1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሚሊዮኖችን አደጋ ላይ የጣለው የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ

ቅዳሜ፣ የካቲት 29 2017

የአሜሪካ የውጭ እርዳታ መቋረጥ የቲቢ በሽታን ህክምና በመቀነስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣሉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።እንደ ድርጅቱ የአሜሪካ እርዳታ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 3.65 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በበሽታው ከመሞት ታድጓል።

Schweiz Weltgesundheitsorganisation in Genf
ምስል፦ Denis Balibouse/REUTERS

ሚሊዮኖችን አደጋ ላይ የጣለው የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ

This browser does not support the audio element.


የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን እንዳስታወቀው የአሜሪካ የውጭ እርዳታ መቋረጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥለውን የሳምባ ነቀርሳ አገልግሎት ተደራሽነት እንዲቀንስ አድርጓል። 
እንደ ድርጅቱ መግለጫ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ የውጭ እርዳታን ለተወሰነ ጊዜ  ለማቆም መወሰኑ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) በሽታን በመከላከል ረገድ የተገኘውን ውጤት ሊቀለብስ ይችላል። 
የድርጅቱ የቲቢ እና የሳንባ ጤና ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ቴሬዛ ካሳዬቫ  እንደተናገሩት አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ፣ ቲቢን በመዋጋት የተገኘው  ውጤት አደጋ ላይ ነው።
ከዚህ አንፃር የጋራ ምላሾች  ፈጣን እና  ስልታዊ  በማድረግ ተጋላጭ የሆኑትን ለመጠበቅ እና ቲቢን ለማጥፋት የሚያስችል ጥንካሬን ቀጣይ እና የተሟላ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት  ለሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) በሚደረገው የመከላከል፣ ምርመራ እና ህክምና አገልግሎቶች ከ79 ሚሊዮን በላይ ህይወትን መታደግ ተችሏል።

በተለይ ከአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በተገኘ ወሳኝ ድጋፍ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 3.65 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በበሽታው ከመሞት መታደጉን ድርጅቱ ገልጿል።
ይህ ውጤት በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች በተለይም ከዩኤስኤአይዲ በተገኘ ወሳኝ የውጭ ዕርዳታ የተመራ ነው። በመሆኑም የአሁኑ  ድንገተኛ የገንዘብ ቅነሳ የተገኘውን  ትልቅ ውጤት እንዳይቀለብስ ያሰጋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ - በተለይም ለበሽታው በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችም ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላል ሲል ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

እንደ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፉት 20 ዓመታት  ለሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) በሚደረግ ህክምና ከ79 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወትን መታደግ ተችሏል።ምስል፦ Luke MacGregor/REUTERS

ድርጅቱ አያይዞም፤በዚህ ፈታኝ ጊዜ፣ ለበሽታው  ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ መንግስታት፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና ዓለምአቀፍ አጋሮች ዘላቂ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ  የተቀናጄ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

ሻአዳ ኢስላም የተባሉ የአውሮፓ ህብረት ተንታኝ በበኩላቸው ይህንን ተግዳሮት ተባብሮ ለመስራት እንደ እድል መጠቀም ይቻላል ይላሉ።
«ነገር ግን በረጅም ጊዜ ሁላችንም ፣ የአውሮፓ ህብረት ብቻ ሳይሆን ፣ በአለምአቀፍ ደቡባዊ ክፍል ውስጥ ያሉ ሀገራትም  በትክክል ተባብረው ከሰሩ ይህንን እንደ እድል ልንጠቀምበት የምንችል ይመስለኛል ። ተለዋዋጭ የዓለም ሥርዓትን ለማመቻቸት እና እውነተኛ ባለብዙዋልታ ዓለም ለመፍጠር ያስችለናል።»ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ የአውሮፓ ህብረት የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባም ያስረዳሉ። «የአውሮፓ ህብረት ይህ እድል እንዳለው ግልፅ ነው። ግን ከአሜሪካ ፖሊሲዎች ግንኙነቱን ለማቋረጥ ወይም እራሱን ለማራቅ የበለጠ ጠንክሮ መሥራት አለበት። ምክንያቱም ቀደም ባሉት ጊዜያት እና አሁንም ፣ በአውሮፓ ውስጥ የእነሱን ለማግኘት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የመመልከት አዝማሚያ አለ። ይህ በትራምፕ ዘመን መቆም አለበት።»ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካለቲቢ መርሃ ግብሮች ከሚደረገው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ  ድጋፍ  አንድ አራተኛ ያህሉን  አስተዋፅኦ ታደርጋለች።ይህ የሁለትዮሽ የገንዘብ ድጋፍም    በዓመት ከ200 እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ  መሆኑን  የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ዩኤስኤአይዲ የትራምፕ አስተዳደር ዒላማ ከሆኑት የረድኤት ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፤ ይህም የፌደራል መንግስትን ወጪ ለመቀነስ እና የትራምፕን መንግስት ውጤታማነት ለመጨመር በሚል  በቢሊየነር ኤሎን ማስክ የሚመራ ዘመቻ ነው።

ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW