1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንሶና አካባቢው ተፈናቃዮች አቤቱታ

ሐሙስ፣ ኅዳር 1 2015

ኢሰመኮ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓም ባወጣው መግለጫ በኮንሶ ዞን ፣ በአሌ ፣ በደራሼና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ኮሚሽኑ ሥጋቱን የገለጸው ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. አደረኩት ባለው ክትትል ባዘጋጀው ባለ 21 ገጽ ሪፖርቱ ነው ፡፡

 Ethiopian Human Rights Commission about SNNPR human rights case
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኮንሶና አካባቢው የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል አለ፡፡ ኮሚሽኑ በአካባቢው ባደረኩት ምልከታ አረጋገጥኩ እንዳለው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በአካባቢው ተፈናቅለው የሚገኙ ከ145 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መሠረታዊ የሚባሉ ሰብአዊ ድጋፎች እየቀረቡላቸው አይደለም ፡፡ የአካባቢው ባለሥልጣናት በበኩላቸው የድጋፍ አቅርቦቱ በቂ ባይሆንም በመንግሥት በኩል ክፈተቶችን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ ፡፡ 
የ72 ዓመት አዛውንት የሆኑት ገረመው ኦርካይዶ በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ መሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ በወረዳው ቢርቢርሳ በተባለ ቀበሌ መወለዳቸውን የሚናገሩት ገረመው ‹‹ በዚሁ ቀበሌ ተድሬ የልጅ ልጆች አይቼበታለሁ ›› ይላሉ ፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በአካባቢው በተነሳው የማዋቅር ጥያቄና የወሰን ይገባኛል  ጭቅጭቅ ወትሮ ሰላማዊ የነበረው ቢርቢሳ  የግጭትና የሞት ቀጠና መሆን መጀመሩን  የሚያስታውሱት ገረመው በዚህም ሳቢያ እሳቸውን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ የቀበሌይቱ ነዋሪዎች ወደ ጉማይዴ ከተማ  በመሸሽ አሁን ድረስ በተፈናቃይነት እየኖሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ ፡፡ ‹‹ ተፈናቅለን ከመጣን ወዲህ በቂ የምግብ ደጋፍ እየቀረበልን አይደለም ›› የሚሉ ገረመው ‹‹ ብዙዎቻችን በችግር ውስጥ ነው ያለነው ፡፡ ባለፈው ጊዜ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰዎች መጥተው ችግራችንን ገልጸንላቸው ነበር ፡፡ ከዚያም ወዲህ ቢሆን መፍትሄ አላገኘንም ፡፡ የዕለት ድጋፍ እንድናገኝና ወደ አካባቢያችን ለመመለስ ፍላጎት ቢኖረንም የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ይህ ሊሆን አልቻለም ›› ብለዋል ፡፡ 

ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የተፈናቃዮቹ ይዞታና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ  

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓም ባወጣው መግለጫ በኮንሶ ዞን ፣ በአሌ ፣ በደራሼና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ሥጋቱን የገለጸው ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሰረት በማድረግ አደረኩት ባለው ክትትል ባዘጋጀው ባለ 21 ገጽ ሪፖርቱ ነው ፡፡ የክትትል ሥራውን ለማከናወን ጾታን፣ ዕድሜን እና የአካል ጉዳትን መሰረት ያደረጉ 18 የቡድን ውይይቶችን ከተፈናቃዮች ጋር ማድረጉን የጠቀሰው የኮሚሽኑ ሪፖርት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ውይይቶችን እና ቃለ መጠይቆችን ማከናወኑን ዘርዝሯል፡፡ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎቹ ምልከታ ማድረጉን ፣   መረጃና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡንም ገልጿል፡፡  
እንጉዳይ መስቀሌ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፣ ስደተኞችና ፍልሰተኞች መብት የሥራ ክፍል ሃላፊ ናቸው ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ክትትል በተደረገባቸው በእነዚሁ አካባቢዎች በአጠቃለይ 145,933 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የጠቀሱት እንጉዳይ ከእነዚህ መካከል 53,400 ተፈናቃዮች በኮንሶ፣ 40,000 ተፈናቃዮች በዲራሼ፣ 8,331 ተፈናቃዮች በአሌ እና 44,202 ተፈናቃዮች በአማሮ የሚገኙ መሆናቸውን ነው ለዶቼ ቬለ DW  የገለጹት ፡፡ ድርቅ + ግጭት + የዋጋ ውድነት = የኮንሶ ፈተና
በአሁኑወቅት ለተፈናቃዮቹ ተደራሽ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ እንደማይቀርብ እና በዚህም የተነሳ ለሰብአዊ ቀውስ መዳረጋቸው የሚናገሩት እንጉዳይ ‹‹ በሥፍራው ተገኝተን እንዳረጋገጠነው የምግብ እጥረት ምልክቶች በሕፃናት እና በአጥቢ እናቶች ላይ ይስተዋላል ፡፡ በተለይ በአካባቢዎቹ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ በተፈጠረው ድርቅና በግጭቱ ምክንያት የእርሻ ሥራ በመስተጓጎሉ የምግብ እጥረት ከመከሰቱም በላይ የረሀብ ሥጋት መኖሩ ተመላክቷል ›› ብለዋል ፡፡ 
ዘላቂ መፍትሔን አስመልክቶ መንግሥት በቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው አስተማማኝ ፀጥታና ደኅንነት በማረጋገጥ እና መደበኛ ኑሮ ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታ በመፍጠር ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው የጠየቁ ተፈናቃዮች ነበሩ ያሉት እንጉዳይ ‹‹ ነገር ግን ይህንን ለማሳካት የሚያስችል የፀጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ መመለስ አልቻሉም ፡፡  በመሆኑም የዞን ፣ የክልል ፣  የፌዴራል መንግሥታትና  ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተፈናቃዮቹ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ የሚገኙበት ሁኔታ ሊያመቻቹ እንደሚገባ ጠቁመናል ፡፡ እንዲሁም ወደ ቦታቸው በመመለስ መልሶ ማቋቋም እንደሚገባም ምክረ ሀሳብ ተሰጥቷል ›› ብለዋል ፡፡ 

ምስል Ethiopian Human Rights Commission

በኮንሶ ዞን ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት

የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች በተፈናቃዮቹ ዙሪያ ምን ይላሉ ? 
ዶቼ ቬለ DW  በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት ዙሪያ የደቡብ ክልልንም ሆነ የፌዴራል ሥራ አመራር ኮሚሽን የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሃላፊዎቹን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ያምሆኖ በደቡብ ክልል የኮንሶ ዞን መስተዳድር የሥራ ሃላፊዎች በኮሚሽኑ የቀረቡ ክፍተቶችን ለማረም እየተሠራ ይገኛል ይላሉ ፡፡ የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ በአካባቢው ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ከደቡብ ክልል ፣ ከፌዴራሉ መንግሥት ፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ከተለያዩ የማህብረሰብ ክፍሎች ድጋፎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል ፡፡ ይሁንእንጂ አቅርቦቱ ከተረጂዎች ቁጥር ጋር አለመመጣጠንና በጉዞ ሂደት መዘግየት በሰብአዊ ድጋፍ አቅርበት ላይ ክፍተት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል የሚሉት አቶ ሠራዊት  በቀጣይ ክፍተቶቹን ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡ የፀጥታ ሥጋትና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ በኮንሶ ዞንና በደቡብ ክልል መስተዳድር በኩል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ሠራዊት ‹‹ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ በቅድሚያ የዕርቅ እና የሰላም ግንባታ ሥራዎች መከናወን አለባቸው ፡፡ ለዚህም በየአካባቢው ካሉ የአገር ሽማግሌዎች ጋር እየተሠራ ይገኛል ፡፡ በዚህም አሁንባለው ሁኔታ መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል ፡፡ ለምሳሌ ቀደምሲል በህዝቦቹ መካከል ተቋርጦ የነበረውን ገበያ ማስጀመር የተቻለ ሲሆን ወደ አሌና ደራሼ መስመሮች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቀጥል ተደርጓል ፡፡ ይህም በቀጣይ ተፈናቃዮቹን ወደ ቦታቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም መሠረት የሚጥል ይሆናል ›› ብለዋል ፡፡ 
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW