1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሚያዝያ 3 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2014

የሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውብ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት መሪው ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከሊቨርፑል ጋር አቻ ወጥቷል።  ቸልሲ ተጋጣሚውን የግብ ጎተራ አድርጎ ጉድ ሲያደርግ፤ አርሰናል ከወራጅ ቀጣና በመጣ ቡድን ሽንፈት ገጥሞታል።

Fussball Bundesliga Hertha BSC - 1. FC Union Berlin
ምስል Tilo Wiedensohler/camera4+/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውብ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት መሪው ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከሊቨርፑል ጋር አቻ ወጥቷል።  ቸልሲ ተጋጣሚውን የግብ ጎተራ አድርጎ ጉድ ሲያደርግ፤ አርሰናል ከወራጅ ቀጣና በመጣ ቡድን ሽንፈት ገጥሞታል። በቡንደስሊጋው ላይፕትሲሽ ሆፈንሀይምን በሰፋ የግብ ልዩነት ሲያሸንፍ፤ ብርቱ ፉክክር በታየበት አዝናኝ ጨዋታ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ለፍራይቡርግ እጅ ሰጥቷል። ባየርን ሙይንሽን በመሪነቱ እንደገሰገሰ ነው። የፖርቹጋል አቻውን በሰፊ ግብ ያሸነፈው የጀርመን ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ፉክክር ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

ሻምፒዮንስ ሊግ

በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ግማሽ ፍፋሜ ለማለፍ የሚደረጉ የእግር ኳስ የመልስ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት በሚደረጉ ግጥሚያዎች የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን የስፔኑ ቪላሪያልን ይገጥማል። ሌላኛው የስፔን ቡድን ሪያል ማድሪድ በሳምንቱ መጨረሻ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ በግብ የተንበሸበሸው የእንግሊዙ ቸልሲን ያስተናግዳል። ከነገ በስትያም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ እና የእግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ይጋጠማሉ። ትናንት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ድንቅ ጨዋታ ያሳየው ሊቨርፑል የፖርቹጋሉ ቤኔፊካን በሜዳው ያስተናግዳል።

ምስል Javier Sorano/AFP

በካሪም ቤንዜማ ድንቅ ብቃትና ሔትትሪክ ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ ቸልሲን በ3 ለ1 ግብ ያስደነገጠው ሪያል ማድሪድ በሳንቲያጎ ቤርናቤዎ ሜዳው ለቸልሲ መከራ መሆኑ አይቀርም። ሆኖም አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ለቸልሲ ዝቅተና ግምት እንደማይኖራቸው ዛሬ ተናግረዋል። በፕሬሚየር ሊጉ 6 ግብ የተንበሸበሸው ቸልሲ ከሪያል ማድሪድ ጋር ወደ ጭማሪ ሰአት ጨዋታ ለመግባት አለያም ለማሸነፍ 3 ግብቦችን ማስቆጠር ይኖርበታል። ያ የመሆን እድሉ ግን እጅግ ጠባብ ነው። ግን ደግሞ የኳስ ነገር ዐይታወቅም። በሜዳው ኤቲሀድ ስታዲየም አትሌቲኮ ማድሪድን 1 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ከተከላካይ እስከ አጥቂው ክፍል እጅግ የተደራጀ ነው። እናም ማንቸስተር ሲቲ አሁን ባለው ጠንካራ አቋሙ ወደ ማድሪድ አቅንቶ ዋንዳ ሜትሮፖሊታን ስታዲየም ውስጥ አትሌቲኮ ማድሪድን ዳግም ያሸንፋል የሚሉ በርካቶች ናቸው።  

አ ሉዝ ስታዲየም ውስጥ የፖርቹጋሉ ቤኔፊካን በገዛ ሜዳው 3 ለ1 ጉድ ያደረገው ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ከነገ በስትያ በሚያደርገው ጨዋታ ያለጥርጥር ያሸንፋል የሚሉ ይበዛሉ። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው የትናንቱ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ጠንካራ ቡድን መሆኑን ያስመሰከረው ሊቨርፑል ቤኔፊካን በመልሱ ጨዋታ አንፊልድ ደጋፊው ፊት አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉ የሚያጠራጥር አይመስልም።

በሜዳው ተጫውቶ ባየርን ሙይንንን 1 ለ0 ያሸነፈው ቪላሪያል በወቅቱ ድንቅ የሚባል ጨዋታ ዐሳይቷል። በስፔን ላሊጋ የ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቪላሪያል ነገ የሚጋጠመው ጀርመን ውስጥ በባየርን ሙይንሽን ሜዳ አሊያንስ አሬና ስታዲየም ውስጥ ነው። እናስ ዳግም ጥንካሬውን ዐሳይቶ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፍ ይሆን ወይንስ በቡንደስሊጋው መሪነት ላይ የሚገኘው ባየርን ሙይንሽን ሽንፈቱን ይበቀላል? ጨዋታውን ነገ መከታተል ነው።

የአውሮጳ ሊግ

የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች እንዳበቁም ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚደረጉ የአውሮጳ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች ሐሙስ እለት ይኖራሉ።  ምሽቱን ለሁለት ሰአት ሩብ ጉዳይ ላይ የጀርመኑ ላይፕትሲሽ ከጣሊያኑ አታላንታ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ቀዳሚ ነው። ከዚያም የፈረንሳዩ ሊዮን ከእንግሊዙ ዌስት ሐም ዩናይትድ፤ የስፔኑ ባርሴሎና ከሌላኛው የጀርመን ቡድን አይንትራኅት ፍራንክፉርት፤ እንዲሁም የስኮትላንዱ ግላስኮው ሬንጀርስ ከፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ብራጋ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይከተላሉ። ሦስቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ነው የሚካኼዱት።

ፕሬሚየር ሊግ

ምስል Jon Super/AP Photo/picture alliance

ትናንት ብርቱ የማሸነፍ ፉክክር በታየበት የኢትሀድ ስታዲየም ግጥሚያ የፕሬሚየር ሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲ እና በአንድ ነጥብ ልዩነት የሚከተለው ሊቨርፑል ነጥብ ተጋርተዋል። የጨዋታዎች ሁሉ ጨዋታ በተባለለት ፍልሚያም ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ማንቸስተር ሲቲ የመጀመሪያ ግቡን በደብረወይነ ያስቆጠረው ጨዋታው በተጀመረ 5ኛው ደቂቃም ሳይሞላ ነበር። ግቧም የተገኘችው በሊቨርፑል የመከላከል ድክመት ሲቲ ያገኘውን ኳስ በመጠቀሙ ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ ግን ዲዬጎ ጆታ ለማንቸስተር ሲቲ ምላሽ የሆነውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። በረዥም ርቀት የተላከለትን ኳስ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ለዲዬጎ ጆታ አመቻችቶ ያቀበለበት ስልት ድንቅ የሚያስብለው ነው። 36ኛው ደቂቃ ላይ ግን የሊቨርፑል ተጨዋቾች የማንቸስተር ሲቲ አጥቂዎችን ከጨዋታ ውጪ አድርገው በተደረደሩበት ጋብሬል ጄሱስ ባልተጠበቀ ቅጽበት አፈትልኮ በመውጣት 2ኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። የጋብሬል ጄሱስ ድንቅ ብቃት የታየበት አጋጣሚ ነው።

ከእረፍት መልስ ሊቨርፑል አቻ ለመሆን የፈጀበት 45 ሰከንዶች ብቻ ነበር። ግቧ ሳዲዮ ማኔ 30ኛ ዓመቱን በደፈነበት ዕለት የተገኘች በመሆኗ እንደ ልዩ የልደት ስጦታ ትታያለች። በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል በአሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲን በኳስ ይዞታም ሆነ በአጠቃላይ በልጦት ታይቷል። በርካታ የግብ ዕድሎችንም አግኝተው ነበር ባይጠቀሙበትም። ማንቸስተር ሲቲ 90ኛው ደቂቃ ላይ በማሬዝ በኩል ያገኘው የግብ እድል የሊቨርፑል ደጋፊዎችን ልብ ቀጥ ልታደርግ የደረሰች ነበር ማለት ይቻላል። በቅጣት ምት የተገኘው ኳስ ከተደረደሩት የሊቨርፑል ተጨዋቾች በፊርሚኖ አናት በኩል እየተጠመዘዘች በመክነፍ ያረፈችው የግቡ የቀኝ የማእዘን ቋሚ ላይ ነበር።

ምስል Jon Super/AP Photo/picture alliance

ጨዋታው እንደተጠናቀቀ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕን የጨበጡበት ኹኔታ  አድናቆታቸውን ያሳዩበት ነበር። ሁለቱም አሰልጣኞች የጀርመን ቡንደ ስሊጋ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ፔፕ ጓርዲዮላ ከዬርገን ክሎፕ የአሰለጣጠን ልምድ በመውሰድ አብነታቸው መሆናቸውንም በኋላ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አልሸሸጉም። 74 እና 73 ነጥብ ሰብስበው አንገት ለአንገት ከተናነቁት ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል የዘንድሮ የዋንጫ ባለቤቱን ለመለየት ሰባት ጨዋታዎች ይቀራሉ። ፔፕ ጓርዲዮላ ከእንግዲህ አንድም ጨዋታ ከተሸነፍን ስለዋንጫው ማሰብ አይኖርብንም ሲሉ አጠቃላይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ቀሪ ጨዋታዎች ሲታዩ ከሲቲ ሊቨርፑል ፈተና የሚገጥመው ይመስላል። ሁለቱ ቡድኖች ምናልባትም በሻምፒዮንስ ሊግ ዳግም ይገናኙ ይሆናል። በእርግጠኝነት ግን ለኤፍ ኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ የፊታችን ቅዳሜ ዳግም ይገናኛሉ።

በሌሎች ግጥሚያዎች ዌስትሀም ዩናይትድ ከታች ባደገ ቡድን ብሬንትፎርድ የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ኖርዊች በርንሊን 2 ለ0 አሸንፏል። ባለፈው ጨዋታ አርሰናልን 3 ለ0 ጉድ ያደረገው የፓትሪክ ቪዬራ ክሪስታል ፓላስ በላይስተር ሲቲ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። አርሰናል ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገው ብራይተን ቅዳሜ ዕለት የ2 ለ1 ዳግም ሽንፈት አስተናግዷል። ቶትንሀም አስቶን ቪላ ላይ 4 ግብ አከታትሎ በማግባት አንድም ሳይገባበት ድል ተቀዳጅቷል። ሊድስ ዋትፎርድን 3 ለ0 ሲያሸንፍ የሳምንቱ በርካታ ግብ የተመዘገበው በቸልሲ ነው። ቸልሲ የሳውዝሀምፕተን የግብ ክልል እየተመላለሰ በመምነሽነሽ 6 ለ0 ድል አድርጓል።

ምስል Pierre-Philippe Marcou/AFP

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ውድድሮች፦ ትናንት ፍራይቡርግ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 2 ለ1 እንዲሁም ላይፕትሲሽ ሆፈንሀይምን 3 ለ0 አሸንፈዋል። ባየርን ሌቨርኩሰን ከቦሁም ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ጨዋታዎች መሪው ባየርን ሙይንሽን አውግስቡርግን 1 ለ0 አሸንፏል። በቡንደስሊጋው ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽቱትጋርትን እንዲሁም ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ግሮይተር ፊዩርትስን 2 ለ0 ድል አድርገዋል። ኮሎኝ ማይንስትስን 3 ለ2 ማሸነፍ ችሏል። ዑኒዮን ቤርሊን ሔርታ ቤርሊንን 4 ለ1 እንዲሁም ቮልፍስቡርግ መከረኛው አርሜኒያ ቢሌፌልድን 4 ለ0 ድባቅ መትተዋል። ባየርን ሙይንሽን በ69 ነጥብ ቡንደስሊጋውን ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ60 እንዲሁም ባየርን ሌቨርኩሰን በ52 ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው። 51 ነጥብ ያለው ላይፕትሲሽ የአራተኛ ደረጃን ይዟል።

ምስል Mirko Kappes/ foto2press/picture alliance

የጀርመን ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የፖርቹጋል አቻውን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በሚደረገው ፉክክር የቅዳሜው ለሰባተኛ ጊዜ የተከናወነ ነበር። በአሰልጣኝ ማርቲና ፎስ-ቴክሌንበቡርግ የሚመራው የጀርመን ቡድን አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ በጎርጎሪዮሱ 2023 በሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን አንድ ጨዋታ ብጫ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ቀጣይ ውድድሮቹም ነገ ከሰአት በኋላ ከሠርቢያ ጋር የሚያደርገውን ጨምሮ ወደፊት ከቱርክ፣ እና ቡልጋሪያ ጋርም ይጋጠማል።

አትሌቲክስ

4ኛው የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ፌስቲቫል የአትሌቲክስ ውድድር ሰኞ፤ ሚያዝያ 3 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ጀምሯል። በውድድሩ 100 እና 5,000 ሜትርን ጨምሮ በተለያዩ ርቀቶች የሩጫ ፉክክር፤ የርቀት ዝላይ እና የጦር ውርወራ ይከናወናሉ።

ትናንት ኔዘርላንድስ ሮተርዳም ውስጥ በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶችም በወንዶችም ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር ፌቨርን ኃይሉ 2:22.01 በመሮጥ 1ኛ ደረጃን አግኝታ አሸንፋለች። በወንዶች ፉክክር ደግሞ አትሌት ልዑል ገብረስላሴ 2:04.56 በመሮጥ ለጥቂት የአንደኛ ደረጃውን አጥቷል። ብርቱ ፉክክር በታየበት ሩጫ ልዑል የ2ኛ ደረጃ አግኝቷል። በዚህ ውድድር የኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ባለድሉ ትውልደ ሶማሊያ ኔዘርላንዳዊው ሯጭ አብዲ ናጊዬ የአንደኛ ደረጃን አግኝቶ ለድል በቅቷል። የኬንያው ሯጭ ሮይበን ኪፕሮፕ ኪፕዬጎ የሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ዘንድሮ የመርሴዲስ ቡድን ብርቱ ፈተና ገጥሞታል። የአለማችን ምርጡ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የሚገኝበት መርሴዲስ ቡድን ኃላፊ ቶቶ ቮልፍ፦ ምናልባትም ሜርሴዲስ በማጠቃለያ ነጥቡ በዘንድሮ ውድድር ባድል የመሆን እድሉ ጠባብ ነው ሲሉ ዛሬ ይፋ አድርገዋል። ዘንድሮ ውጤት ከመርሴዲስ ቡድን የመራቁን ምሥጢርም ከራሱ ከመኪናው አሠራር ሊሆን ይችላልም ሲሉ በትዊተር ይፋዊ የመገናኛ አውታራቸው ዐሳውቀዋል። በዘንድሮ ውድድር መርሴዲስ ቡድን እስካሁን «37» ነጥብ ብቻ ሰብስቦ ከፌራሪ ኋላ ይገኛል። በአጠቃላይ ነጥብ የፌራሪው አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌር በ71 ነጥብ ይመራል። የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል በ37 ነጥብ ይከተላል።ሌላኛው የፌራሪው አሽከርካሪ ካርሎስ ሳይንስ 33 ነጥብ አለው፤ ደረጃውም ሦስተኛ ነው። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ሠርጂዮ ፔሬዝ በ30 ነጥብ የአራተኛ ደረጃ ይዟል። የ7 ጊዜያት የዓለም ባለድሉ የመርሴዲሱ ሌዊስ ሐሚልተን ዘንድሮ አልቀናውም። ከእነዚህ ሁሉ አሽከርካሪዎች ኋላ 28 ነጥብ ብቻ ሰብስቦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ያለፈው የውድድር ዘመን ባለድል የነበረው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐንም እንደ ዋነና ተቀናቃኙ ሌዊስ ዘንድሮ ውጤት ርቆታል። 25 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል።

ምስል Paul Crock/AFP/Getty Images

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከናወኑ አጠቃላይ ውድድሮች ተጠናቀው የውድድር ዘመኑ ባለድል የሚታወቀው ከ22 ዙር ውድድሮች በኋላ በኅዳር ወር አቡ ዳቢ ውስጥ ነው። ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ በተከናወነው የአልበርት ፓርክ ሰርኪውት ፉክክር የፌራሪው አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌር አሸናፊ ሲሆን፤ የሬድቡል አሽከርካሪ ካርሎስ ሳይንስ ሁለተኛ እንዲሁም የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል ሦስተኛ ወጥተዋል። ሌላኛውየመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን 4ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW