1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግስት ከሸኔ ጋር የድርድር እቅዱና የኦሮሞ ፖለቲከኞች አስተያየት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2015

የኢትዮጵያ መንግስት ኦነግ ሸኔ ካለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰዉ ቡድን ጋር የሚያደርገውን የሰላም ድርድር ነገ በታንዛኒያ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ በዚህ ላይ ለመንግስት መግለጫ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠው የኦሮሞ ነጻነት ጦር በፊናው፤ ይህ እርምጃ ሰላም ለማውረድ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብሎታል፡፡

 Ethiopia I  “Enough With War - Let’s Celebrate Peace” in Addis Ababa
ምስል Office of Prime Minister of Ethiopia

የኢትዮጵያ መንግስት ኦነግ ሸኔ ካለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰዉ ቡድን ጋር የሚያደርገውን የሰላም ድርድር ነገ በታንዛኒያ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ በዚህ ላይ ለመንግስት መግለጫ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠው የኦሮሞ ነጻነት ጦር በፊናው፤ ይህ እርምጃ ሰላም ለማውረድ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብሎታል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ስለጉዳዩ አዎንታዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንዳረጋገጠውም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስትን ወክለው የሚደራደረው ልዑካን ቡድን ዛሬ ወደ ታንዛኒያ አምርቷል፡፡

“ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና” በሚል መሪ ሐሳብ የሰሜን ኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲቋጭ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምሥጋና እና የዕውቅና ሥነ ሥርዓት ትናንት እሁድ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሲካሄድ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ትኩረት የሳበው አንደኛው ጉዳይ፤ “ኦነግ-ሸነ” ካሉት ታጣቂ ቡድን ጋር ነገ ማክሰኞ በታንዛኒያ የሰላም ንግግር እንደሚጀመር ማብሰራቸው ነው፡፡

ዐቢይ በዚህው ንግግራቸው ድርድሩን የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ አብዝተው የሚሹት ነው ብለዋል፡፡ ህዝብም ካለበት አለመረጋጋት እፎይ እንዲል ሁሉም ወገን ውጤታማ ድርድር እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡ 

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በፊናው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ከስምምነት መደረሱን ትናንት ምሽት ባረጋገጠበት መግለጫው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ያስቀመጥነውን ቅድመ ሁኔታ መቀበሉን ጠቅሷል። ታጣቂ ቡድኑ ገለልተኛ ሦስተኛ ወገን ባለበት በድርድሩ ወቅት በዘላቂነት ግልጸኝነት እንዲኖር ተስማምተናል ያለ ሲሆን፤ መንግሥት ድርጅቱን “ሸኔ” ብሎ ከመጥራት እንዲቆጠብም ግን አሳስቧል።

የድርጅታችን መጠሪያ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው፤ ሌላ ስያሜ ስህተት ከመሆኑም በላይ ማንነታችንን እና ዓላማችንን የሚወክል አይሆንም” ካለ በኋላ መንግሥት ይህን አይነት የተሳሳተ መረጃ ከማሰራጨት ሊቆጠብ ይገባል ብሏል።ሁለቱ አካላት ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት ቀጠሮ መያዛቸው፤ “ለፍትሕ፣ እኩልነት እና የራስን እድል በራስ ለመወሰን የለውጥ ምዕራፍ ጅማሮ ነው” ብሏል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ታጣቂ ቡድኑ ሁለቱን አካላት በታንዛኒያ የሚያደራድራቸው ሦስተኛ ወገን ማንነትን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።

በኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም መንግስት ይፋ ያደረገውን የሰላም ድርድሩን ተስፍ ሰጪ ብለውታል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባለስልጣን አቶ በቴ ዑርጌሳ ከአስተያየት ሰጪዎቹ ናቸው፡፡ “እንደ ፓርቲም ሆ በግሌ በበጎ ነው ያየሁት፡፡ እንደ ፓርቲም ችግሮች በውይይት መፈታት አለባቸው የሚል የፀና አቋም ነበረን፡፡ ስለዚህ በሁለቱም ወገን ወደ ድርድር መመጣቱ የሚደገፍና ስንጣራለት የቆየንም ነው፡፡ ከስምምነት የሚደረስበትና የዘመናት የኦሮሞ ጥያቄን ለመፍታት ከቻለ መልካም ነው እንላለን” ሲሉም አስተያየታቸውን አብራርተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው፡፡ “እኛ ሰላማዊ ትግልን እንደ መፍትሄ እንደመያዛችን ከዚህም በፊት ስንወተውት የኖርነው ሁሉም ልዩነት በሰላምና በንግግር እንዲፈታ ብቻ ነው፡፡ አሁን ኦሮሚያ ሰላም የላትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ያስተላለፉት መልእክት የእውነት ከልባቸው ከሆነ፤ የሚደገፍና እኛም የምንፈልገው ነው” ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባለስልጣናቱ መንግስት የተጀመረውን የሰላም ተስፋ በቁርጠኝነት በመያዝ ከግጭት አፈታት ባሻገር በኦሮሚያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የፖለቲካ ውይይቶችንም በቀጣይ ምዕራፎች መቀጠል ይኖርበታል የሚል አስተያየታቸውን አክለው ሰጥተዋል፡፡ ነገ በታንዛኒያ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው በዚሁ ድርድር ላይ የሚሳተፉ የፌዴራል መንግስትን የሚወክሉ ልዑካን ዛሬ ወደዚያው ማቅናታቸውን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገለግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠው ሌሎች መረጃዎችን ከማብራራት ግን ተቆጥበዋል፡፡

በምዕራባዊ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ኦሮሚያ ትጥቅ አንግቦ በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚህ ቀደም ለድርድር የመቀመጥ ፍላጎት እንዳለው ገልጾ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል። ከእነዚህም መካከል ንግግሩ ከኢትዮጵያ ውጪ በሦስተኛ ወገን አሸማጋይነት ሊደረግ እንደሚገባ ማሳወቁ ነበር።

ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከታጣቂው ቡድኑ ጋር መንግሥት ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል።

 

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW