1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

መንግስት አፋጣኝ ጸጥታን በማስከበር ዘላቂ መረጋጋት እንዲያመጣ ተጠየቀ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ግንቦት 28 2018

ዘጠኝ ሲቪል ዜጎች እና ሁለት የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች በደለታ ጨፋ ቀበሌ በእሁድ እና ሰኞው ጥቃት መገደላቸውን የሚያረጋግጡት አስተያየት ሰጪው የግጭቱ ሰለባ፤ አሁን ላይ በርካታ ዜጎች በሱንቴ ቅድስት ማሪያም እና እሬቻ ቅዱስ ሚካኤል ቤትክርስቲያን እንደተጠለሉ ናቸው ብለዋል፡፡

Äthiopien | Grenzgebiete der Region West-Arsi Oromia
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

መንግስት አፋጣኝ የጸጥታ በማስከበር ዘላቂ መረጋጋት እንዲያመጣ ተጠይቋል፡፡

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚ ክልል አርሲ ዞን ግጭት በተከሰተባቸው ወረዳዎች መንግስት አፋጣኝ የጸጥታ ማስከበር እርምጃዎችን በመውሰድ ዘላቂ መረጋጋት እንዲያመጣ ተጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የተመራ የቤተክርስቲያንቱ ልዑክ ቡድን ከሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ስለመወያየታቸውም ተሰምቷል።

ባሳለፍነው እሁድ እና ሰኞ ግንቦት 23 እና 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ታጣቂዎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ ሰላማቸውን የሚያረጋግጥላቸው መፍትሄ ከመንግስት እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡

ትናንት ስለተቀበረው አስከሬን

ዛሬ በርካታ ዜጎች ከተጠለሉበት በወረዳው ከሚገኝ ኢሬቻ ቀበሌ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ተፈናቃይ እንዳሉት፤ ከትናንት በስቲያ የመንግስት ፀጥታ አካላት ወደ ስፍራው ገብተው አከባቢውን ለማረጋጋት ባደረጉት ጥረት ባለፈው ሰኞ በደረሰው ከፍተኛ የታጣቂዎች ጥቃት ተገድለው እስካሁን ያልተቀበረን አስከሬን ትናንት መቅበራቸውንም ገልጸዋል፡፡ “መከላከያ ከትናንት ወዲያ ገብቶ ትናንት የጠፋውን ልጅ ተሬ ደሴ የተባለን ወጣት አስከሬን አንስተን የክርስቲያን ወግ ነው ብለን ኢሬቻ ቅዱስ ሚካኤል ቀብረናል” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ሰኞ ቀን የተገደለውን ወጣት ለማንሳት ሳይቻል በርካታ የአከባቢው ማህበረሰብ ከደለታ ጨፋ ቀበሌ መፈናቀሉን አስረድተዋል፡፡

የአርሲ አሰኮ ተፈናቃዮች

ዘጠኝ ሲቪል ዜጎች እና ሁለት የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች በደለታ ጨፋ ቀበሌ በእሁድ እና ሰኞው ጥቃት መገደላቸውን የሚያረጋግጡት አስተያየት ሰጪው የግጭቱ ሰለባ፤ አሁን ላይ በርካታ ዜጎች በሱንቴ ቅድስት ማሪያም እና እሬቻ ቅዱስ ሚካኤል ቤትክርስቲያን እንደተጠለሉ ናቸው ብለዋል፡፡ “ያው ሰው አሰኮ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ቀበሌያት ተበትነው b,ቤተሰብም የተጠለለ አለ” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በብዛት ግን በሱንቴ እና እሬቻ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች እንደሚበዙ ገልጸዋል፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪ ተጎጂዎቹ በሁለት ቀናቱ የታጣቂዎች ጥቃት ቢያስ ከ200 በላይ አባወራዎች ሃብት ቀዬያቸው ወድሞባቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ መንግስት አከባቢው ላይ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ በማረጋጋት ውድመቶችን በመገንባት ተፈናቃዮችን በአጠረ ጊዜ ወደ ቀዬያቸው  ለመመለስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የተፈናቃዮች ቀጣይ ተስፋ እና ስጋት

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ግን ግጭቱ የፈጠረው ቁሳዊ እና የስነአእምሮ ጉዳት ከባድ በመሆኑ ይህ ቀላል እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡ “ሁሉ ነገር በወደመበት፤ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት እንዴት እንመለሳለን” ሲሉ የሚጠይቁት አስተያየት ሰጪው፤ የተጎጂውን ማህበረሰብ ተስፋ መመለስ ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በሄባን አርሲ ወረዳም ትናንት በተፈጠረው አለመረጋጋት የሰው  ሕይወት መጥፋቱ ተነግሯል፡፡
ሰኞ ለት መጠነኛ አለመረጋጋት ተፈጥሮበት በነበረው ሺርካ ወረዳ ሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ግን በዚህ ባለፉት ጥቂት ቀናት የተረጋጋ ፀጥታ መኖሩን የአከባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪው “ይህቺ ባለፉት ቀናት ደግሞ ሰላም ነው ምንም ኮሽታ የለም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ተወካዮች እና የመንግስት ውይይት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በኦርቶዶክሳውያን ወገኖች ላይ የደረሰውን ሕልፈተ ሕይወትና የቤተ ክርስቲያን መቃጠልን በማስመልከት በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና በብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የተመራ ልዑክ ከሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ትናንት ሓሙስ ባካሄዱት ውይይት፤ በአርሲ ዞን አሰኮ፣ ሺርካ እና ሆንቆሎ-ዋቤ ወረዳዎች የተፈፀሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምን እንዲያሰፍን ጥያቄ መቅረቡ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ የሚቋቋሙበት ሥራ እንዲሠራ ብሎም ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችም ለፍርድ ቀርበው
እንዲቀጡ አባቶቹ ስለመጠየቃቸው የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ባለስልጣናቱም በተፈጠረው ችግር ማዘናቸውን ገልጸው በመንግሥት በኩል  አጣሪ ቡድን ተቋቁም ወደ ስፍራው ተልኳል ካሉ በኋላ የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት መሠረት በማድረግም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸው ነው የተነገረው።

የቤተክርስቲያኗ የበላይ አባቶቹ፤ በኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሮች ጋርም ባደረጉት ዝርዝር ውይይት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያንምመልሶ ለመገንባት እና በአካባቢው ዳግመኛ መሰል ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እንደሚያከናውኑ በውይይት ተጠቅሷል ነው የተባለው።


ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW