መንግስት በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ ተጠየቀ
ዓርብ፣ መጋቢት 1 2015
የኢትዮጵያ መንግሥት በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የጣለውን ገደብ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ቲክቶክ እና ዩቱብ የተሰኙ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ከዘጉ አንድ ወር ሊሆናቸው እንደሆነ አስታውሷል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክርቤት ባወጣው መግላጫ እና ለዶቼ ቬለ/DW/ በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያም ድርጊቱን ተቃውሟል።
መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች ግጭቶች ሲፈጠሩ በፍጥነት የሚወስደው እርምጃ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ማቋረጥ ከሆነ ሰነባብቷል። መንግሥት ግጭቶች እንዳይባባሱ ለመቆጣጠር ነው የሚል ምክንያት በተደጋጋሚ ቢገልጽም የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ግን ድርጊቱ የመናገር ነጻነትን የሚገድብ ነው ሲሉ ይቃወማሉ።
በቅርቡም በኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የተፈጠረውን አለመግባባት ተንተርሶ አሁንም የማሕበራዊ መገናኛ ዜዴዎች ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል እንዲገደቡ ተደርጓል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካቃ ምክትል ኃላፊ ፋሊቪያ ማዋንጎቭያ እንዳሉት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሕዝቡን የመናገር ነጻነት መብትን መጣስ ቀጥለውበታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክርቤት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉም " የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አባል የሆኑ የሚድያ አካላት ስራቸውን በግባቡ መስራት መቸገራቸውን መረጃዎችን በፍጥነት ለጝብረተሰቡ ለማረስ በተለም ኢንተርኔትን እንደ ዋነኛ ማሰራጫ የሚጠቀሙ መገናኛ ብዙሃን መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን ተቸግረዋል። እና ይሄ መቆም ይኖርበታል፤ መስተካከል ይኖርበታል" ብሏል።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የትንታኔ ሥራዎቹን በዩቱብ በማቅረብ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ቴዌድሮስ አስፋው ገደቡ በሥራዎቹ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሆነገልጿል። አዲስ ዘይቤ የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊ አቤል ዋበላም የቴዎድሮስን ሐሳብ ይጋራል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክርቤት ምክትል ሰብሳቢ ታምራት ኃይሉ በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ያለው ክፍተት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት እንዳለበትና መንግሥትም የመናገር ነጻነት ማክበርና ማስከበር እንዳለበት ጠይቋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመግለጫው መንግሥት ይህን ገደብ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ጠይቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ሽዋዮ ለገሰ