መገናኛ ብዙኃን 7ኛዉን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ እንዴት ዘገቡት?
ማክሰኞ፣ ግንቦት 25 2018
መገናኛ ብዙኃን 7ኛዉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጠቅላላ ምርጫ እንዴት ዘገቡት?
መገናኛ ብዙኃን 7ኛዉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጠቅላላ ምርጫ እንዴት ዘገቡት? ምርጫዉ ለጋዜጠኞች ምን ያህል ነጻ እና የሚዲያን ነጻነት ያከበረ ነበር። ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ማግሥት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ጋዜጠኞች በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ለዘገባ ያደረጉት እንቅስቃሴ ፈታኝ እንደነበር ተናግረዋል። ፎቶ ማንሳት ክልክል የነበረባቸዉ ፤ ፖሊስም ሆነ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት፤ „ተመለስ“ እያሉ ጋዜጠኞች እንዳይገቡ የከለከሉበት፤ የምርጫ ቦታዎች ነበሩ።
ይህ የፀጥታ ችግር አንጻራዊ ሰላም በሚታይባቸዉ አዲስ አበባ መዉጫ አካባቢ ያሉ የምርጫ ጣብያዎች እና በከፊል መሃል አዲስ አበባ ላይ በሚገኝ ምርጫ ጣብያ ላይ የታየም ነበር። ባለሥልጣናትን ለቃለ ምልልስ መጠጋት የማይቻልባቸዉ የምርጫ ጣብያዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ለደህንነታቸዉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ ጋዜጠኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ትላንት ሰኞ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘጋቢዎች በአዲስ አበባ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ፎቶግራፍ እንዳያነሱ በብልፅግና ፓርቲ ታዛቢዎች እና በምርጫ አስፈጻሚ መከልከላቸውን የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ68 መገናኛ ብዙኃን እና 1,815 ጋዜጠኞችን በመዝገብ “በምርጫ ጣቢያ 200 ሜትር ንፍቀ-ክበብ ውስጥ ገብተው መዘገብ የሚያስችላቸውን ባጅ“ እንደሰጠ አስታውቋል። ይሁንና ከድምጽ መስጫው ቀን በፊት “ጋዜጠኞች በተለያዩ አካባቢዎች ዘገባ በሚሠሩበት ወቅት በቦርዱ መዘገብ ስለመቻላቸው ደብዳቤ ሊጻፍላቸው እንደሚገባ በመግለጽ ከዘገባ ሥራ ማስቆም በውስን አካባቢ” መስተዋሉን አረጋግጦ ነበር። ክልከላውን “የተሳሳተ” በማለት ያወገዘው ምርጫ ቦርድ “በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተመዘገበ መሆን ብቻ ምርጫን ለመዘገብ” እንደሚያስችል አስታውቋል።
ምርጫው የተካሔደው የኢትዮጵያ መንግሥት በተከታታይ በወሰዳቸው እርምጃዎች በተለይ ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በኃይል በተዳከሙበት ወቅት ነው። በአማርኛ፣ እንግሊዘኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ዘገባዎች የሚያቀርበው አዲስ ስታንዳርድ ፈቃዱ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመሠረቱ ምርጫ ለመዘገብ ፍላጎት ቢኖረውም ሳይችል መቅረቱን አስታውቋል። አዲስ ስታንዳርድ ለ10 ጋዜጠኞች እና ሁለት የካሜራ ባለሙያዎች የምርጫ ዘገባ ፈቃድ እንዲሰጥ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በይፋ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃኑ ትላንት ሰኞ ገልጾ ነበር።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ባሕር ዳር የሚገኘው የዶቸ ቬለ ዘጋቢ ፈቃድ በቋሚነት በመሠረዙ ምክንያት ምርጫውን ሳይዘግብ ቀርቷል። በባሕር ዳር እና በመቐለ የሚገኙት የዶቸ ቬለ ዘጋቢዎች ፈቃድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በቋሚነት የሠረዘው ከሰባት ወራት ገደማ በፊት ነበር።
በአማርኛ፣ ትግሪኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ዘገባዎች የሚያቀርበው ቢቢሲ የጋዜጠኞቹ ፈቃድ ባለመታደሱ ምርጫውን የዘገበው በመግለጫዎች ላይ በመመሥረት እንደሆነ ዶቸ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ተቋሙ ምርጫው ከመድረሱ በፊት የዘጋቢዎቹን ፈቃድ ለማሳደስ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ተቀባይነት አላገኘም።
የዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ 7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት የኢትዮጵያ የነጻ ሚዲያምህዳር በአሳሳቢ ሁኔታ ተሸርሽሯል፤ ባለስልጣናት በጠቅላላ ምርጫዉ ላይ የሚሰሙትን ትችቶች ዝም ለማሰኘት የሚወስዱት ጭካኔ የተሞላ እርምጃን አጠናክረዋል በማለት ተችቷል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ፤ ሃይማኖት አሸናፊ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ድርጅታቸዉ ባደረገዉ ዳሰሳ፤ በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት ወዲህ የሚዲያ ነጻነት እጅግ በአሳሳቢ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።
«በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እና ጋዜጠኞች ላይ ሲያጋጥም የነበረዉ፤ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ በግዳጅ መሰወር እና ህገ-ወጥ ክትትል፤እና በገለልተኛ ሚዲያዎች ላይ የጭቆና ዘመቻ የመሳሰሉ እርምጃዎች ታይተዋል። ይህ ከኢትዮጵያ ብሎም ከዓለም አቀፍ ሕግጋቶች ጋር የሚጣረስ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የጋዜጠኞች የሞያ የሥራ ፈቃድ ያለአግባብ መነጠቅ፤ የጋዜጠኞች ያለአግባብ መታሰር፤ ከሕግ አግባብ ዉጭ በጋዜጠኞች ላይ የሚደረጉ ክትትሎች ፤ እና ጋዜጠኞችን ያላግባብ መሰወር እና ከቤተሰቦቻቸዉ እና ከጠበቆቻቸዉ ለበርካታ ቀናት የተሰወሩባቸዉን ሂደቶች ስንሰንድ ቆይተናል። ይህ በአገር ዉስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን ፈቃድ ተሰጥቷቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚሰሩ የዉጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችን፤ እና መገናኛ ብዙኃኖችን ጭምር መሆኑን እና ሲደርስባቸዉ የነበረዉን ጥሰት ዘግበናል። ስለምርጫ ስናወራ፤ ስለምርጫ ቦርድ እናነሳለን፤ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተቋቋመበት አዋጅ መሰረት ፤ አንዱ እና ትልቁ ኃላፊነት፤ ገለልተኛ የሆነ ምርጫ እንዲደረግ ማስቻል ነዉ።»
የፕሬስ ነጻነት ማሽቆልቆል የታየዉ በምርጫ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከአለፈዉ አንድ ዓመት ጀምሮ መሆኑን ዓለም አምነስቲ አስታዉቋል።
«ባለፉት ጥቂት ወራት እና ባባለፈዉ አንድ ዓመት ለማለት በሚያስችል ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ የነጻ ሚዲያ ምህዳር በጣም በሚያሳስብ ሁኔታ ተሸርሽሯል። ባለፉት ሁለት ወራት፤ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ የሃገሪቱ የደህንነት ተቋም መሪ እንዲሁም የሃገሪቱ የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካል አመራሮች ጭምር፤ ወደ መገናኛ ብዙኃን እየመጡ፤ በሞያ አግባብ በገለልተኝነት የሚሰራ፤ የጋዜጠኝነት ሥራን፤ አገራዊ አደጋ አድርጎ የመሳል ከባድ የሚባል የቅስቀሳ ስራ፤ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጭምር ሲተላለፍ ተመልክተናል። ይህ አሰራር በተለይ ዛሬ የተካሄደዉ ምርጫ ከመድረሱ ከሳምንታት በፊት ተባብሶ የታየነዉ። ጋዜጠኞች በዚህ ሁኔታ ነዉ ዛሬ የተካሄደዉን ምርጫ እየዘገቡ ያሉት። እንዲያም ሆኖ ጋዜጠኞች በምርጫዉ እለትም ሆነ ከምርጫዉ በኃላ ባቀረብዋቸዉ ዘገባዎች ምንም አይነት ማዋከብ እስር እና እንግልት እንደማያጋጥማቸዉ፤ አልያም ባልታወቀ አካል እንደማይሰወሩ ተስፋ እናደርጋለን።»
በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየደረሰ ያለዉን ጫና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቀለብስ ጥሪያችንን አቅርበናል፤ ያለዉ አምነስቲ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆኑ ሌሎች ሃገራት ፤ የመገናኛ ብዙኃኖች ብሎም የጋዜጠኞች በነጻነት የመኖር እና የመስራት ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ ፤ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ፤ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፤ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ላይ የደረሰዉን አደጋ ለመቀነስ ዝምታቸዉን እንዲሰብሩ እና ኢትዮጵያ ዉስጥ የነጻ ፕሬስ ምህዳር እንዲከበር እና የማሻሻል ስራ እንዲሰሩ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ ያቀርባል ሲሉ የድርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ ሃይማኖት አሸናፊ ተናግረዋል።
ትላንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት በነበረው የቅድመ-ምርጫው ሒደት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጠንካራ ትችት ቀርቦበታል። በአገሪቱ ውስጥ በሚካሔዱ ግጭቶች እና በቀጠናዊ ውጥረት ውስጥ የተካሔደውን የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብልፅግና ፓርቲ በከፍተኛ ውጤት እንደሚያሸንፍ ድምዳሜ ላይ የደረሱ ተንታኞች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በርካታ ናቸው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናታለም መለሰ ግን የምርጫው ዓላማ መንግሥታቸው “ለዲሞክራሲ ያለውን አገራዊ ቁርጠኝነት ማረጋገጥ” እንደሆነ ለአልጀዚራ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በጻፉት የግል አስተያየት ሞግተዋል። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “በብሔር የተከፋፈሉ መሆናቸው በምርጫው የመወዳደር አቅማቸውን እንደሚገድብ” መንግሥታቸውን በተከላከሉበት የግል አስተያየት ሚኒስትሯ አስፍረዋል። ገዢው ፓርቲ በተወሰኑ ምርጫ ክልሎች ዕጩዎች ያላቀረበው ተቃዋሚዎች በምክር ቤት መቀመጫ እንዲያገኙ በማሰብ እንደሆነም በይፋ አምነዋል።
አርታዒ፤ እሸቴ በቀለ