1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፈተና ውስጥ የቀጠለው የመጫና ቱለማ የልማትና መረዳጃ ማሕበር

ሐሙስ፣ ሐምሌ 11 2016

ከተመሠረተ ዓመታትን ያስቆጠረው የመጫና ቱለማ የልማትና መረዳጃ ማሕበር 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባለፈው እሑድ አዲስ አበባ ላይ አከበረ። ማሕበሩ በዚህ የ60 ዓመት ጉዞው ተከፍቶ ሠራውን ከሠራበት ይልቅ ግን ተዘግቶ ያሳለፈበት ጊዜ እንደሚበልጥ ይነገራል።

ቢሾፍቱ
በ2011 ዓ.ም. ዳግም ተከፍቶ ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት እየተንቀሳቀሰ ያለው የመጫና ቱለማ ማሕበር አሁንም ድረስ ከተጽእኖ ነጻ ሆኖ ለመሥራት ፈታኝ ሁኔታዎች መኖራቸውን ይገልጻል። ፎቶ ከማኅደር፤ ቢሾፍቱ ምስል Seyoum Getu/DW

የመጫና ቱለማ የልማትና መረዳጃ ማሕበር

This browser does not support the audio element.

የማሕበሩ አመሠራረትና የፈተናው ጅማሮ

አቶ ድሪቢ ደምሴ የመጫና ቱለማ ልማትና መረዳጃ ማሕበር ፕሬዝዳንት ናቸው። መረዳጃ ማሕበሩ በ1956 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን በዚህ ሳምንት የ60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል። የማሕበሩ ዓላማም የኦሮሞ የማንነት (ባህልና ቋንቋን) የማነቃቃት ብሎም አጠቃላይ ማኅበራዊ ንቃተ ሕሊና ለመፍጠር እንደሆነ ይነገራል። ማሕበሩን በወቅቱ የልማትና መረዳጃ ማሕበር ብለው ሲመሰርቱ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ መንገድ እንዲዘረጋና ጤና እንዲጠበቅ የሚሉ ጉልህ ዓላማዎችን ይዘው እንደነበርም ተገልጿል።  ማሕበሩ በ1956 ዓ.ም. ተመስርቶ በዚህ ሳምንት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ያክብር እንጂ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በመዘጋት መሆኑን የማሕበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ድሪቢ ያስረዳሉ።

የማሕበሩ ዳግም መከፈትና ያልተቋረጠ ፈተናው

ይሁንና ማሕበሩ ከተመሠረተ አንስቶ በሦስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ የአሁኑ ኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች በማስከፈት ትውልድ እንዲማር ጉልህ አበርክቶ ማድረጉ ነው የተነገረው። በ1959 ዓ.ም. የተዘጋው ማሕበሩ ኢህአዴግ መንግሥታዊ ሥልጣን በተቆናጠጠ በሁለት ዓመት ውስጥ በ1985 ዓ.ም. ዳግም በቀድሞ አመራሮቹና አዳዲስ አባላት ቢከፈትም በ1996 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እንዲወሰድ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራቱ እንደገና ንብረቶቹ ተወርሰው ተዘጋ። በዚህን ወቅት ከ60 በላይ የማሕበሩ አመራሮችና አባላት ለእስር ተዳርገው 36 ያህል ሰዎች ተገድለው በርካታ ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ተባረሩ።  

ከዚያም ለሦስት ዓመታት ገደማ ተዘግቶ የቆየው ማሕበር በ1999 መጨረሻ ሰኔ ወር ላይ ዳግም ቢከፈትም የኢትዮጵያ አንድነት ስጋት ተደርጎ በመታየቱ በ2004 ዓ.ም. ከመንግሥት በተጻፈ ደብዳቤ አሁንም እንደገና እንዲዘጋ ተወሰነ። እንደገና በ2011 ዓ.ም. ተከፍቶ እስካሁን በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

ማሕበሩ ያስገኘው ጭብጥ ውጤት

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቢራቱ ቀነኢ ምንም እንኳ ሲከፈት ሲዘጋ ዓመታትን ቢፈጅም ማሕበሩ በሕዝቡ ውስጥ ንቃተ ሕሊናን እና ኅብረትን በመፍጠር ጉልህ አሻራ ማኖሩን ያወሳሉ። «ሕዝቡን በማንቃት ማንነቱን እንዲያቅና ለዚያም እንዲታገል ያደረገው ይህ መጫና ቱለማ ማሕበር ነው።» የሚሉት ዶክተር ቢራቱ፤ «ምንም እንኳን መንግስት ማሕበሩን ቢዘጋም አባላቱ ባገኙት ግንዛቤ መላው የኦሮሞሕዝብ ኅብረት እንዲፈጥሩና የሚደርስባቸውን የማንነት ጭቆና እንዲታገሉት አድርጓል።» ባይ ናቸው። አያይዘውም። «የማሕበሩ መዘጋትም በማህበሩ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ፊታቸውን ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄ አዙረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን መስርተው እንዲታገሉ አደረጋቸው» ብለዋል።

ከጅማ ወደ ጂንካ የሚወስደው ጎዳና ፎቶ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

አሁንም ያልተቋረጠው የማሕበሩ የተገደበ ነጻነት

በከፍተኛ ውጣ ውረድ እዚህ የደረሰው የመጫና ቱለማ ማሕበር አሁን አሁን እየተዳከመ ይገኛል የሚሉት ዶ/ር ቢራቱ ከ2011 ዓ.ም. ዳግም ተከፍቶ ሕጋዊ ሰውነት ቢኖሩውም አሁንም ከተጽእኖ ነጻ አለመሆኑን በግልጽ ይናገራሉ። የችግሩ መንስኤዎችም ውስጣዊና ውጫዊ ነው ይላሉ። እንደ እሳቸው ከሆነ «ማሕበሩን በፖለቲካ ዐይን የማየቱ ጉዳይ አሁንም አልተቀረፈም።»

የማሕበሩ ፕሬዝዳት አቶ ድሪቢ ደምሴም ያሉትን አሁናዊ ተጽእኖዎች ሲያስረዱ፤ «በርግጥ አልዘጉንም እንጂ ዛሬም ማሕበሩ ከተጽእኖ ነጻ አይደለም። ይህን የምለው እንዲሁ አይደለም። ከዚህ በፊት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መጫና ቱለማ ማሕበርን እንዘክር ብለን ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ 14 ዩኒቨርሲቲዎች በሚታደሙበት ኮንፈረንስ ለማካሄድ ዝግጅት ጨርሰን ልክ ዩኒቨርሲቲው ልንገባ ስንል ወታደር ደርሶ በተነን። በጉደር የማሞ መዘምርን ሃውልት ለማቆም የአካባቢው ማኅበረሰብ የመሠረት ድንጋይ እንድናቆምላቸው ጠርተውንም ከልክለውናል። ወደ ክፍላተ ሀገር የመንቀሳቀስ ነጻነት የለንም ስጋት አለን።» ይላሉ።  

ማኅበሩ አሁን በ2011 ዓ.ም. ከተከፈተ ወዲህም የተፈናቀሉ ዜጎችን በተለያዩ ቁሳቁሶች ከመደገፍ ጀምሮ በርካታ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣም ተገልጿል።    

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW