1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

መካኖችን ልጅ ወልዶ ለመሳም የሚያበቃው ቴክኖሎጅ

ረቡዕ፣ የካቲት 12 2017

ይህ የሥነ ተዋልዶ ቴክኖሎጂ ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን ይባላል። የሚከናወነውም የሴት እንቁላልን ከሴቷ ማህፀን በማውጣት እና ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር በማድረግ ፅንስ እስኪሆን ድረስ በቤተ ሙከራ ውስጥ እንዲዳብር ይደረጋል።ከቀናት በኋላም የተፈጠረውን ፅንስ ወደ ሴቷ ማህፀን በመመለስ እርግዝና እንዲፈጠር በማድረግ የሚከናወን ነው።

Symbolbild Einfrieren von Embryonen
ምስል፦ Andrew Brookes/Image Source/IMAGO

መካኖችን ልጅ ወልዶ ለመሳም የሚያበቃው ቴክኖሎጂ

This browser does not support the audio element.


በተፈጥሮም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ልጅ ወልደው መሳም ላልታደሉ ሰዎች በሰው ሰራሽ መንገድ ልጅ እንዲያጘኙ ለማድረግ የህክምና ሳይንስ የተለያዩ  ዘዴዎችን እያቀረበ ይገኛል። ከነዚህም መካከል  ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን/in-vitro fertilization/ በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /IVF/የሚባለው የሥነተዋልዶ ቴክኖሎጅ አንዱ ነው።
ዶክተር ቶማስ መኩሪያ በመካንነት እና ሥነ ተዋልዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ናቸው።በአሁኑ ጊዜ ሩዋንዳ ኪጋሊ በሚገኘው ሚሊታሪ ሆስፒታል የማስተማሪያ ማዕከል ውስጥ በሙያቸው እየሰሩ ይገኛሉ።ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅትም አዲስ አበባ በሚገኘው የጳውሎስ  ሆስፒታል በዚሁ ህክምና የመውለድ ችግር ያገጠማቸው ጥንዶች አይናቸውን በአይናቸው እንዲያዩ አድርገዋል። 
እሳቸው እንደሚሉት ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን/IVF/ በቴክኖሎጅ የታገዘ የመካንነት የመጨረሻው ህክምና ነው።

ዶክተር ቶማስ እንደሚገልፁት መካንነት ሰፊ የጤና ችግር ሲሆን፤ ጥንዶች ያለመከላከያ ከአንድ አመት በላይ ግንኙነት አድርገው እርግዝና መፈጠር ካልቻለ።ወይም ደግሞ የሴቷ እድሜ ከ35 ዓመት በላይ ሆኖ ፤ጥንዶቹ ያለመከላከያ ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ እየተገናኙ በስድስት ወር ውስጥ እርግዝና መፈጠር ካልተቻለ መካንነት ተከስቷል ተብሎ ይታሰባል።በዚህ ጊዜ ታዲያ የተለያዩ ምርመራዎች ተደርገው ወደ ህክምና ይገባል። ከህክምናዎቹ መካከል በቴክኖሎጅ የታገዘው ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን  አንዱ እና የመጨረሻው አማራጭ ነው።በሰው ሰራሽ መንገድ ልጅ የማግኘት ዘዴ ወይም /In-vitro fertilization/ የሴት እንቁላልን እና የወንድ የዘር ፍሬን የሚያካትት የመካንነት ህክምና ነው። ሂደቱ የሴት የእንቁላል ማዳበርን ፣ መከታተልን እና ማነቃቃትን ያካትታል።
በአጠቃላይ በሰው ሰራሽ መንገድ ልጅ የማግኘት ዘዴ  ወይም ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን / Invitro Fertilization/  የሴት እንቁላልን ከሴቷ ማህፀን በማውጣት  ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር በማድረግ ፅንስ እስኪሆን ድረስ በቤተ ሙከራ ውስጥ እንዲዳብር ይደረጋል።ከቀናት በኋላም  የተፈጠረውን ፅንስ ወደ ሴቷ ማህፀን በመመለስ በእናትየው ማህፀን ውስጥ እንዲያድግ በማድረግ የሚከናወን በቴክኖሎጅ የታገዘ የሥነተዋልዶ ህክምና ነው። 

ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን/IVF/ በቴክኖሎጅ የታገዘ ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ የመካንነት ህክምና ነው።ምስል፦ Michael Hoffmann/picture alliance

ይህ ህክምና ዶክተር ቶማስ እንደሚሉት በሁለት መንገድ ሊሰራ ይችላል።የመጀመሪያው ጥንዶች በራሳቸው እንቁላል እና የወንድ የዘር ፍሬ የሚያሰሩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሌሎች ለጋሾች የሚሰጡትን እንቁላል እና የወንድ የዘር ፍሬ በመጠቀም ሊከናወን ይችላል። ለጋሾቹም የሚታወቁ ወይም የማይታወቁ ሊሆኑ  ይችላል።ይህም ዶክተር ቶማስ እንደሚሉት  ልጅ እንደሚፈልጉት ጥንዶች ችግር የሚወሰን ነው።

«አንድንዴ ከእድሜ ጋር ተያይዞ ሴት ልጅ የማረጥ ደረጃ  ልትገባ ትችላለች።እንደዚያ ሲሆን እንቁላል እንደ አዲስ የሚያድግበት ምንም መንገድ የለም።እስካሁን ሳይንሱ አልደረሰበትም።ስለዚህ እርግዝና እንዲፈጠር ከሌላ ሰው እንቁላል መወሰድ ግድ ይሆናል ማለት ነው።በወንዱ ደረጃ ብዙ ጌዜ የዘር ፍሬ የማለቅ ደረጃ አይደርስም።«አንድሮፖዝ« በሚባለው በሽታ ምክንያት ከ80 ዓመት በላይ ካልሆኑ በስቀር ብዙ ጌዜ ወንድ ልጅ  እስከመጠረሻው «ስፐርም«ይኖረዋል ተብሎ ነው የሚታሰበው።አንዳንዴ ግን በተለያዩ ችግሮች በ«ኢንፌክሽን» ሊሆን ይችላል።በሌሎች የሆርሞን ችግሮች፣በተፈጥሮ ችግሮች ሊሆን ይችላል የወንድ የዘርፍሬ ላይገኝ ይችላል።» ካሉ በኋላ፤ በዚህ ጊዜ  የወንድ የዘር ፍሬ ከሌላ ሰው ሊወሰድ እንደሚችል አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያ እስካሁን በለጋሾች ከሚሰጥ ዘር  እርግዝናን መፍጠር ያልተጀመረ ቢሆንም፤በሌሎች ሀገራት ይሰራበታል።በዚህ ጊዜ ከማንኛውም ሰው አይወሰድም።ለጋሾች በወጣትነት ዕድሜ ክልል ያሉ በተለይ ሴቷ ከ30 ዓመት በታች መሆን እና የጤና ችግር የሌላባቸው መሆን ይገባቸዋል።ለዚህም ከልገሳው በፊት ቅድመ ምርመራ እንደሚደረግ ባለሙያው ገልፀዋል።በተጨማሪም ከጥንዶቹ የቅርብ ዘመድ የተገኘ የወንድም ሆነ የሴት ዘር ለዚህ ህክምና አይውልም።

የሴት እንቁላልን እና የወንድ የዘር ፍሬን የሚያካትት የመካንነት ህክምና ነውምስል፦ Michael Wyke/AP Photo/picture alliance

እርግዝናውን በሚፈልጉ ሴቶች በኩልም ህክምናውን ከማግኘታቸው በፊት እንደ እድሜ እና ጤና ያሉ ጉዳዮች ግምት ውስጥ ይገባሉ ይላሉ ዶክተር ቶማስ።
ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን ከጎርጎሪያኑ 1978 ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለና በቴክኖሎጅ የታገዘ የመካንነት ህክምናሲሆን፤በዓለም ዙሪያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህፃናት በዚህ ቴክኖሎጅ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተወልደዋል። እንደ ዶክተር ቶማስ በኢትዮጵያም ጥቅም ላይ ውሎ ብዙ ስኬት ተገኝቶበታል።
ከዚህ አንፃር ውጤታማ የሚባል ቴክኖሎጅ ሲሆን፤በደህንነት በኩልም በተፈጥሮ መንገድ ከሚወለዱ ህፃናት የተለዬ የጤና እክል እንደማያስከትል  ባለሙያው ገልፀዋል።
በዚህ ሁኔታ  በኢትዮጵያም ይህ ህክምና በጳውሎስ ሆስፒታል እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን፤እንደ ባለሙያው ብዙ ስኬት ተገኝቶበታል።«ጳውሎስ ሆስፒታል የመጀመሪያው የህዝብ የ«አይ ቪ ኤፍ» ማዕከል የተከፈተው በጳውሎስ ሆስፒታል ነበረ።በዚያም ለአምስት ዓመት ስሰራ ነበረ።ተቋሙንም ስመራ ነበረ።በዚያ ጊዜ ውስጥ ለ7 ሺህ ጥንዶች ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን /በቴክኖሎጅ የታገዘ የመካንነት ህክምና/ሰርተን የውጤታማነት ደረጃውን ከ46 እስከ 50 ፐርሰንት አካባቢ ነው።ያደግሞ እኛ ሀገር የዘር ልገሳ አይደረግም።በራስ የሴት እንቁላል እና የወንድ የዘር ፍሬ ተጠቅመን ነው።»በማለት ገልፀዋል።

እድሜ እየጨመረ ሲሄድ እርግዝና የመሳካቱ ዕድል እየቀነሰ ስለሚሄድ በዚህ ህክምና እድሜ ወሳኝነት አለው።በሌላ በኩል ወልዶ ለማሳደግ ወይም የሚወለደው ልጅ ከወላጆቹ በቂ  እንክብካቤ እንዲያገኝ እድሚያቸው ለገፉ ሰዎች አይመከርም።

ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን የተባለውን የመካንነት ህክምና ለማግኘት እንደ እድሜ እና ጤና ያሉ ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው።ምስል፦ Kalinich24/Pond5 Images/IMAGO

በአጠቃላይ ይህ ሂደት እርግዝናን የመፈጠር ዕድልን መጨመሩ፣መካንነትን ማስቀረት መቻሉ፣የቅድመ የዘረ መል ምርመራ መኖሩ፣ የዘር ፍሬን ማቆየት መቻሉ፣ማግባት ላልቻሉ ሰዎች አማራጭ ሆኖ መቅረቡ ጠቀሜታዎቹ ናቸው።በሌላ በኩል በዋጋ ደረጃ ውድ መሆኑ፣ ሂደቱ የሚያስከትለው የሥነልቡና እና የስሜት ጫና ቀላል አለመሆኑ፣፣በአጠቃላይ ሲታይ ጤናማ ነው ቢባልም የሚያስከትለው አንዳንድ ተጓዳኝ የጤና ችግሮች፣ ለምሳሌ የሆድ ህመም እና መነፋት ምቾት ማጣት የሚያስከትለው እንደ Ovariian Hyperstimulation Syndrome /OHSS/ ያሉ በሽታዎች መከሰት፣ ከአንድ በላይ እርግዝና የመከሰት ዕድልን የሚጨምር መሆኑ እና ህክምናው ስኬታማ ካልሆነ በሰዎቹ ላይ የሚያስከትለው የስሜት መጎዳት እንደ እጥረት ይጠቀሳል።
በተጨማሪም የሥነ ተዋልዶ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም  በጥንዶች ላይ ጥያቄ ባያስነሳም፤ ከለጋሽ በሚገኝ የዘር ፍሬ የሚደረግ እርግዝና ላይ ከሞራል እና  ከሀይማኖት አንፃር   አከራካሪ ጉዳዮች መኖራቸውም በዚህ ቴክኖሎጅ የሚነሳ ሌላው  ጉዳይ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW