1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጤ ጠሉ አ.ኤፍ.ዴ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2011

ስደተኞች ጀርመን በብዛት መግባታቸውን በጽኑ የሚቃወመው አ.ኤፍ.ዴ ፣ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት ባለፈው እሁድ በዛክሰን እና በብራንድንቡርግ ፌደራዊ ክፍለ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ አሸናፊዎች ግን አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች CDU እና SPD ናቸው።ፓርቲዎቹ ቢያሸንፉም ያገኙት ድምጽ ከዛሬ 5 ዓመቱ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።

Lantagswahlen Brandenburg Andreas Kalbitz AFD Jubel
ምስል Reuters/A. Schmidt

መጤ ጠሉ«አማራጭ ለጀርመን»የገዘፈበት ምርጫ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው እሁድ በሁለት የቀድሞ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች በተካሄደው ምርጫ   «አማራጭ ለጀርመን» በጀርመንኛው ምህጻር አ ኤፍ ዴ የተባለው የጀርመን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ሁለተኛዉን ከፍተኛ ዉጤት ማግኘቱ ጀርመኖችን እያነጋገረ ነዉ።በዚህ ምርጫ አንጋፋዎቹ የጀርመን ፓርቲዎች አብላጫ ድምጽ ቢያገኙም ከቀድሞ ያነሰ ውጤት ማስመዝገባቸው የድክመታቸው ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።በጎርጎሮሳዊው 2021 በጀርመን የሚካሄደው አጠቀላይ ምርጫ መስታወት የተባለው የዚህ ምርጫ ውጤት እና ያስከተለው ስጋት የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው። በቀድሞዋ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች በጀርመንኛ አጠራራቸው በዛክሰን እና በብራንድንቡርግ ባለፈው እሁድ በተካሄደ ምርጫ «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው መጤ ጠሉ ፓርቲ ገዝፎ ወጥቷል።ፓርቲው በሁለቱም ግዛቶች ከነባሮቹ ፓርቲዎች ከጀርመኑ ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት በጀርመንኛው ምህጻር CDU እና ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲዎች በምህጻሩ SPD ቀጥሎ ያለውን ደረጃ አግኝቷል።አ.ኤፍ.ዴ በእሁዱ ምርጫ ፀረ-እስልምና አቋም ያለው ፔጊዳ የተባለው ንቅናቄ በተወለደበት በዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት 27.5 በመቶ፣የጀርመንን ርዕሰ ከተማ በርሊንን በከበበው በብራንድንቡርግ ክፍለ ግዛት ደግሞ 23.5 በመቶ ድምጽ አሸንፏል።ፓርቲው 2.5 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት በዛክሰን ያገኘው ድምጽ በተቋቋመ በዓመቱ በበጎርጎሮሳዊው 2014 በተካሄደው ምርጫ ካገኘው 9.7 በመቶ ድምጽ ጋር ሲነጻጸር በ17.8  ጭማሪ አሳይቷል።ይህም ወደ ሥስት እጥፍ ሊጠጋ ጥቂት የቀረው ነው።ፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ በሚያዋስኑት 4.1 ሚሊዮን ህብዝ ያለው የብራንድንቡርጉ ምርጫ ውጤት  ደግሞ በ11.9 በመቶ አድጓል።እዚህ ያሸነፈው ድምጽ በእጥፍ ብልጫ አለው ውጤቱ የፓርቲውን አመራሮች አስፈንጥዟል።በዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ዋነኛው የAFD እጩ ዮርግ ኡርባን ውጤቱን አወድሰው ፓርቲያቸው ከተለያዩ ወገኖች ተቃውሞ ባይገጥመው ኖሮ ከዚህም በላይ የሆነ ውጤት ሊያመጣ ይችል ነበር ዓይነት አስተያየት ሰጥተዋል።

ምስል Imago Images/Future Image/M. Wehnert

«በዛክሰን ያገኘነው፣በክፍለ ግዛት እና ከዚህ ቀደም በአውሮጳ ደረጃም ጭምር በተካሄደ ምርጫ ከተገኘው፣ ምርጥ የሚባል ውጤት ነው።ከፍተኛ ተቃውሞ እያለ ነው ለዚህ ውጤት የበቃነው።ይህም ከሌሎች ፓርቲዎች ብቻ አይደለም።ከአጠቃላዩ መገናኛ ብዙሀን፣ ከማህበራት፣ከተዋንያን፣ከዐብያተ ክርስቲያን እና ከሌሎችም ጭምር እንጂ።ለዚህም ነው ከዚህም በላይ ጠንካራ ልንሆን ያልቻልነው።ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር ሲነጻጸር ተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ አይደለንም።በጣም ፍትሀዊነት የጎደለው የምርጫ ዘመቻ ማካሄድ ነበረብን።»

ከሦስት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ከዚህም የተሻለ ውጤት ሊመጣ የመቻሉ እድል አለው የተባለው«አማራጭ ለጀርመን»ከሚተችባቸው ጉዳዮች መካከል ሃላፊነትን መውሰድ አለመፈለግ ይገኝበታል።ከፓርቲው አመራሮች አንዱ አሌክዛንደር ጋውላንድ ፓርቲያቸው ወደፊት ከተቃዋሚነት ወደ መንግሥት አካልነት ሲሸጋገር ሃላፊነት መውሰዱ እንደማይቀር አስረድተዋል።

«የሚጀምረው በተቃውሞ ነው። አሁን ተጨባጭ ነገር ማቅረብ መቻል አለብን ይህ ፍጹም ግልጽ ነው።ወደፊት ሃላፊነት መውሰድ ይኖርብናል።ሆኖም ሁሉም የሚጀመረው በተቃውሞ ነው።ከዚህ ቀደም ተመርጠናል።አሁንም እየተመረጥን ነው፤ምክንያቱም ሌሎቹ አስፈላጊዎቹ ጉዳዮች ላይ ምንም እንዳልተሳካላቸው አውቃለሁ።የስደተኞች ጉዳይ ፖሊሲ አለ፣ዩሮን የሚያድን ፖሊሲ አለ።ብዙ ህዝቦች በፖለቲካው ተወክለናል የሚል ስሜት የላቸውም እናም እኛን ይመርጡናል።ይህ ግን ለእኛ አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ አይደለም።»     

ምስል Reuters/H. Hanschke

ብሔረተኛም የሚባለው አ.ኤፍ.ዴ በነዚህ ሁለት ግዛቶች ያገኘው ድምጽ በጎርጎሮሳዊው 2017 በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ካገኘው ውጤት ጋር የሚመሳሰል ነው።አ.ኤፍ.ዴ በተመሰረተ በ4 ዓመቱ ነበር  በፌደራል ጀርመን ምክር ቤት 94 መቀመጫዎችን በማሸነፍ በምክር ቤቱ ሦስተኛው ትልቅ እና ተቃዋሚ ፓርቲ ለመሆን የበቃው።በወቅቱም ፓርቲው ከ16ቱ የጀርመን ግዛቶች በ14ቱ ምክር ቤቶች መቀመጫዎችን ይዞ ነበር። ስደተኞች ጀርመን በብዛት መግባታቸውን በጽኑ የሚቃወመው አ.ኤፍ.ዴ ፣ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት ባለፈው እሁድ በዛክሰን እና በብራንድንቡርግ ፌደራዊ ክፍለ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ አሸናፊዎች ግን አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች CDU እና SPD ናቸው።ፓርቲዎቹ ቢያሸንፉም ያገኙት ድምጽ ከዛሬ 5 ዓመቱ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።SPD በብራንድቡርግ 26.8 በመቶ ድምጽ አግኝቶ ቢያሸንፍም በ2014 በተካሄደው ምርጫ ካገኙኘው ውጤት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው በ5.1 በመቶ ያነሰ ነው።CDUም በዛክሰኑ ምርጫ ያገኘው 33.1 በመቶ ድምጽ ሲሆን ይህም ካለፈው በ6.3 በመቶ ዝቅ ብሏል። በዛክሰኑ ግዛት ያሸነፈው CDU ሁለተኛ ደረጃ ካገኘው ከAFD ጋር መንግሥት የመመሥረት እቅድ እንደሌለው አስታውቀዋል።  

«ድምጻቸውን ለኛም ሰጡ አልሰጡ የምንታገለው ለሁሉም ድምጽ ሰጭዎች ነው፤ ከዚሁ ጋር ግን ለAFD ግልጽ መስመር አስምረናል።ይህም ከAFD ጋር ምንም ዓይነት ተጣማሪ መንግሥት እንደማይኖረን የተላለፈው ውሳኔ አሁንም እንደሚሰራ ግልጽ ያደርገዋል።»

በብርንድንቡርግ ያሸነፈው የSPDም አቋም ተመሳሳይ ነው።በሁለቱ ግዛቶች በተካሄደው ምርጫ ውጤት ላይ ህዝቡም የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥቷል።ድጋፍ፣ስጋት እና ተቃውሞአቸውን ከገለጹት መካከል እኚህ በዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር የምትገኘው የድሬዝደን ነዋሪ በውጤቱ ደስተኛ ነኝ ይላሉ።

«በምርጫው ውጤት በጣም ደስተኛ ነኝ።AFD በርካታ አዳዲስ መራጮችን በማግኘቱ ተነቃቅቼያለሁ።CDU ከዚህ ውጤት በኋላ ምን እንደሚያደርግ በመጪዎቹ 5 ዓመታት የምናየው ይሆናል።»

ምስል picture-alliance/dpa/G. Fischer

እኚህ አስተያየት ሰጭ ደግሞ አዝነዋል።ለፓርቲው ድምጽ የሚሰጠው ሰው ቁጥር እየጨመረ የመሄዱ ምክንያትም አይገባቸውም።

«እንዴት በዚህ ደስተኛ ልሆን እችላለሁ?AFD ይህን ያህል ድምጽ በማግኘቱ በጣም አዝኛለሁ።ይህን በቀላሉ መረዳት ያዳግተኛል።ፓርቲው የጠራ አቋም የሌለውና ሃላፊነት ለመሸከም የማይፈልግ ፓርቲ ነው።እንደዚህ ዓይነት ፓርቲ እንዴት ያን ያህል ብዙ ድምጽ እንዳገኘ ሊገባኝ አይችልም።»

እኚህ ደግሞ ውጤቱ ሌላ ቢሆን ነበር የሚመኙት።

«የተለየ ውጤት ቢገኝ እመኝ ነበር።አ.ኤፍ.ዴ ሁለተኛው ጠንካራ ፓርቲ መሆኑ ጥሩ አይደለም።»

ደስተኛም ደስተኛም አይደለሁም ያሉ አስተያየት ሰጭም አሉ።

«AFD ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ባለመውጣቱ(ባለማሸነፉ) ደስተኛ ነኝ ።ሆኖም ሰዎች  በተለይ ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር የተያያዙ እና ሌሎችንም ጉዳዮች በተመለከተ ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሳይረዱ በመቅረታቸው በጣም ደስተኛ አይደለሁም።ሰዎች አ.ኤፍ.ዴ ለምን ድጋፍ እንደሚያገኝ ሳይገባቸው ሲቀር እናደዳለሁ።ይህን ዝም ብለው ነው የሚያልፉት።አሁን ተጎድተን አልፈናል እላለሁ።ይህ ጥሩ አይደለም።ግን ከዚህም የባሰ ይሆን ነበር።»

አ.አር.ዴ የተባለው የጀርመን ዜና ማሰራጫ ባሰባሰበው የህዝብ አሰተያየት አብዛኛዎቹ መራጮች ከምዕራብ ጀርመን ነዋሪዎች ጋር ራሳቸውን ሲያነጻጽሩ ሁለተኛ ዜጋ የሆኑ ያህል ነው የሚሰማቸው።ይህም የዛሬ 6 ዓመት ለተመሰረተው አማራጭ ለጀርመን ድምጽ የመስጠታቸው አንዱ ምክንያት ተብሏል።በርካታ ስደተኞች አውሮጳ ከገቡበት ከጎርጎሮሳዊው 2015 ወዲህ ቀኝ ጽንፈኛ አቋም ካለው የፔጊዳ እንቅስቃሴ ጋር ለመሥራት በሩን ክፍት ያደረገው አማራጭ ለጀርመን ስለ ስደተኞች የሚሰጠው አስተያየት ሁሌም እንዳወዛገበ ነው።ከፓርቲዎች አመራሮች አንዱ የሆኑት አሌክዛንደር ጋውላንድ ወላጆቹ ከጋናዊ እና ከጀርመናዊ የሆኑት እውቁ የጀርመን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ጀሮም ቧቴንግ ጎረቤቴ እንዲሆን አልፈልግም ማለታቸው ሲያወዛግብ ከርሟል።ፓርቲው በ2015 የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች ጀርመን እንዲገቡ መፍቀዳቸውን አጥብቆ ሲቃወምም ነበር።በዚህ የተነሳም አማራጭ ለጀርመን መጤ ጠል የሚል ስም አትርፏል።የፓርቲው ሊቀ መንበር ዮርግ ሞይተን ግን አቋማችን ተዛብቶ እየቀረበ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

ምስል Reuters/W. Rattay

«ባህላችንን፣የእሴታችንን ስርዓት፣ሕጋዊ ስርዓታችንን የሚቀበሉ፣ከኛ ጋር በሰላም የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው እዚህ የሚገኙ ጀርመናዊ ዜግነት ያገኙ ፣የውጭ ዝርያ ያላቸው ጀርመናውያን ጥያቄ የማይነሳባቸው ጀርመኖች ናቸው።ይህን በሌላ መንገድ ይተረጉማሉ ተብለን ስንወቀስ ነበር።ምክንያቱ ግን ይህ አይደለም።ይህ ደግሞ እዚህ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።እኛ በጣም ግልጽ በሆነ ሁኔታ ወደ እና ሃገር የሚደረግ ሕገ ወጥ ስደትን እና ይህም የሚካሄድበትን መንገድ ብቻ  እንቃወማለን።ይህ ደግሞ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ከሚካሄደው ስደት የመጣ አይደለም።እናም እንደዚህ ልንቀጥል አንችልም።ስለዚህ ይህን መሰሉን ሕገ ወጥ ስደት መቶ በመቶ ማስቆም እንፈልጋለን።ይህ ተግባራዊ እንዲሆን እንጥራለን።»

«የአማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ ሊቀ መንበር ይህን ቢሉም ፣ፓርቲው በምርጫ ሰዓት የሚቀሰቅስበት መንገድ የሚያነሳቸው ጉዳዮች እና ሌሎች የፓርቲው አባላት የሚሰጧቸው መግለጫዎች ግን ከርሳቸው ማብራሪያ ጋር የሚጣጣም አይደለም። የዛክሰን እና የብራንድንቡርግ ክፍለ ግዛቶች ምርጫ ውጤት አንጌላ ሜርክል ለሚመሬት ተጣማሪ መንግሥትም አስጊ መሆኑ ይነገራል።በዛሬ 3 ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ላይም ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም እየተባለ ነው።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW