ማሕደረ ዜና፣የኢትዮጵያ ጉዞ አቅጣጫዉ ይታወቅ ይሆን?
ሰኞ፣ ነሐሴ 19 2017
ኢትዮጵያ ከሉሲ ግኝት እስከ አክሱም ሐዉልቶች፣ ዋልያን ከመሰሉ-እንስሳት እስከ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ከሶፍ ዑመር ዋሻ-እስከ ሐረር ግንብ፣ ከአድዋ እስከ ካራማራ ድል የሚደርሱ የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ የጀግንነት ታሪኮች ባለቤት መሆንዋ አያከራክርም።የዚያኑ ያክል የርስበርስ ጦርነት፣ የጎሳ ጥቃትና የፖለቲካ ዉዝግብ ዘመናዊቱን ኢትዮጵያ ቁል ዉል እየደፈቋት ነዉ።የድሕነት፣የበሽታና የረሐብ አስከፊነት ከተጠቀሰ የኢትዮጵያዉያን ቁጥር የአሐዞች ማድመቂያ ነዉ።የኑሮ ዉድነት፣ሥራ አጥነት፣ የስደተኞች ብዛትና ሞት ከተዘረዘረ ኢትዮጵያና ዜጎችዋን ማለፍ አይቻልም።ሥርዓተ አልበኝነት፣ እገታና ዘረፋም ከኢትዮጵያ «መለያዎች» እየተካተቱ ነዉ።እና የኢትዮጵያ ጉዞ አቅጣጫ አለዉ ይሆን? ጥቂት ሰሞናዊ አብነት እየጠቀስን ላፍታ እንጠይቅ።
የሕዳሴ ግድብ ትሩፋት-የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መጥፋት
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያስገነባችዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ለዘመኑ ኢትዮጵያዉያዊ እንደ አክሱም ሐዉልቶች ሁሉ ኩራት፣ ለሐገሪቱ ምጣኔ ሐብት ብዙዎች እንደመሰከሩት ጠንካራ መሠረት ነዉ።የኢትዮጵያ የኤሌክሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ በቅርቡ እንዳሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አብዛኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨዉ ከሕዳሴ ግድብ ነዉ።
«ቅድም እንዳልነዉ አብዛኛ ኃይል እያመነጨን የምንገኘዉ ከዚሕ (ከሕዳሴ) ግድብ ነዉ።የምናመጨዉን፣ ኤክስፖርት የምናደርገዉን አብዛኛ ኃይል የምናገኘዉም ከዚሕ ግድብ ነዉ።ሥለዚሕ ይሕ ግድብ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሐገሮችም ከፍተኛ ድጋፍና እገዛ እያደረገ ነዉ።»
ብዙ ባለሙያዎች እንዳሉት ባሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር የለባትም።
«እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ የኃይል ችግር የለም ባሁኑ ጊዜ።» አሉ አቶ ፈ,ቂአሕመድ ነጋሽ ባለዉ መጋቢት ነበር።አቶ ፈቂ አሕመድ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለረጅም ጊዜ የሰሩና የግንባታዉን ሒደት በቅርብ የሚዉቁ የዉሐ ሐብት አሰተዳደር የድንበር ተሻጋሪዎች ወንዞች የሐይድሮ ዲፕሎማሲ ባለሙያ ናቸዉ።ኢትዮጵያ የኃይል ችግር የለባትም።ርዕሠ ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ ግን አብዛኛዉ አካባቢ አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ይቆራረጥበታል።
«የኃይል መቆራረጥ አለ በየቦታዉ።አንዳዴ እንዲያዉ የሆነ ልጅ ማብሪያ ማጥፊያዉ ጋ ቆሞ እያበራ እያጠፋ የሚጫወትበት ሁኔታ አለ እና እንደዚያ ሁኔታ ሁሉ እናያለን።እና ይኸ በአብዛኛዉ የመልካም አስተዳደር እጦት ይመስለኛል።»
የኃይል ችግር የለም፣ ኃይል ግን የለም-ግራ አጋቢ ዕዉነት
ባለፈዉ ሳምንት ምዕራብ ጎንደርየኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም።ምክንያቱ የአካባቢዉ ነዋሪዎችና ባለሙያዎች እንዳሉት የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች በመሰረቃቸዉ ነዉ።የኤሌክትሪክ ኃይል ምሰሶ መሠረቅ ለአብዛኛዉ የአማራ ክልል አካባቢ እንግዳ አይደለም።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የከፍተኛ መስመር ጥገና ኃላፊ በላይ ልጅዓለም እንደሚሉት ከዚሕ በፊትም ተመሳሳይ ችግር ነበር።አሁን ተደገመ።ወደፊት ላለመደገሙም ምንም ዋስትና የለም።
«መሥመሩ አደጋ ላይ ነዉ።አሁን ይሕን ብንሠራዉም ምንም ያን ያክል ጥቅም የለዉም።ስድት ምሶሶዎች ወድቀዉ--ተዘርፈዉ እሱን መልሰን ጠግነን መብራት ሰጥተን ነበር።አሁን ደግሞ ሁለት ምሰሶዎች ጣሉ፣ እዚሕ ጭልጋ አካባቢ ሌሎች አካባቢዎች ላይም ተመሳሳይ ዘረፋ ሥላለ መስመሩ አገልግሎት የመስጠት እድሉ ትንሽ ጠባብ ነዉ።»
የደቡብ ወሎ ነዋሪዎች በተለይም የኮምቦልቻ የፋብሪካ ባለቤቶች እንደሚሉት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሥራ እያስፈታቸዉ፣ወጪ እያበዛባቸዉም ነዉ።
«እንዲያዉ፣ እንዲያዉ ግቢ ሒደት ሠራተኞቹን አሁን የቆሙትን ብታይ።በቃ ምንም እየሠራን አይደለም።ምርት እያለን ዕቃ እያለን፣ መፍጨት ሲያቅተን በመብራት፣ ሠራተኛ ቁጭ ብሎ ደሞዝ እየከፈልን ነዉ።»
ምክንያቱ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሙያ ማነስ፣ የፀጥታ መታወክ፣ ሥርቆት፣የዋጋ ጭማሪ ይሁን ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል። የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኙ የነበሩ አካባቢዎች በጨለማ ከተወጣቱ ግን የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨቱ «አ,ሕያ ሰባ ምን ረባ» እንዳያሰኝ ሊሳስብ ይገባል።የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፍፃሜ-የፈጠረዉ ደስታ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መጥፋት ባስከተለዉ ኪሳራ መጣፋቱ ሲያነጋግር የኢትዮጵያ መንግሥት ለመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ መወሰኑ ተስሟቷል።
የደሞዝ ጭማሪ እፎይታና ሥጋት
ሐኪሞችንና መምሕራንን ሥራ እስከማቆም ለደረሰ ተቃዉሞ ያነሳሳዉ፣ የሠራተኛ ማሕበራት መሪዎችን ለእስር የዳረገዉ፣ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ መልስ ማግኘቱ እሰዬዉ እንጂ ሌላ ሊያስብል አይችልም።ይሁንና ብዙዎች እንደሚሉት የሸቀጦች ዋጋ፣የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርትና የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋን የመሳሰ,ሉ የአገልግሎት ክፍያዎች፣ ግሽበት ዕለት በዕለት እየናሩ የደሞዝ ጭማሪዉ የሠራተኛዉን ኑሮ ማሻሻሉ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።
የተቃዋሚዉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ የደሞዝ ጭማሪ መደረጉን ይደግፋሉ።ጭማሪዉ ግን የሠራተኛዉን ይሁን የሌላዉን ሕብረተሰብ መሠረታዊ ችግር ማቃለል አይችልም ባይ ናቸዉ።
«ጭማሪዉን በመጠኑም ቢሆን እደግፋለሁ።ነገር ግን (ኤኮኖሚዉን) አያረጋጋዉም።ሠራተኛዉንም ደግሞ የበለጠ (---) አሁን ሰሞኑን እምንሰማዉ ምንድነዉ ማስጠንቀቂያ ለነጋዴዎች ሁሉ እየተሰጠ ነዉ።ዋጋ የሚጨምሩ አሉ እየተባለ ማስፈራሪያ ሁሉ ይደርሳል።ኤኮኖሚሕ ላይ ነፃ ገበያ ነዉ ብለሕ አዉጥተሕ፣ ፈቃድ ሰጥተሕ ዋጋዉን ከፍ አደረግሕ፣ ዝቅ አደረግሕ የሚል ቁጥጥር ዉስጥ ከገባሕ የሥርዓቱ ይሕም ሊሆን አይችልም ነዉ----»
ምሥቅልቅሉ ችግር መፍትሔ አለዉ ይሆን?
ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ አንደኛ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ገንባታ-በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌላት፣ ደሞዝ ተጨምሮ የሠራተኛዉ ኑሮ ካልተሻሻለ፣ ብልፅግናዋ እየተወራ-ሥራ አጥነት፣ ሥደትና ድሕነት ካናጠረባት አንድም የሚባለዉ ጥሩ ሁሉ ሐሰት ነዉ።ሁለትም መልስ ያልተሰጠዉ መሠረታዊ ችግር አለ ማለት ነዉ።አቶ ሙላቱ «ፖለቲካ» ይሉታል።
«ፖለቲካዉ ከዘመነ፣ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋዉረዉ፣ ተቀጥረዉ ምርት ሲያመርቱ፣ ምርቱ ወደ ገበያ ሲወጣ ሁሉንም ነገር ይፈታልሐል።የተራበዉን ታበላለሕ፣ የተረፈዉን ወደ ዉጪ ትልካለሕ፣ከዉጪ የምታገኘዉን ለዕድገትሕ ትጠቀምበታለሕ።ቀኑን ሙሉ ሠርተሕ ማታ መጥተዉ የሚዘርፉሕ ከሆነ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሠራተኛዉ ለልማት አምጣ፣ ለመንገድ አምጣ፣ ለሚሊሺያ አምጣ አንዳድ ነገሮች ከመንገድ ያለፉ መዋጮዎችም አሉ።»
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ ወይም ለመንግሥት የወገኑ መገናኛ ዘዴዎች ከሰሞኑ ትላልቅ ርዕሶቻቸዉ አንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ 4ኛ መፅሐፍ ማሳተማቸዉ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንዳሉት «የመደመር መንግስት» የሚል ርዕሥ የተሰጡት መፅሐፋቸዉ ከሚያወሳቸዉ በርካታ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ ከተቀረዉ ዓለም ጋር የተነጠለችበት በጠቅላይ ሚንስትሩ አገላለፅ «ሥብራቶቻችን የትጀመሩ» የሚል ጥያቄ አንስቶ መፍትሔዉን ይተነትናል።
«እኛና የተቀረዉ ዓለም የተላለፍነዉ የትነዉ? ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊ ማሕበራዊ ሥብራቶቻችን የት ጀመሩ? በኛና በዓለም መካከል የተፈጠረዉን ክፍተት እንዴት ልናጠበዉ እንችላለን።ምን ዓይነት መደመራዊ አካሔዶች ብንከተል ሊጠብ እንደሚችል ይተነትናል።»
የጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ መፅሐፍ ጭብጥ፣ የመንግሥታቸዉ ርዕይ ታላቅነት፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠዉ ጥቅም አዲስ አበባ ላይ ሲተነተን፣ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነፃነት፣ በነፃነት የመናገርና የጋዜጠኞች መብቶችን ክፉኛ መደፍለቁን ይዘግቡ ነበር።
ምክንያቱ ቢያንስ ሶስት ጋዜጠኞች እዚያዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ጭብል ባጠለቁ ፀጥታ አስከባሪዎች ጭምር መታሰራቸዉ ወይም አንዳዶች እንደዘገቡት መታገታቸዉ ነበር።ኢትዮጵያ፣ የተቃርኖ ምድር።ጠቅላይ ሚንስትሩ «ሥብራት» ያሉትን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ ምሥቅልቅልን ለማስወገድ ብዙዎች ብዙ መደረግ እንዳለበት በየጊዜዉ ጠቁመዋል።
ጉባኤና የሰላም ጥሪ
የኢትዮጵያ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት እንዳለዉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሐገሪቱንና ሕዝቧን ክፉኛ የጎዳና የሚጎዳዉ ጦርነት፣ ግጭትና ጥቃት ነዉ።የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት አሕመድ ሁሴን እንደነገሩን ጦርነት፣ ግጭትና ጥቃቱን ለማቃለል ምክር ቤቱ ተከታታይ ጉባኤዎችንና የሰላም ጥሪዎችን ያደርጋል።
«ጠንከር ያለ ጥሪ ነዉ።ጥሪዉ ለሁሉም አካላት ነዉ።ጫካም ላሉት ጭምር፣ ጫካ ሊያስገባ የሚችለዉ ቫዮለስ አይጠቅምም ሁሉንም የሚጎዳ ነዉ።እንደ ሐገርም ተጋላጭ ሥለሚያደርገን፣ አሳፋሪም ስለሆነ፣ በድሕነት የሚኖርን ማህበረሰብ፣ በድሕነት የሚኖርን ሐገር በዚሕ ሁኔታ---»
ኢትዮጵያን ከርስበርስ ጦርነት፣ ግጭት፣ ጥቃት፣እገታ፣ ዘረፋና ከምጣኔ ሐብት ድቀት የዶለዉን ሥርየሰደደ ችግር ለማስወገድ ዋናዉ ተዋኝ በርግጥ በመንግሥት ነዉ።ይሁንና በመንግሥት ጥረት (ጥረቱ ካለ) ብቻ ሊወገድ ይችላል ብሎ ማሰብም የዋሕነት ነዉ።አቶ አህመድ እንዳሉት ጫካ የገቡ ኃይላት፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ችግሩን የሚገነዘቡ ምሁራንና የሕብረተሰብ ክፍሎችም የጥረቱ አካል መሆን እለባቸዉ።የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ እንመካከር ብለን ነበር ይላሉ።
«የርስበርስ ጦርነት በተፋፋመበት፣ የዉጪ ምንዛሪ ሰማይ በጠቀሰበት፣ ራቡም፣ ሥራ አጥነቱም በከፋበት፣ማንም ተነስቶ መንገድ ስትሔድ ከትራንስፖርት ላይ አዉርዶ የሚግትበት፣ ገንዘብ የሚጠየቅበት፣ አፈና የበዛበት፣እንግዲሕ አገርን አስተዳድራለሁ፣ ኃላፊነት ተሰጥቶኛል፣ ሕዝብ መርጦኛል የሚለዉ አካል ይኸን ማድረግ አልቻለም---እንመካከርና የሚሻለዉን እናድርግ ነዉ ያልነዉ።»
የሚቻለዉን መወሰን እስካሁን አልተቻለም።ከእንግዲሕ ይቻል ይሆን? ቸር ያሰማን
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ