘው ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን አሁንም ለችግር ተተጋሉጡ ዜጎችን የማስወጣቱ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል። የአየር ትራንስፖርት ችግር ግን የሥራው እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል።
"አንዱ ትልቁ ቁልፍ ችግር የትራንስፖርት ችግር ነው። ሚድል ኢስት ኤርላይን የሚባል ብቻ ነው እየወጣ ያለው። ሌላው ከሰነድ ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው"
የኢትዮጵያ መንግሥት ሊባኖስ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ የተባሉ 51 ኢትዮጵያውያንን ከሳምንታት በፉት ወደ አገራቸው መመለሱን አስታውቆ ነበር። ቤይሩት ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ጦርነትን በመሸሽ እየተንከራተቱ መሆናቸዉን የሚናገሩ ኢትዮጵያዉያን አስተያየት ሰጭዎች መንግሥት አሁንም በፍጥነት እንዲደርስላቸው እና ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲያስወጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸዉን የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ዘግቧል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር