መከከለኛው ምስራቅና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያ አቅርቦት
ሰኞ፣ ሐምሌ 23 1999ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያላት ተፅዕኖ በተጠናከረበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በአአካባቢው ለሚገኙ አጋሮችዋ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የጦር መሳሪያ ለማቅረብ አቅዳለች ። በዚሁ መሰረት እስራኤል ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው የጦር መሳሪያ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚሰጣት ሲሆን ለሳውዲ አረቢያና ለሌሎች የባህረ ሰላጤው አገራት ደግሞ አማኤሪካን አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ትሸጣለች ። የጦር መሳሪያ ዕርዳታውና የሽያጩ ዓላማም ወደ ምዕራቡ የሚያዘነብል አስተሳሰብ የሚያራምዱትን አጋሮች ከኢራን ሊደርስ ከሚችል ጥቃት አንፃር ማስታጠቅ ነው ። የአሁኑ ስልት ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ ጠላቶችዋ ላይ የወሰደችውን የከዚህ ቀደሙን ዕርምጃዋን ያስታውሳል ። የዋሽንግተን አስተዳደር በፀረ ኢራኑ ትግል የሳዳም ሁሴንን መንግስት እንዲሁም በፀረ ሞስኮው ትግል ታሊባኖችን አስታጥቋል ። ፔተር ፊሊፕ እንዳተተው ዩናይትድ ስቴትስ ኢራንን እንደገና ለመጫን የቀየሰችው የአሁኑ ስልቷ ግን የሚያዋጣ መንገድ የተከተለ አይመስልም ።
ከኢራቅ ጋር በሚካሄደው ጦርነትና በዓለም ዓቀፉ የፀረ ሽብር ዘመቻ ዋሽንግተን በሳውዲ አረቢያ ሚና ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደስተኛ አይደለችም ። ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ አሁን ለሪያድ መንግስት ዋጋው ወደ ሀያ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ትፈልጋለች ። ይህ ደግሞ ከጥቂት ወራት በፊት ለሳውዲ አረቢያ ለመሸጥ ከታሰበው የጦር መሳሪያ መጠን በዕጥፍ የላቀ ነው ። ሌሎች የባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራትም አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ይታጠቃሉ ። ግብፅም እንዲሁ ወደ አስራ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ይሰጣታል ። እስራኤል ደግሞ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የሰላሳ ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ታገኛለች ። “በጦር መሳሪያ ብዛት ሰላምን ማምጣት “ የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት አዲስ ስልት አይደለም ። ይፋ የተደረገው የጦር መሳሪያ ሽያጭ በአንድ በኩል የዋሽንግተን መንግስት ያጋጠመው የፖለቲካ ሀፍረት መሸፈኛ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኢራንን ይበልጥ ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ነው ። ይህ ዕቅድም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ “እየጨመረ የመጣውን የኢራን አደገኝነት ለመከላከል የሚወሰድ ዕርምጃ ተብሎ ነው በይፋ የሚገለፀው ። በሌላ በኩል ለባህረ ሰላጤው አገራት የታቀደው የጦር መሳሪያ አቅርቦት ግን አትራፊ ንግድም ነው ለዩናይትድ ስቴትስ ። ከእስራኤልና ከግብፅ በስተቀር የተቀሩት ነዳጅ ዘይት አምራች አገራት የጦር ማሳሪያ ግዥ ነው የሚያከናውኑት ። እዚህ ላይ ምናልባት የሚያስገርመው ነገር የሳውዲ አረቢያውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እስራኤል ያለ አንዳች መጉረምረም መቀበሏ ነው ። ከአካባቢው አገራት የአሜሪካን የረዥም ጊዜ የጦር መሳሪያ ደንበኛ የሆነችው እስራኤል ምናልባትም የተጠበቀውን ወቀሳ ያላቀረበችው በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያ አቅርቦት ረክታ ይሆናል ። ወይም ደግሞ እንደ ሳውዲ አረቢያ ያሉት አገራት ለእስራኤል አስጊ አለመሆናቸውን በመገንዘቧ ብቻ ሳይሆን ሳውዲ አረቢያ እስካሁንም የገዛቻቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በአካባቢው ግጭቶች በደረሱበት ወቅት ስትጠቀም ባለመታየቷም ነው ። እንደ ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት እስራኤልም ራስዋን ለመከላከል የውጭ ኃይሎችን ማለትም የአሜሪካኖችን እገዛ ታገኛለች ። ለእስራኤል ብቸኛው አደጋ ሆኖ የሚታየው አንዳንድ የሳውዲ የጦር ኃይሎች ለምሳሌ አንድ ፓይለት በራሱ ተነሳሽነት ጥቃት ቢያደርስ ወይም ደግሞ የጦር መሳሪያዎቹ ሊደርሳቸው በማይገባ ሰዎች እጅ የሚወድቁ ከሆነ ነው ። ሁለቱ እንደምሳሌ ይቀርቡ እንጂ ሌሎች መላ ምቶችም ሊሰነዘሩ ይችላሉ ። ዩናይትድ ስቴትስ ለአረብ አገራት የጦር መሳሪያ መሸጧ እስራኤልን እንደማያሰጋት ሁሉ በኢራንም ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ። ሆኖም ግን አሜሪካ ለተግዋዳኞችዋ የጦር መሳሪያ እንደምታቀርብ ማስታወቋ በኢራን ላይ ተጨማሪ ትንኮሳ ማካሄድ መሆኑ ቴህራን ቢሰማት አግባብ ነው ።ይህ በመሆኑ ደግሞ ኢራን ህራን ተጨማሪ ዕክል ይገጥማታል ማለት አይደለም ። ለሳውዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ የታቀደበት ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ጠቀሜታ ያለው ነው ። በአንድ በኩል ኢራንን ማናደድ በሌላ በኩል ደግሞ የተግዋዳኞቹን የአረቦቹን ስሜት ለማርካት ነው ። አሜሪካን ለእስራኤል የምትሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ በሀያ አምስት በመቶ በማሳደግ አሜሪካን ለእስራኤል እንደምታደላ ያስገነዝባል ። ይሁንና የአረብ ሀገራት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማድረግ አይችሉም ።