‘ማህበረሰብን ማብቃት’ ሁሉን አቀፍ መርሃ ግብር በዋሽንግተን ዲሲ
ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2017
ለምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አካላት ተደራሽ የሆነ ሁሉን አቀፍ መርሃ ግብር በዋሽንግተን ዲሲ
በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ለምስራቅ አፍሪካ ማሀበረሰብ አካላት ተደራሽ የሆነ ሁሉን አቀፍ መርሃ ግብር ተካሄደ። ባሳለፍነው ቅዳሜ የተካሄደው ይሄው ዝግጅት፣ የተለየዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሱ ውይይቶችና የልምድ ልውውጦች የተደረጉበት፣ የመጽሃፍት አውደ ርዕይ፣ የንግድ ትረኢት፣ የጤና አቅርቦትና የመዝናኛ ዝግጅትን ያካተተ ነበር። አዘጋጇ ሄለን መስፍን ራዕዩዋ የማህበረሰቡ አባላት መረጃን፣ ድጋፍን እና መነሳሳትን ያገኙ ዘንድ እንደሆነ የገለጸች ሲሆን የዝግጅቱ ታዳሚወችም ከመድረኩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ በዋሽንግተን ዲሲ ኮንቬንሽን ማዕከል ‘ማህበረሰብን ማብቃት’ በሚል መሪ ቃል የተካሄደው መርሃ ግብር ከዲሲ፣ ከቨርጂኒያና ከሜሪላንድ አካባቢወች የመጡ በርካታ ታዳሚወችን አስተናግዷል። ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደው ዝግጅት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሄለን ሾው አዘጋጅ ሄለን መስፍን የተዘጋጀ ሲሆን አጀማመሩም በዝግጅቶቿ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች የበለጠ ለህዝብ የሚደርሱበትን መንገድ ለማመቻቸት በማሰብ እንደሆነ ሄለን ትናገራለች። የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ተከበረ፣ ተመሰገነ።
በዚህም መሰረት በተለያዩ ትልልቅ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ አመራር ላይ የሚገኙና የረጅም አመታት ልምድን ያካበቱ ተጋባዦች ልምድና ተሞክሮወቻቸውን አካፍለዋል። ከዛም መለስ ሲል ከ40 አመት በታች የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና በስራ፣ በሞያና በአመራር ክህሎታቸው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ውጤታማ ግለሰቦች ያለፉበትን መስመር፣ የተሻገሩትን መሰናክል እና የተጠቀሙበትን በጎ አማራጮች ነገ እነሱን መሆን ለሚሹ አጋርተዋል። በተለይ በአሜሪካ ውስጥ መንገዱን ባለማወቅ፣ አልያም የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ባለመገንዘብ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላትና የተለያዩ ተጽዕኖወችን ሰብሮ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ላይ መፍትሄ ጠቋሚ እንደሆነ ሄለን መስፍን ገልጻለች።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ፣ ታዳሚው ከባለሞያወች ጋ በቀጥታ የተወያየባቸው መድረኮችም ነበሩ። አንገብጋቢ በሆነው የስደተኞች ህግ ጉዳይ ላይ የተደረገው ውይይት አንዱ ዝግጅት ነበር። አርቴፊሺአል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) በወደፊ የስራ እድሎች ላይ የሚያመጣው ፈተናና በጎ ሚናም ተዳሷል። በሁሉም የስራ መስክ ላይ ያሉ ሃበሾች በተለይ በፍጥነትና በስፋት እየተቀየረ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር አብረው ለመራመድ ያሏቸውን አማራጮችና ሊያሟሉ የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታወች በተመለከተ በታዳሚወችና በባለሞያወች ውይይት ተደርጓል። የአዕምሮ ሀመም ጉዳይ ሊሰጠው የሚገባውም ትኩረት የውይይቶቹ አንድ አካል ነበር። ታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ በአሌክሳንደሪያ፤ቨርጂኒያ
እነዚሁ መድረኮች ከዚህም ሌላ ያነሷቸው ሃሳቦች እንዳሉ አዘጋጇ ሄለን መስፍን ትገልጻለች ።
ይሄው ዝግጅት ወላጆች ተረጋግተው ውይይቶቹን እንዲካፈሉ፣ ልጆች የሚጫወቱበትና የተለያዩ የፈጠራና ሳይንሳዊ ሙከራወችን የሚያደርጉባት፣ ሃገር በቀል ታሪኮችን የሚያደምጡበት የተከለለ ቦታም ነበረው። ከ14 በላይ ጸሃፍት መጽሃፎቻቸውን ለህዝብ አቅርበዋል። ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ከዲሲና አካባቢዋና ከሌሎችም የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት የንግድ ትርኢትም የዝግጅቱ አካል ነበር። የተለያዩ መሰረታዊ የጤና ምርመራወች፣ለጤና ተስማሚ የሆኑ የምግብ ዝግጅቶች፣ የምክር አገልግሎቶች፣ የግብረሰናይ ድርጅቶች መልዕክቶችም በዚህ ዝግጅት ላይ ተካተው ነበር። ለታዋቂው ድምጻዊና ደራሲ ታምራት አበበ አክብሮት የሰጠው መድረክ በቨርጂኒያ
ያነጋገርኳቸው በዚሁ ማህበረሰብን የማብቃት ዝግጅት ላይ የተገኙ እንግዶች፣ ስለዝግጅቱ የየበኩላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። በዚሁ ዝግጅት የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅት፣ ባህላው ውዝዋዜ፣ የሃገር በቀል ፋሽን ትርዓኢትና የቡና ስነስራዓት ተካተው ነበር።
አበበ ፈለቀ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ