ማሕደረ ዜና፣የሱዳን ዉድመትና የመከፋፈሏ ሥጋት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2017
ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እንደ ጋዛ፣ እንደ ዩክሬን፣ እንደ ኮንጎ ተፋላሚዎች ሁሉ የሱዳን ጦረኞችም ሠላም እንዲያወርዱ፣ ሕዝብ እንዲረዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲጠይቁ፣ ሲማፀኑ፣ ሲፀልዩ ነበር።ዛሬ ሞቱ።የአዲስ አበባ-ኒዮርክ፣ የለንደን-ብራስልስ ዲፕሎማት-ፖለቲከኞች ዛሬም ጥያቄ፣ማሳሰቢያ፣ምክራቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።ፀሎት፣ ተማፅኖ፣ ማሳሰቢያዉ በተደጋጋመ ቁጥር የሱዳን ጄኔራሎች በጦርነት ያወደሟትን ሐገር እሁለት ሊገመሷትያሴሩ፣ ይካሰሱባታል።የአረብ ገዢዎች ይሻኮቱ፣ ይሻሙ፣ ይወቃቀሱባታል።ሕዝቧም ያልቃል፣ ይራባል፣ ይደፈራል።ሱዳን-የታጥቦ ጭቃ ጄኔራሎች፣ የአረብ ጨካኞች ምድር።
የሱዳን ፖለቲከኞች የጦርነት ማግስት ጦርነት «ሱስ»
ሚያዚያ 11፣ 2019 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)።የደቡብ ሱዳን መሪዎች ለዘመናት የነፃነትን ጥቅም ሲሰብኩ፣በፍትሕ፣ እኩልነት ሕልም ሲያማልሉ፣ ሲያጋድሉት የነበረዉን ያን ጎስቋላ፣ደሐ፣ምንድብ ሕዝብን ለሥልጣን ሲሉ እርስበርሱ በሚያፋጁበት በዚያ ዘመን የአዲሲቱ ሐገር ገዢዎች ሰላም እንዲያወርዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ፖለቲከኞቹ እግር ላይ ወድቀዉ ተማፅነዉ ነበር።
ጄኔራል ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና ዶክተር ሪያክ ማቻር ዓለምን ካስደነገጠዉ ተማፅኖዕ ከሁለት ዓመት በኋላ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ገቢር መሆን አለመሆኑ በሚያጠያይቅበት መሐል ፍራንሲስ አዲሲቱን ሐገር ጎብኝተዉ፣ስምምነቱ እንዲፀና ፀልየዉ፣ ተስማሚዎችን መክረዉ ነበር።የካቲት 2023።ሚያዚያ ላይ ሌላዋ ሱዳን ከሌላ ጦርነት ተማገደች።ፀሎት፣ተማፅኖ፣ ጥሪዉም ለሌላ ዘመን ቀጠለ።
«ሱዳን ዉስጥ ዉጊያ የገጠሙት ወገኖች ጠባቸዉን እንዲያቆሙና እንዲደራደሩ በድጋሚ እማፀናለሁ።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ለተፈናቃዮች ርዳታ ለማድረስና ተፋላሚዎች ሰላም እንዲያወርዱ የሚችለዉን ሁሉ እንዲያደርግ እየጠይቃለሁ።»
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጥር 2025።ዛሬ ሞቱ።የደቡብ ሱዳን ገዢዎች ለዳግም ዉጊያ መዛዛታቸዉ ቀጥሏል። የሰሜን ሱዳን ጄኔራሎች ደግሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያወደሟትንና የሚያድሟትን ሐገር እሁለት ለመግመስ እየተራወጡ ነዉ።
የሱዳን ሕዝብ መከራ
እስካሁን ከሞት ያመለጠዉ የሱዳን መከረኛ ሕዝብምካንዱ መጠለያ ጣቢያ ወደ ሌላዉ መንከራት፣ መራብ፣ መሰቃየቱን ቀጥሏል።የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ታጣቂዎች ዱላ፣ቃጠሎ፣ ማሳደድ «ትክት» ያላት እናት «አበሳ ነዉ» አለች በቀደም።
«ችግር ነዉ።ያባርሩሐል።ይደበድቡሐል።ያለሕን ነገር ያቃጥሉብሐል።የተረፈዉን ይወስዱታል።ምንም ነገር አይተዉም።ከዘምዘም መጠለያ ጣቢያ ራቅ ብሎ በሚገኘዉ ሒላት ማራ መንደር ሠፍረን ነበር።ሁለት ወር ቆየን።ከዚያም አባረሩን።ሰሉማ ገባን እዚያም ችግር ነዉ።ተባረርን።ተደበደብን።አቃጠሉብን።ልጆቻችን እና ትናንሽ ማሰሮዎች ብቻ ቀሩን።ምግብ ወይም ሌላ ነገር የለንም።»
በብዙ መቶ ምናልባትም በሺ ከሚቆጠሩ ብጤዎችዋ ጋር አዋላላ ሜዳ ላይ ፈስሰዋል።የቀን ሐሩር፣ የሌት ቁር ይፈራረቅባቸዋል።ጦርነቱ ከቤት ንብረቱ ያፈናቀለዉ ከ13 ሚሊዮን በላይ የሱዳን ዜጋ የሚያዉ መከራ ከዳርፉሯ እናት ቢከፋ እንጂ ያነሰ አይደለም።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ፣ የቻድና የሌሎች ሐገራትን ስደተኞች የሚረዳ፣የሚያስተናግደዉ የሱዳን ሕዝብ ዛሬ የገዛ ገዢዎቹ በለኮሱበት ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠረዉ አልቋል። ከሞት ያመለጠዉ ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷል፣ሴቷ ትደፈራለች።ከ20 ሚሊዮን የሚበልጠዉ ይራባል።
የርዳታ ዘመቻ፣ የሰላም ጥሪ መግለጫም ሠላም አያወርድም
ባለፈዉ ሳምንት የቀድሞዋ የሱዳን ቅኝ ገዢ ብሪታንያ ለንደን ላይ ያስተናገደችዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎች ለጦርነቱ ሰለቦች መርጃ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።ይሁንና የጉባኤዉ አስተናጋጅ የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ላሚይ እንዳሉት የርዳታና የመግለጫ ጋጋታ ለሱዳን ሰላም አልበጀም።
«ትልቁ እንቅፋት የርዳታ ገንዘብ ወይም የተባበሩት መንግስታት መግለጫ አይደለም።የፖለቲካ ፈቃደኝነት እንጂ።በጣም ቀላል ነዉ።ተፋላሚዎች ሰላማዊ ሰዎችን እንዳያጠቁ፣በመላዉ ሐገሪቱ ርዳታ እንዲርስ እንዲፈቅዱና ሰላም እንዲያወርዱ ልናሳምናቸዉ ይገባል።ሥለዚሕ ትዕግስት የተሞላበት ዲፕሎማሲ ያስፈልገናል።»
ተሰናባችዋ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌላ ቤርቦክም ጦርነቱ ካልቆመ ርዳታ ቢጋዝ አይጠቅምም ባይ ናቸዉ።
«ጦርነቱ ከቀጠለ የፈለገዉን ያክል ሰብአዊ ርዳታ ቢሰጥም በቂ አይደለም።የአፍሪቃ ሕብረት እንዳለዉ ለዚሕ ጦርነት ወታደራዊ መፍትሔ ሊኖር አይችልም።ጦርነቱ መቆም አለበት።»
የጳጳሳት፣ መሻኢኮቹ ተማፅኖ፣ የፖለቲካ-ዲፕሎማቶቹ ምክር ማሳሰቢያ ለዉጤት የሚያበቃበት ወይም የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳሉት ጦርነቱ የሚቆምበት ሥልትና ጊዜ በርግጥ ለጊዜዉ አይታወቅም።እዚያዉ ለንደን የተሰበሰቡት ጉባኤተኞች ራሳቸዉ የጋራ አቋም የያዘ መግለጫ ለማዉጣት እንኳን አልተግባቡም።
የጋራ አቋም መያዝ የተሳነዉ የጋራ ጉባኤ፣ የአረቦች ሽኩቻ
ያለመግባባቱ ምክንያቶች ከሩቅ ያሉት በቅኝ ገዢነት ብዙ ጊዜ የሚወቀሱት አዉሮጶች፣ በአረብ ጠላትነት የምትወገዘዉ እስራኤል ወይም አሜሪካኖች አይደሉም።የሱዳንን ሕዝብ «ወንድም» የሚሉት፣ከአብዛኛዉን ሱዳናዊ ጋር ቋንቋ፣ ባሕል፣ ኃይማኖት የሚጋሩት አረቦች እንጂ።የዜና አገልግሎቶች የጉባኤዉን ተሳታፊዎችን ጠቅሰዉ እንደዘገቡት ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በጋራ መግለጫዉ ይዘት ላይ አልተስማሙም።
ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት የሪያድ፣ የአቡዳቢና የካይሮ ገዢዎች ከሊቢያ እስከ ሶሪያ፣ ከኢራቅ እስከ የመን፣ ከሶማሊያ እስከ ኢትዮጵያ በቅርቡ ደግሞ ጋዛ ላይ ለተፈፀመና ለሚፈፀመዉ እልቂት በጋራም በተናጥልም ዶላር የሚዝቀዉ እጃቸዉ በቀጥታም በተዘዋዋሪም አለበት።
ከ2015 ጀምሮ የመንን በጋራ ሲያወድሙ የቆዩት የሶስቱ የአረብ ሐገራት ገዢዎች በስተመጨረሻ ተቃራኒ ኃይላትን በመደገፍ እንደተቃረኑ ሁሉ ሱዳንም ላይ ተቃራኒ ኃይላትን እየደገፉ ነዉ።የፖለቲካ የወታደራዊ ጉዳይ አጥኚዎች እንደሚሉት ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን
የሚመሩትን የሱዳን መከላከያ ጦርና መንግስትን ይረዳሉ።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምዲቲ) የሚያዙትን የፈጥኖ ደራሽ ጦርን ትደግፋለች።
የለንደኑ ጉባኤ የተደረገዉ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ያደረጁት «የሱዳን የሰላምና የአንድነት» ወይም የሱዳን ትዩዩ መንግሥት መመሥረቱ ናይሮቢ ላይ በታወጀ ማግሥት፣ አል ቡርሐን የሚመሩት መንግስት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን በዘር ማጥፋት ወንጀል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍርድ ቤት ላይ በከሰሰ ሳልስት ነበር።ሚዚያ 16።ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመሯቸዉ ቡድናት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የገንዘብ ድጋፍ፣ በኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ አስተናጋጅነት የትይዩ መንግስት መመሥረታቸዉን ግብፅና ሳዑዲ አረቢያ አዉግዘዉታል።
የአፍሪቃ ሕብረትና የአባላቱ ተቃርኖ
የአፍሪቃ ሕብረትም በለንደኑ ጉባኤ ላይ በግልፅ አዉግዞታል።የአፍሪቃ ሕብረት የፖለቲካ፣ የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዮዬ እንዳሉት ሕብረታቸዉ የሱዳንን መከፋፈል አጥብቆ ይቃወማል።
«የሱዳን ተፋላሚዎች በሙሉ ይሕን ጦርነት እንዲያቆሙ የአፍሪቃ ሕብረት ይጠይቃል።እዚሕ የተገኘነዉ ለሱዳን ሰላም አስተዋፅኦ እናደርጋለን ብለን ስለምናምን ነዉ።ግልፅና ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ አለብንም።ሱዳን እንድትቀራመት፣ እንድትከፋፈልና እንድትፈራርስ የአፍሪቃ ሕብረት አይፈቅም።የሱዳን ሪፐብሊክን ሉዓላዊነት፣ የግዛትና የፖለቲካዊ አንድነቷን መጠበቅ አለብን።»
አዉዳሚዉን ጦርነት ግራ ቀኝ ቆመዉ ሲያግፈጠፍጡት ሁለት ዓመት ያስቆጠሩት የሪያድ፣ አቡዳቢ፣ ካይሮ ገዢዎችና ተከታዮቻቸዉ የየሚደግፉት ኃይል ካላሸነፈ ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ ብሎ ማሰብ በርግጥ የዋሕነት ነዉ።ልዩነታቸዉ በከረረበት መሐል በተደረገዉ በለንደኑ ጉባኤ ላይ ተቃራኒ አቋም ቢይዙ በርግጥ ሊያስገርም አይገባም።
የከፋዉ የሪያድ፣አቡዳቢና ካይሮ ገዢዎችን ባሻቸዉ የሚዘዉሩት የዋሽግተን መሪዎች ሶስቱን ታዛዦቻቸዉን ይሁን ሱዳንን ለመሰነጣጠቅ የሚጣጣሩትን ኃይላት «ኃይ» ማለት አለመፍቀዳቸዉ ነዉ።
የአፍሪቃ ሕብረት ኬንያና ግብፅ በግልፅ ሌሎች አባላቱ በድብቅ ወይም በተዘዋዋሪ የመስራች፣ ሰፊ፣ ትልቅ አባሉንን የሱዳንን አንድነትና ሉዓላዊነትን ለአደጋ ያጋለጠዉን ጦርነት በቅርብ ርቀት እንደሚያኖኩረት ያዉቃል።ሕብረቱ የአባላቱን ሴራ እያወቀ የሱዳንን መከፋፈል ማዉገዙ ለቻርተሩ መከበርም፣ ለሱዳን አንድነትም፣ ከሁሉም በላይ በመራብ-መሰደድ መሰቃየት ከዓለም የመጀመሪያዉን ደረጃ ለያዘዉ ለሱዳን ሕዝብም አለመፈየዱ፣ለሩቁ ታዛቢ አሳዛኝ፣ ለአፍሪቃዉያን አስፈሪ፣ ለሱዳኖች ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ነዉ ዚቁ።
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር