“መፈንቅለ-መንግሥት” ወይስ “ሕግ ማስከበር” የትግራይ ቅርቃር
ሰኞ፣ መጋቢት 8 2017
የትግራይ የፖለቲካ ልሒቃን መቃቃር እንደ አብዛኛው የክልሉ ነዋሪዎች ለመምህርት ንግሥቲ ጋረድ ሥጋት ፈጥሯል። “የመሪዎቻችን ልዩነት ለሕብረተሰቡ ከፍተኛ ችግር ይዞ እንደመጣ ሁሉም ያውቀዋል” የሚሉት መምህርት ንግሥቲ “መሪዎቻችን በሁለት ተከፍለው፤ ሕብረተቡንም ለሁለት ከፍለው፤ በችግር ላይ ችግር ፈጥረው ሕብረተሰቡ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሔድ አድርገውታል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የክልሉ ነዋሪ “ነገስ ምን ይፈጠራል?” በሚል ሥጋት ውስጥ “እየተሳቀቀ እንዲኖር” መገደዱን የገለጹት የመቐለ ነዋሪ የተከሰተው ውጥረት ለኑሮ ውድነት ገፊ ምክንያት ለመሆን መብቃቱን ታዝበዋል። ንግሥቲ እንደሚሉት “የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ፤ የትግራይ ሕዝብ በማይቋቋመው ሁኔታ ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቋል።”
ጦርነት ቢቀሰቀስ ሸቀጥ ወደ ትግራይ ላይገባ ይችላል በሚል ስሌት ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን የተናገሩት መምህርት ንግሥቲ “ሕዝቡ በከፍተኛ ችግር ላይ እንዳለ ግልጽ ነው” ሲሉ የገበያውን ሁኔታ አስረድተዋል። ሌላው የመቐለ ነዋሪ ዘርዓይ ገብረሕይወት “ሸቀጣ ሸቀጥ በሙሉ ተወዷል። ዘይት፣ የመኪና ነዳጅ የለም። ወደ የግል ሱቅ ገብቷል ማለት ይቻላል” በማለት ወቅታዊው ሁኔታ በግብይት ላይ አሉታዊ ጫና እንዳስከተለ ይናገራል።
“ይኸ ነገር የመጣው ፖለቲከኞች ባደረጉት የሥልጣን ሽሚያ ይመስላል” የሚለው ዘርዓይ ሕዝቡን ለመረበሽ መዳረጉን አስረድቷል።
ትግራይ እንደ መምህርት ንግሥቲ ያሉ ዜጎችን “ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችል ይሆን?” የሚያሰኝ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቀችው ከቀደመው በቅጡ ሳታገግም ነው። ከ2013 እስከ 2015 በተካሔደው ጦርነት ቢያንስ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ሆነው ተፋላሚዎቹን ያሸማገሉት የናይጄሪያው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እንዳሉት 600,000 ሰዎች ተገድለዋል። በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተገደው ተደፍረዋል፤ በሚሊዮኖች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ትግራይ ገና አላገገመችም
ትግራይ ከሐዘን፣ ከስነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሳታገግም የሚቀሰቀስ ጦርነት ለክፍሎም አብርሐ ጭምር ሥጋት ነው። “ጦርነት ይከሰታል ብሎ ሰዉ በጣም ተረባብሿል” የሚለው ክፍሎም ጉዳዩ በኅብረተሰቡ ዘንድ “መከፋፈል” እንደፈጠረ ታዝቧል። “ሰዉ ሥራ እየሠራ አይደለም። ባንክ ወረፋ ይዞ እየዋለ ነው። ኑሮም በጣም ጨምሯል” የሚለው የመቐለ ነዋሪ “እርስ በራስ ተጋጭተው ጦርነት ሊያስነሱብን ይችላሉ” የሚል ሥጋት እንዳለ አስረድቷል።
“የቃላት ጦርነት ሳይኖር [ልዩነቶቻቸውን] ቢፈቱ ደስ ይለን ነበር” የሚለው ክፍሎም “ሁሉም ነገራቸው ወደ ጦርነት የሚያመራ” በመምሰሉ ምክንያት “ሰዉ በጣም ተረብሾ ” እንደሚገኝ ይገልጻል።
የተከፋፈሉት የህወሓት አመራሮች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ፌድራል መንግሥት ሥር ለሰደደ ልዩነታቸው መፍትሔ ካላበጁ መምህርት ንግሥቲ፣ ክፍሎም እና ዘርዓይ የፈሩት ጦርነት ዳግም ላለመቀስቀሱ ማረጋገጫ የለም።
ለወራት ሲንከባለል በቆየው የፖለቲካ ቀውስ ከተመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱን የደፈነው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና አስተዳደሩ እንዲቋቋም መነሾ የሆነው ግጭት የማቆም ሥምምነት ጭምር አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በጥቅምት 2015 በተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት መሠረት የተቋቋመ ነው።
ሥምምነቱ በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል መካከል ብቸኛ የመደበኛ ግንኙነት መስመር ሆኖ ዘልቋል። ተኩስ ያቆመው ሥምምነት በፖለቲካዊ ውይይት ወደ ሰላም ሥምምነት መሸጋገር የነበረበት ቢሆንም እስካሁን አልተሳካም። በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሥምምነቱ ፈራሚ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ 51 በመቶ ድርሻ አለው። አቶ ጌታቸው ረዳ ከመጋቢት 2015 ጀምሮ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በፕሬዝደንትነት ሲመሩ የቆዩትም በዚሁ የፓርቲ ወክልና ነበር።
ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህወሓት ክንፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ባይሰጠውም በነሐሴ 2016 ካካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ከፌድራል መንግሥት ጋር በመነጋገር አቶ ጌታቸው ረዳን ከሥልጣን ለማንሳት ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። በርግጥ በዶክተር ደብረጽዮን ለሚመራው ህወሓት አቶ ጌታቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “የቀድሞው ፕሬዝዳንት” ናቸው።
የህወሓት የውስጥ ሽኩቻ ለወራት ሲብላላ የቆየ ቢሆንም አቶ ጌታቸው ረዳ ሦስት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ካገዱ በኋላ ተባብሷል። ርምጃውን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር የሚገኘው የትግራይ ሰላም እና ጸጥታ ሴክሬታሪያት እና በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት ተቃውመዋል።
የህወሓትን ጽህፈት ቤት የተቆጣጠረው የፓርቲው ክንፍ ዓዲግራት እና ዓዲጉደምን በመሳሰሉ አካባቢዎች በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙ ባለሥልጣናትን የቀየረበት ርምጃ ውዝግቡን ያካረረ ነው። ለወራት ተዘግቶ የቆየውን የመቐለ ከንቲባ ጽህፈት ቤት በአንደኛው የህወሓት ክንፍ ይሁንታ የተሰጣቸው ዶክተር ረዳኢ በርኸ ተረክበዋል።
አቶ ጌታቸው ግን “ማኅተም መንጠቅ” እና “ቢሮዎች ሰብሮ መግባት” ሲሉ የገለጹትን እርምጃ “ሕገ-ወጥ” ሲሉ ኮንነዋል። በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “ትግራይን ወደ ሌላ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የሚከት መሆኑ በተግባር እየታየ ነው” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸው ነበር።
አቶ ጌታቸው “ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥረት” ግጭት የማቆም ሥምምነቱን “ከማፍረስ በላይ በዐይናችን የሚታይ ያፈጠጠ የጦርነት ዕድል የፈጠረበት ሁኔታ ስላለ ይኸ በፍጥነት መገታት አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት የህወሓት ክንፍ “የተወሰኑ ወታደራዊ መኮንኖችን በመያዝ” የወሰደው እርምጃ ለአቶ ጌታቸው “መፈንቅለ-መንግሥት” ነው። የፌድራል መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ባለው ድርሻ ምክንያት “አስፈላጊ ድጋፍ” ማድረግ እንዳለበትም ያምናሉ።
“የፌድራል መንግሥት በሙሉ ኃይል መጥቶ እንዲዋጋ እየጋበዝኩ አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ “ያ እንዲፈጠር አንፈልግም” ሲሉ አስረድተዋል። ይሁንና ፌድራል መንግሥት “ትግራይ ወደ ጦርነት ተመልሳ አለመግባቷን ለማረጋገጥ ባለው አቅም የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ መመልከት” ይፈልጋሉ።
በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ግን “ትግራይ ውስጥ በጸጥታ ኃይሉ የተጀመረው ሕገ-መንግሥትን እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ” እንደሆነ አስታውቋል። ፓርቲው ባለፈው መጋቢት 3 ቀን 2017 ባወጣው መግለጫ እርምጃው “የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የሚያከብር እንጂ የሚያፈርስ እንዳልሆነ” ገልጿል።
የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ፍስሃ ሃፍተፅዮን “በተወሰኑ የትግራይ አካባቢያዊ መንግሥታት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተወሰነ ጥረት” መደረጉን በመቐለ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። እርምጃው “በትግራይ ከሚገኙ በርካታ አካባቢያዊ አስተዳደሮች በጥቂቶቹ” መከናወኑን አብራርተዋል።
ዶክተር ፍስሃ “በትግራይ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር እየተፈጠረ እንደሆነ በተለይም ግጭት የማቆም ሥምምነቱ ላይ አደጋ እንደተጋረጠ እና ሥምምነቱን ለመታደግ ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ለማሳመን በተሳሳተ መንገድ በተቻለ መጠን ለከፍተኛ ታዛቢ ለማቅረብ ተሞክሯል” ሲሉ ተደምጠዋል። “ይህ ከመጠን በላይ ማጋነን ነው” ሲሉም አጣጥለዋል።
ጌታቸውም ሆኑ የደብረጽዮን ገብረሚካኤል ህወሓት በትግራይ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመፍታት ከፌድራል መንግሥት ጋር ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል። እስካሁን ውይይቶች መደረጋቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢኖሩም በተጨባጭ የተላለፈ ውሳኔ የለም።
ባለፈው አርብ በመቐለ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት በፌድራል መንግሥት እንደሚሾም አስታውሰው “ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ወደ ግጭት የሚያስገባ ነገር የለም” የሚል ማስተማመኛ ሰጥተዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩን በምክትል ፕሬዝደንትነት የሚመሩት ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ “የፌድራል መንግሥት ይህን ችግር ለመፍታት በኃይል የሚገባበት፣ የኃይል መፍትሔ የሚከተልበት ዓይነት ነገርም አይኖርም። ይህን ምክንያት ያደረገ ከውጭ የሚመጣ ግጭት አይኖርም። ከውስጣችንም አይኖርም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ችግሩ መፈታት አለበት” ያሉት ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ መፍትሔው “ፖለቲካዊ” እንደሆነ ጠቁመዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የውጪ ዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ከአቶ ጌታቸው ጋር በሰጡት ማብራሪያ “ያለ ኃፍረት እና በግልጽ ኃይል በመጠቀም ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማፍረስ እየሞከሩ ነው” ሲሉ በደብረጽዮን የሚመራውን የህወሓት ቡድን ከሰዋል። “የተፈናቃዮችን መመለስ ለወራት አዘግይተዋል” ያሉት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ “በግልጽ ጠብ ቀስቃሽ ፕሮፖጋንዳ እና ንግግር ተጠምደው፤ ብጥብጥ እና ወደ ግጭት መመለስን እየቀሰቀሱ ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ከረዥም ጊዜ በፊት መጠናቀቅ” ነበረበት ያሉትን የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ሒደት በማዘግየትም ወንጅለዋል። “በአንዳንድ ቴክኒካዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ተቋርጦ” ነበር የተባለው ይህ ሒደት ዳግም ሊጀመር ዝግጅት እየተደረገ የነበረ ቢሆንም በህወሓት አመራሮች መካከል ውጥረት ሲባባስ ዳግም ተስተጓጉሏል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ካቀረቧቸው ክሶች መካከል “የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነ የውጪ ኃይል ጋር ግንኙነት እያደረጉ እና እየተባበሩ ይገኛሉ” የሚለው ይገኝበታል። ጌዲዮን “የኢትዮጵያ ጠላት” ያሉትን “የውጪ ኃይል” በስም ባይጠቅሱም አቶ ጌታቸው ግን ደጋግመው ያነሱት ኤርትራን ነበር። “ትግራይ ውስጥ ከሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ ብዙ ወገኖች” መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው “የኤርትራ መንግሥት አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኤርትራ ግን በሁለቱ የህወሓት አንጃዎች መካከል የተፈጠረውን “የውስጥ ሽኩቻ የማባባስ ፍላጎት” እንደሌላት በማስታወቂያ ሚኒስትሯ የማነ ገብረመስቀል በኩል አስታውቃለች። የማነ በኤክስ በኩል ባሰፈሩት መልዕክት ሀገራቸው በደቡብ አፍሪካ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ሥምምነት “የማፍረስ ምንም ዐይነት ፍላጎት እንደሌላት” ገልጸዋል።
ጉዳዩን የሚያወሳስበው ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወደ ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ሥጋት ባረበበት ወቅት የተነሳ በመሆኑ ነው። ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ግን “ከሻዕቢያ ጋር በይፋ የተደረገ ግንኙነት የለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው በቀጥታ ጌዲዮን በገደምዳሜ ያቀረቡትን ክስ አስተባብለዋል።
“ከሻዕቢያ ጋር ለምን ዓላማ ነው ግንኙነት የምናደርገው?” ሲሉ የጠየቁት የትግራይ ኃይሎች አዛዥ “ከሻዕቢያ ጋር ሆነን ፌድራል መንግሥቱን ለማዛባት ነው? ወይስ በፌድራል መንግሥቱ ላይ ተስፋ ቆርጠን ከሻዕቢያ ጋር ለማበር ነው?” ሲሉ ተደምጠዋል። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ውጥረት እንዳለ አስታውሰው “በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከዚህኛው ወይ ከሌላኛው ጋር እወግናለሁ ማለት አይቻልም። የትግራይ ህዝብ ከባድ ጦርነት አልፏል። አዲስ ቁስል አዲስ ጠባሳ ነው ያለበት” ሲሉ አስረድተዋል።
ጄኔራል ታደሰ የጠቀሱት የትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰ በደል በእርግጥ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥትም ይሁን ሁለቱ የህወሓት አንጃዎች የሚክዱት አይደለም። መምህርት ንግሥቲ ግን ችግሩን የፈጠሩ ፖለቲከኞች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ይፈልጋሉ።
“ይኸን ችግር የፈጠሩት አመራሮች ናቸው። ከሕዝብ የመጣ ችግር አይደለም” የሚሉት ንግሥቲ “አሁንም ማስተካከል ካለባቸው፤ እነሱ ናቸው ማስተካከል የሚችሉት። ስለዚህ መሪዎቹ ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ቢፈቱት የሚል ዕምነት ነው ያለኝ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽዖ አበርክቷል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ