መፍትሔ ያላገኘው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ፈተና
ሐሙስ፣ ነሐሴ 8 2017
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ደረጃ በሚገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንደተገለጸው፤ በየቦታው በተለይም በከተሞች መግቢያ እና መውጫ ገመድ ተወጥሮ ከአሽከርካሪዎች የሚሰበሰበው ክፍያ በመጠን ቀንሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የትራንስፖርት ዘርፍ ባለስልጣናት የኬላዎች ዓለማ ሕገወጥነትን መቆጣጠር እንጂ መንገደኞች እና አሽከርካሪዎችን በማማረር ያልተገባ ገቢ መሰብሰብ አለመሆኑንም ማስረዳታቸውም እንዲሁ ይታወሳል፡፡
ዛሬ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስከያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ግን የተቀነሰ አሊያም የተነሳ ኬላ አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡ “የተነሳ ኬላ የለም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ፤ መንግስት ግን ከፌዴራል ጀምሮ ይህን ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመው ቅሬታችን ቢቀበልም ከመታዘዝ ውጪ ሆነው እየሰሩ ያሉት ታች በወረዳ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት መንገዶች በሚያልፍባቸው ከተሞች በሙሉ ነው ይህን ችግር እየፈጠሩ ያሉት” ብለዋል፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም በቅርቡ ከንግድ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት የኬላዎች ዓላማ ከሰዎች ገንዘብ መሰብሰብ አይደለም” በማለት ነገሩ እንደሚስተካከል ቃል ቢገቡም እስካሁን የተስተካከለ ነገር አለመኖሩንም አስረድተዋል፡፡
የማህበሩ ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ሰለሞን ካልተገባው የክፍያ መጠየቅ በተጨማሪ በአሽከርካሪዎች ላይ አላስፈላጊ በደሎች እና የመብት ጥሰቶች በተለያዩ ታጣቂዎች እንደሚፈጸሙም አመልክተዋል፡፡ “ገመዶቹ ቀን ተነስተው በሚታይባቸው አከባቢዎች ሌሊቱን በታጣቂዎች እና ሚሊሻዎች ገመድ ተወጥሮ ሾፌሮችን ገንዘብ ማስከፈል፣ መደብደብ እና ማገት ተስፋፏቷልም” ነው ያሉት፡፡ አልከፍልም ያለ ሾፌር በሚሊሽያዎች ይደበደባል ያሉት አቶ ሰለሞን “በተለይም በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡ አንድ ሾፌር ከጎንደር ጋይንት በመነሳት አዲስ አበባ እስኪገባ እስከ 75 ሺህ ብር በአንድ ጉዞ ብቻ ለመንግስት ሚሊሻዎች እና በየቦታው ለሚቆሙ ታጣቂዎች መክፈሉንም በአብነት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡ ችግሩ ለአሽከርካሪዎች አሳሳቢ ነው ያሉት ሃላፊው መንግስት ሁኔታውን በቁጥጥር ስር እስከሚያውል ድረስ አሽከርካሪዎች ሌሊት ከመጓዝ እንዲቆጠቡም መክረዋል፡፡
በየክልሎቹ በተለይም ኦሮሚያ ክልል፣ አማራ ክልል እና በሶማሌ ክልል እንዲሁም በድረዳዋ ከተማ አስተዳደር መሰል ክፍያዎች መንግስት ባሳተመው ሕጋዊ ደረሰኝ ታግዞ እንደሚሰበሰብም ገልጸዋል፡፡ “ድረዳዋ አሁን ከከተማ ጭነው የሚወጡትን ብቻ 600 ከመቀረጥ ሌላለአሽከርካሪዎች እጅግ መልካም አያያዝ የሚደርግ አከባቢ ነው፡፡ በኦሮሚያ ሞጆን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች አንዳንዴ ከሚደረግ የዘፈቀደ ክፍያ ውጪ በደረሰኝ ነው ክፍያው የሚፈጸመው፡፡ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ ግን የተለየ ነው፤ ታጣቂዎች ጭምር ደረሰኝ እየሰጡ ነው ከአሽከርካሪዎች ገንዘብ የሚሰበስቡት” ብለዋል፡፡እንደ ሃላፊው ገለጻ ከዚህ ከክፍያ ጥያቄም የከፉ አሉታዊ እርምጃዎች በየጊዜው ሾፌሮች ላይ ይወሰዳሉ፡፡ “እገታ፣ ግድያ እና መቁሰሎች አሉ በየመንገዱ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በሁሉም አከባቢዎች አሉ፡፡ አንዳንዴ ነዳጅና ማዳበሪያ የጫኑ አሽከርካሪዎች ታጅበው ካልሆነ አደጋ ይገጥማቸዋል፡፡ ለማህበረሰቡ ነዳጅ/ማዳበሪያ ለማራገፍ ሄደው ሲመለሱ እገታ እና ግድያ እየተፈጸመባቸው ነው” በማለት እሮሮአቸውን አሰምተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ