1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መውሊድን እና መስቀልን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር የተጒዙት ወጧቶች

ዓርብ፣ መስከረም 18 2016

ይህ ሳምንት ሁለት ትላልቅ ኃይማኖታዊ በዓላትን ያስተናገደ ነበር። በተለይ ዕሮብ ዕለት ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የነቢዩ መሐመድ ልደትን ሲያከብሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች ደግሞ ደመራ እና መስቀልን አክብረዋል።

ክትፎ እና ቁርጥ ስጋ
ክትፎ እና ቁርጥ ስጋምስል B. Haile

መውሊድን እና መስቀልን ከቤተሰብ ጋር

This browser does not support the audio element.

ሁሴን ኢብራሂም የመውሊድበዓልን ለማክበር ከሚኖርበት ሎጊያ ከተማ ወደ ጭፍራ የተጓዘው ከበዓሉ በፊት ገና እሁድ ዕለት ነበር።  ቤተሰቦቹ ጋር ለመድረስ 120 ኪ ሜትር መጓዝ እንደነበረበት የነገረን ሁሴን በዓሉ በሁሉም ሙስሊሞች ዘንድ ባይሆንም እሱ በሚኖርበት አካባቢ እንደሚከበር ገልፆልናል። «ነብዩ መሐመድ የተወለዱበት ቀን እና የሞቱበት ቀን አንድ ነው። የልጀታቸው ቀን ይከበር እንዴት ግን የሞቱበት ቀን ይከበራል የሚል ክርክር አለ። እኛ አካባቢ ግን ይከበራል። እኔም ለዛ ነው ወደእዛ የሄድኩት። ብዙ ነገር አለ። » ለዚህም ነው ሁሴን በዓል ከተከበረበት መስከረም 16 ቀደም ብሎ ለቅድመ ዝግጅቱ ወደ ቤተሰቦቹ የተጓዘው። « ብዙ ዝግጅትቶች አሉ፣ ቦታ ይስተካከላል። መስኪድ ይፀዳል። ምንጣፎች እናጥፋለን። እንግዶች ይጠራሉ።  ለእርድ የሚሆኑ እንሰሳት ይሰበሰባሉ። » በማለት ቅድመ ዝግጅቱን ገልፆልናል።

1498ኛው የመውሊድ በዓልን ለማክበር አህመድ ጀማል እንደ ሁሴን ብዙ መጓዝ አልነበረበትም። እዛው የሚኖርበት አፋር ክልል  ሎጊያ ነው ያከበረው። «አልፎ አልፎ መስኪድ ሄደው የሚያከብሩ ቢኖሩም አብዛኞቻችን በዓሉን ሰብሰብ በማለት እቤታችን ነው ያከበርነው» ይላል።  « ከግደኞቹ ጋር ሆኜ የነብዩ መሐመድን የልደት ቀን በማስመልከት አንዳንድ መንዙማዎችን በማዳመጥ ዱአ እያደረግን ነው የምናከብረው።»

በፍቅር ኃይሌምስል B. Haile

ይህ ሳምንት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች ዘንድ ደመራ እና መስቀል የተከበረበትም ነበር። መስቀል በደማቅ ሁኔታ ወደሚከበርበት የጉራጌ ማህበረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋባዥ እንግዳ ሆና እንዳከበረች የገለፀችልን እና ሌላው የዛሬ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳ በፍቅር ኃይሌ ትባላለች። በምስራቅ ጉራጌ ዞን የነበረውን የመስቀል አከባበር ወዳዋለች። « በጣም ደስ የሚል ባህል አላቸው። በጣም የወደድኩት ለምሳሌ የደመራ አበራራቸውን ነው። » የምትለው በፍቅር እሷ ከምትኖርበት ኦሮምያ ክልል በተለየ ሰዎች በጋራ አንድ ቦታ ደመራ ካበሩ በኋላ በሰፈር ሰዎች ተሰብስበው የሚያበሩትን ደመራ ወደዋለች። ሌላው ደግሞ « ሰኞ ዕለት የተከበረው የጎመን ቀን ነበር» ትላለች።

በጉራጌ ዞን ሰዎች ተሰብስበው ደመራ ሲያበሩምስል B. Haile

የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆነው ዮሴፍ ወንድሙ ለመስቀል በዓል ሁል ጊዜ ወደ ቤተሰቦቹ ጋር ይጓዛል። ዘንድሮም እንዲሁ፤ ጉዞውን የጀመረው እሁድ ዕለት ነው። « በአካባቢው ቀደም ብሎ አከባበሩ የሚጀምረው እኛ  የሄድንበት ቦታ ቡኢ ይባላል ከቡታ ጅራ 15 ኪ ሜትር ቢሆን ነው።  መስከረም 14 የሴቶች በዓል አለ የጎመን ቀን ይባላል። በ15 ደግም እርድ ነው። እሱ ደግሞ የወንዶች ቀን ይባላል። እንደዛ እያለ አከባበሩ ይቀጥላል። » 
የመስቀል በዓል በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር  የመውሊድ በዓል ግን የኢድ አል አድአ እና ኢድ አል ፈጥር በዓላትን ያህል በሁሉም ሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ በደማቅ ሁኔታ አይከርም።  በተለይ ሴቶች ደግሞ የመውሊድ በዓል እንብዛም ተካፋይ እንዳልነበሩ ነው የአፋሩ ነዋሪ አህመድ የገለፀልን። « በእኛ አካባቢ ሴቶች በዓሉን ሲያከብሩ አላየሁም። ወንዶች ናቸው። ምግብ ይሰራሉ። ቤቱ ባዶ እንዳይሆን ቤቱን ሞቅ ደመቅ እያደረጉ ይጠብቃሉ።» 

ሴቶች እና ህፃናት መውሊድን ሀረር ላይ ሲያከብሩምስል Mesay Tekelu/DW

በአፋር ክልል ለበዓሉ ግመል የሚታረድበት አጋጣሚ አለ። ይህም መስኪድ አካባቢ እንደሆነ እና አላማውም የተቸገሩ ሰዎችን ለማብላት እና ለማጠጣት እንደሆነ አህመድ ገልፆልናል። ምግቡ እንዴት ይሰጋጃል? « አብዛኛውን ጊዜ ስጋው ተቀቅሎ ወይም ተገንፍሎ ይከተፍ እና እንደ ጥብስ ሆኖ ከሩዝ ጋር ደገርጎ ይበላል።» ይህም ለተቸገሩ ሰዎች ይቀርብላቸዋል። ዋናው አላማው እና ቁም ነገሩም ይህ ነው ይላል አህመድ ።

ልደት አበበ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW