1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሚያዝያ 17 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2014

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተደረጉ የማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል። ባለፈው ሳምንት አዲስ የተወለደ ልጁን በሞት ያጣው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሜዳ ተመልሶ በፕሬሚየር ሊግ ለማንቸስተር ዩናይትድ 100ኛ ግቡን አስቆጥሯል። ነገ እና እና ከነገ በስተያ የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይኖራሉ።

Champions League - Young Boys Berne v Manchester United - Christiano Ronaldo
ምስል Lairys Laurent/ABACA/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተደረጉ የማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል። ባለፈው ሳምንት አዲስ የተወለደ ልጁን በሞት ያጣው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሜዳ ተመልሶ በፕሬሚየር ሊግ ለማንቸስተር ዩናይትድ 100ኛ ግቡን አስቆጥሯል። ነገ እና እና ከነገ በስተያ የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይኖራሉ። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ታይሰን ፉሪ በዝረራ አሸንፏል። 

አትሌቲክስ
ትናንት ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው የዓለም ምርጥ በተባለ ውጤት 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ኾናለች። በዚህም በሀገሯ ልጅ በአትሌት መሰለች መልካሙ ከስምንት ዓመታት በፊት ተይዞ የነበረውን የቦታውን ርቀት በአራት ተኩል ሰከንድ አሻሽላለች። ርቀቱም እስከ ዛሬ በተደረጉ ውድድሮች በሴቶች ሦስተኛው ምርጥ ሰአት ተብሎም ተመዝግቧል። በማሸነፏ እጅግ ደስተኛ መሆኗን የገለጠችው አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው «ውድድሩ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር። ተመልካቾች በሚደንቅ ኹኔታ ድጋፋቸውን ሲያደርጉልኝ» ነበር በማለት ምሥጋናዋን አቅርባለች። የቦታውን ርቀት ክብረወሰን በመስበሯ እና በማሸነፏም የ40 ሺህ ዩሮ ተሸላሚ ኾናለች።  አትሌት የዓለምዘርፍ በቅርቡ የካቲት 20 ቀን፣ 2014 ዓም ካስቴሎን ስፔን ውስጥ በተከናወነው የቅይጥ ጾታ የ10 ሺህ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ፉክክርም በሴቶች ዘርፍ 29 ሰከንድ ከ14 ሰከንድ በመሮጥ ድንቅ ውጤት አስመዝግባ ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ምስል AP
ምስል Andrew Couldridge/Reuters

በትናንቱ የሐምቡርግ ማራቶን ሩጫ የሀገሯ ልጆች ተከታትለው በመግባት የሁለተኛ እና ሦስተኛ ቦታንም ይዘዋል። አትሌት ፍቅርተ ወረታ 2:26:15 በመሮጥ የሁለተኛነት ድልን አስመዝግባለች። አትሌት ቦኔ ጩሉቃ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ለድል በቅታለች። የሮጠችውም 2:26:23 ነው። ከስድስት ሰከንድ በኋላ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ጸጋነሽ መኮንን ተከትላት በመግባት የአራተኛ ደረጃን ይዛለች። እስከ ዐሥረኛ ደረጃ ከገቡ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሙሉ ጋዲሳም የስምንተኛ ደረጃን አግኝታለች። 

በወንዶች የሐምቡርግ የሩጫ ውድድር ኬንያዊው ሳይቢሪያን ኮቱትም የቦታውን ክብረወሰን መስበር ችሏል። ኬኒያዊው አትሌት 2 ሰዓት ከ 04 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ በመሮጥ የገባበት ሰአት የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ባለድሉ የሀገሩ ልጅ ኢሉይድ ኪፕቾጌ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ይዞት የቆየውን ክብረወሰን ያስቀማ ነበር። ኡጋንዳዊው ስቴፈን ኪሳ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ወርቅነህ ታደሰ ደግሞ ከኡጋንዳዊው ሯጭ 19 ሰከንድ በኋላ በመግባት ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።  የገባበት ሰአትም 2 ሰዓት ከ 05 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ ነው። አራተኛ ደረጃ ያገኘውን ታዋቂ ኡጋንዳዊው አትሌት ቪክቶር ኪፕላጋት በመከተል ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አበበ ነገዎ እና ማስረሻ በሪ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። እስከ ዐሥረኛ ደረጃ ይዘው ከገቡ አትሌቶች መካከል ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ባዘዘው አስማረ የ9ኛ ደረጃን አግኝቷል።  

ምስል picture-alliance / dpa

በተለያዩ ሃገራት በተደረጉ የማራቶን ሩጫዎችም ኢትዮጵያውያን ድል ተቀዳጅተዋል። በስፔን ማድሪድ ማራቶን ሥራነሽ ይርጋ የቦታውን ሰዓት በማሻሻል ለድል ስትበቃ፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መሰረት አበባየሁ ደግሞ የ2ኛ ደረጃን በመያዝ ለድል በቅታለች። ኬኒያዊቱ ማውሪን ቼፕኬሞይ ባሸነፈችበት የትናንቱ የኔዘርላንድ ኤንሼዴ ማራቶን ደግሞ ዓለምፀሀይ አሰፋ 2ኛ ሆና ለድል በቅታለች፤ አበራሽ ፈይሳ 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በወንዶች ፉክክር ታዱ አባተ 3ኛ ደረጃን ይዞ ለድል በቅቷል። ኬንያውያት አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ተከታትለው ትናንት በገቡበት የቪዬና ማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ኡርጌ ሰቦቃ 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኬንያውያን 1ኛ እና 2ኛ በወጡበት ተመሳሳይ የማራቶን ሩጫ የኤርትራው ሯጭ ዕቁበ ክብሮም የሦስተኛ ደረጃን አግኝቶ ለድል በቅቷል። እስከ ዐሥረኛ ደረጃ ሌሎች ኬንያውያን በተደረደሩበት በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት አብዲ ፉፋ የስምንተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። 

እግር ኳስ
ማንቸስተር ዩናይትድ በሚኬል አርቴታ አርሰናል 3 ለ1 በተሸነፈበት የቅዳሜው የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለማንቸስተር ዩናይትድ 100ኛ ግቡን አስመዝግቧል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ አዲስ የተወለደ ልጁን በሞት በማጣቱ ምክንያት ባልተሰለፈበት ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ በሊቨርፑል የ4 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ከገጠመው ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት ጨዋታ ነበር ግብ ያስቆጠረው። ማንቸስተር ዩናይትድ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ከመምታት ይልቅ ለቡድኑ የመሀል አጥቂ ብሩኖ ፌርናንዴዝ አሳልፎ መስጠቱ ደጋፊዎችን አስደምሟል። ብሩኖ ፌርናንዴዝ 57ኛው ደቂቃ ላይ የተኘነውን የፍጹም ቅጣት ምት መትቶ ኳሷ የግቡ ቋሚን በመግጨቷ ግብ ከመሆን ተጨናግፎበታል። አርሰናል በዚህ ድሉ የቀጣይ ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ አራተኛ ቦታን ከቶትንሀም ተረክቧል። ከብሬንትፎርድ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ቶትንሀም በበኩሉ ወደ አውሮጳ ሊግ 5ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። 

ምስል Paul White/AP/dpa/picture alliance

የፕሬሚየር ሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲ ዋትፎርድን ቅዳሜ ዕለት 5 ለ1 የግብ ጎተራ ባደረገበት ግጥሚያ ጋብሬል ጄሱስ አራት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ብቃቱን አስመስክሯል። ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ጋር ያለውን የግብ ልዩነትም ወደ አራት ዝቅ አድርጎታል። ማንቸስተር ሲቲ የዘንድሮውን የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ በእጁ ለማስገባት ቀሪ አምስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይኖርበታል። አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ከስራቸው የሚከተለው የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑልን በልጠው ዋንጫውን ለመውሰድ ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ይገባናል ሲሉ ቡድናቸውን አስጠንቅቀዋል። እስካሁን ማንቸስተር ሲቲ 80፤ ሊቨርፑል 79 ነጥብ ሰብስበዋል። ሊቨርፑል ወሳኝ የተባለለትን ግጥሚያ ትናንት በሜዳው አንፊልድ አከናውኖ ከረፍት በኋላ ባስቆጠሩት ግቦች ኤቨርተንን 2 ለ0 አሸንፏል። በሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ትናንት 86ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ አንድ ተጨዋቹ የተሰናበተበት ዌስትሀም ዩናይትድን 1 ለ0 አሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ቡንደስሊጋ 
በጀርመን ቡንደስሊጋ በብዙዎች ዘንድ ሲጠበቅ በነበረው የባየር ሙይንሽን እና ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ግጥሚያ መሪው 3 ለ1 አሸንፏል። ለባየር ሙይንሽን ሠርጌ ግናብሬ፤ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ እንዲሁም ጃማል ሙሲያላ ግቦችን አስቆጥረዋል። ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ብቸኛውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ኤምሬ ቻን አስቆጥሯል። በዚህም መሰረት ባየር ሙይንሽን በ75 ነጥብ መሪነቱን አስጠብቋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ63 ነጥብ ይከተላል። ግሮይተር ፊዩርትን 4 ለ 1 ያሸነፈው ባየር ሌቨርኩሰን 55 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ይከተላል። 17 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ 18ኛ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ለሚገኘው ግሮይተር ፊዩርት የትናንቱ በሜዳው መሸነፍ መሰናበቻውን ይበልጥ አጠናክሮታል። 54 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ በሜዳው ባደረገው ግጥሚያ በዑኒዮን ቤርሊን 2 ለ1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ምስል Christian Kaspar-Bartke/Getty Images

ሻምፒዮንስ ሊግ
የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስተያ ይከናወናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አንገት ለአንገት የተናነቁት ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግም ምናልባት በፍጻሜው ሊገናኙ ይችል ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በነገው እለት ማንቸስተር ሲቲ ኢታህድ ስታዲየም ውስጥ ከሪያል ማድሪድ ጋር ሲጫወት፤ ከነገ በስተያ ደግሞ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ስታዲየም ቪላሪያን ያስተናግዳል። 

ቡጢ
ዩክሬናዊው የከባድ ሚዛን የዓለም ባለድል ክሊችኮን ማሸነፍ የቻለው የ33 ዓመቱ ታይሰን ፉሪ ዳግም ድል በመቀዳጀት ቀበቶውን አስጠብቋል። ለንደን ከተማ 94 ሺህ ታዳሚያን በተገኙበት የዌምብሌይ ስታድየም ውስጥ በተከናወነው የከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ታይሰን ፉሪ ያሸነፈው የ34 ዓመቱ ዲሊያን ዋይትን ነው። ለድል የበቃውም ስድስተኛው ዙር ሊጠናቀቅ አንድ ሰከንድ ሲቀረው ተጋጣሚውን በመዘረር ነበር። ውድድሩንም የመሀል ዳኛው ማርክ ሳይደን አቋርጠውታል። 

የመኪና ሽቅድምድም
ጣሊያን ኢሞላ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የኤሚሊያ ሮማግና የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዓለም ባለድሉ ማክስ ፈርሽታፐን አሸነፈ። የፌራሪ ግዛት በሆነው የጣሊያን ሽቅድምድም ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬዝም የሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። ሬድ ቡል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ማስመዝገቡን በተመለከተ አሸናፊው ማክስ ይገባናል ብሏል። የማክላረኑ አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በአጠቃላይ ነጥብ እስካሁን በአንደኛነት የሚመራው ሻርል ሌክሌር ስድስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል ስምንተኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ የሰባት ጊዜያት ባለድሉ የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን 13ኛ ደረጃን ይዞ ያለምንም ነጥብ አጠናቋል። 

ምስል ANDREJ ISAKOVIC/AFP

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW