ማሕደረ ዜና፣ ሒሮሺማ-የመጀመሪያዋ የአዉቶሚክ ቦምብ ሰለባ 80ኛ ዓመት
ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2017
ኮሎኔል ፓዉል ዋርፊልድ ቲቤትስ ትንሹ እንደ ስማቸዉ ቅፅል ሁሉ ትልቁንም ትንሽ ማለት ሳይወዱ አይቅርም።እስከዚያ ዘመን ድረስ ዓለም ዓይቶት የማያዉቀዉን ትልቅ አዉዳሚ ቦምብ ኮሎኔሉና ባልደረቦቻቸዉ ትንሹ ልጅ አሉት-Littel boy።B29 የተባለዉን ግዙፍ አዉሮፕላን ደግሞ ኮሎኔሉ በናታቸዉ ስም ሰየሙት።ኤኖላ ጌይ-ብለዉ።ነሐሴ 06 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኮሎኔል ቲቤትስና ረዳቶቻቸዉ አዉዳዉን ቦምብ የጫነዉ ግዙፍ አዉሮፕላን ከቲኒያን ጦር ሠፈር አስነስተዉ ከ6ሰዓት በረራ በኋላ ሒሮሺማ-ጃፓንን ደረሱ።ከጧት 2:09።ጊዜ አላጠፉም።ቦምብ አስፈንጣሪዉ ሻለቃ ቶማስ ፌሬቤ በ6 ደቂቃ ጣጣዉን ጨርሰዉ አዉዳሚዉን ቦምብ ቁል ቁል ለቀቁት።
ዕልቂት።ዘንድሮ ከነገወዲያ 80ኛ ዓመቱ።በሳልስቱ ናጋሳኪ ተደገመች።ዓለም የመጀመሪያዉን እስካሁን የመጨረሻዉን የአዉቶሚክ ቦምብ ዕልቂ ያስተናገደችበት 80ኛ ዓመት መነሻ፣የኑክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድምድምና ሥጋቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
ዕልቂቱ-የአሜሪካ መንግሥት ዓላማ
«ያየነዉን ማመን በጣም ከባድ ነበር።» አሉ ኮሎኔል ቲቤትስ ኋላ።«አንዱ ባልደረባችን «የፈጣሪ ያለሕ» ሲል ሰማሁት» አከሉ ኮሎኔሉ።እነሱ የሚጥበረብር አስደንጋጭ ብልጭታ፣ ሰቅጣጭ-ድምፅ፣ ሐምራዊ፣ሰማያዊ ነጭ ቀለም ያለዉ ወፍራም፣ እምቅ፣ ጢሱን ሰንጥቀዉ ወደ መጡበት ተፈተለኩ።
መሬት ላይ ለነበሩት ግን የዕልቂት እቶን በር ተበረገደ።አፍንጫ የሚሰነፍጥ ቅርናት፣ጆሮን የሚሰቀጥጥ የሰቆቃ ጩኸት።ከተቀመጡት አስፈንጥሮ የሚያንሳፍፍ ንዝረት፣ ትንፋሽ የሚያሳጣ ወበቅ----ሴፁኮ ቱርሎዉ ያኔ እዚያ ነበሩ።
«በመስኮት ዓይን የሚያሳዉር ሰማያዊ-ነጭ ኃይለኛ ብልጭታ አየሁ።ቀጥሎ እኔ ራሴ ዓየር ላይ የምንሳፈፍ መሰለኝ።የፍንዳታዉ ኃያል ማዕበል ያስፈነጥረን ነበር።ቀስበቀስ ምስሎች ማየት ጀመርኩ።ሰዎች ነበሩ።ግን በፍፁም ሰዉ አይመስሉም።ቆዳና ሥጋቸዉ ተገፍፎ ከአጥታቸዉ ላይ ተንጠጥሏል።አካባቢዉ በደም ርሷል።የተቆራረጠ አካል በየሥፍራዉ ተበትኗል--አንድ ሰዉዬ የአይኖቹን ኳሶች በእጁ ይዞ ለመሔድ ይገዳገዳል---ከዚያ በኋላ የሆነዉን አላዉቅም።»
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪስ ኤስ ትሩማን እንዳሉት ግን መቶ ሺዎችን የፈጀዉ የእልቂት ዶፍ ለዩናይትድ ስቴትስና ለተባባሪዎቿ ታላቅ የታላቅ ድል የመጀመሪያ ምዕራፍ ነዉ።ቦምብ ያነጣጠረዉም ትሩማን እንዳሉት በጃፓን ጦር ኃይል ላይ እንጂ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አይደለም።
«የመጀመሪያዉ የአዉቶሚክ ቦምብ ሒሮሺማ ላይ መጣሉን ዓለም ማወቅ አለበት።በጃፓን ጦር ሠፈር ላይ።ቦምቡን ያፈነዳነዉ የጦርነቱን ሥቃይ ለማሳጠር፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣት አሜሪካዉያንን ሕይወት ለመታደግ ነዉ።ጃፓን የመዋጋት አቅሟ ሙሉ በሙሉ እስኪመታ ድረስ ቦምቡን መጠቀማችንን እንቀጥላለን።»
እንደ እዉነቱ ከሆነ አብዛኛዉ ሟች ቁስለኛ ሰላማዊ ሰዉ ነበር።የአዉዳሚዉ ቦምብ ጥቃት ግን ትሩማን እንደዛቱት ቀጠለ።ሒሮሺማ ሙት ቁስለኞችዋን ቆጥራ ሳታበቃ ናጋሳኪ በሌላ አዉቶሚክ ቦምብ ጋየች።ነሐሴ 9 1945።
ጃፓን እጅ ሰጠኝ፤ የሟቾቹ ቁጥርም አሻቀበ
ናጋሳኪ በነደደች በ6ተኛዉ ቀን ጃፓን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለጠላቶችዋ እጅ ሰጠች።አጥኚዎች እንዳሉት ሒሮሺማ ላይ የተጣለዉ የአዉቶሚክ ቦምብ እስከ 1945 ማብቂያ ድረስ ከ140 ሺሕ እስከ 166 ሺሕ የሚደርስ ሰዉ ፈጅቷል።የኑክሌር ቦምብ እንዲጠፋ የሚታገለዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት ICAN እንደዘገበዉ ናጋሳኪ ላይ የተጣለዉ ቦምብ ሒሮሺማ ላይ ከተጣለዉ የበለጠ ኃይል አለዉ።ከሒሮሺማዉ ዕልቂት የተማረዉ የናጋሳኪ ሕዝብ አንድም አስቀድሞ በመሸሹ ሁለትም ቁጥሩ አነስተኛ በመሆኑ በፍንዳታዉ የተገደለዉ ሕዝብ 74 ሺሕ ነዉ።
ከቦምቦቹ የወጣዉ በካይ ንጥረ ነገር ከቀጥታዉ ፍንዳታ የተረፉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን በካንሰር በሽታ ገድሏል ወይም እስከ ሕይወታቸዉ ፍፃሜ ድረስ የአዕምሮና የአካል በሽተኛ አድርጓቸዋል።የየካባቢዉ የተፈጥሮ ሐብትም እስካሁን ድረስ ወደነበረበት አልተመለሰለሰም።ዓለም ከ80 ዓመት በፊት ከደረሰዉ ጥፋት መማርዋ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነዉ።
እርግጥ ነዉ ከጃፓን እስከ አዉሮጳ፣ ከአሜሪካ እስከ አዉስትሬሊያ የሚገኙ የፀረ ኑክሌር ቡድናት፣ የሰብአዊ መብቶችና የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች ዓለም ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ሥጋት እንድትላቀቅ በየጊዜዉና በየአጋጣሚዉ ይጮሐሉ።ቦምቡን የታጠቁት መንግሥታት ግን ጠላቶቻቸዉን በአስፈሪዉ ቦምብ ለማጥፋት ሲዝቱ ያልታጠቁ ደግሞ ለመታጠቅ እያደቡ ነዉ።
ከዘግናኙ ዕልቂት በኋላ የሚደረገዉ የኑክሌር ቦምብ እሽቅድም
ከዓለም ከፍተኛዉን ቁጥር የኑክሌር ቦምብ የታጠቀችዉ ሩሲያ ምዕራባዉያን መንግሥታት ለዩክሬን የሚሰጡትን ወታደራዊ ድጋፍ ካጠናከሩ፣ በተለይ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ከዩክሬን ጎን ሆኖ ሩሲያን ከወጋ አደገኛዉን ቦምብ እንደምታፈነዳ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
ከደቡብ ኮሪያና ከዩናይትድ ስቴትስ ጦር ጋር የተፋጠጠችዉ ሰሜን ኮሪያ፣ በካሺሚር ጉዳይ የሚወዛገቡት አልፎ አልፎ የሚዋጉት ሕንድና ፓኪስታን፣ በአዉዳሚዉ ቦምብ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት በየጊዜዉ ይዛዛታሉ።እስራኤል የኑኬሌር ቦምብ መታጠቋን በይፋ አላመነችም።አላስተባበለችምም።ቦምቡን መታጠቋ ግን ለድፍን ዓለም የአደባባይ ሚንስጥር ነዉ።
እስራኤልና እስካሁን ድረስ የመጀመሪያዉን የአዉቶሚክ ቦምብ ለዉጊያ ያዋለችዉ ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ ኢራንን ለ12 ቀናት የወጉት የሁለቱ ሐገራት መሪዎች እንዳሉት ቴሕራን እንደነሱ የኑክሌር ቦምብ እንዳይኖራት ለማድረግ ነዉ።ሁለቱ ኑክሌር የታጠቁ ኃያል መንግሥታት የኢራንን ኑክሌር የማምረት አቅም፣ተቋማትና መርሐ-ግብርን ማወደማቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።
«አላማችን የኢራንን ኑክሌር የማብላላት አቅምና የዓለም ቁጥር አንድ ሽብርን ደጋፊ መንግስት የደቀነዉን የኑኬለር ሥጋት ማስወገድ ነበር።ድብደባዎቹ ልዩ ወታደራዊ ድል መሆናቸዉን ዛሬ ለዓለም ማሳወቅ እችላለሁ።የኢራን ቁልፍ የኑክሌር ማብላያ ተቋማት ሙሉ በሙሉና አንድም ሳይቀር ወድመዋል።»
ብለዉ ነበር።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ትራምፕ። ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ተቋም «ሙሉ በሙሉ እና አንድም ሳይቀር» መዉደሙን ለዓለም ካሳወቁ በኋላም ኢራን የኑክሌር ቦምብ ለማምረት ታደባለች የሚል ወቀሳና ዛቻቸዉ መጠናከሩ በርግጥ አነጋጋሪ ነዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቴሕራኖችን በሚያስፈራሩበት መሐል ከቀድሞዉ የሩሲያ ፕሬዝደንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ጋር በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የገጠሙት እንኒኪያ ሰላንቲያንም አንረዉታል።
ኑክሌር መታጠቅ «እብደት ነዉ»-ከአዉቶሚክ ቦምብ የተረፉት ወይዘሮ
ትራምፕ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለተሰነዘረባቸዉ ትችት አፀፋ ማስፈ,ራሪያ ያደረጉት ያን አስፈሪ መዘዘኛ ጦር መሳሪያ ነዉ።ኑክሌር።የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ሁለት የኑክሌር ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ወደ ሩሲያ እንዲጠጉ ባለፈዉ ሳምንት አዘዋል።ከ1945ቱ የአዉቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉትና ዓለም ከኑክሌር ሥጋት እንድትላቀቅ የሚታገሉት ሴፁኮ ቱርሎዉ እንደሚሉት በኑክሌር ቦምብ ለመጫረስ መዛዛት አይደለም ቦምቡን ራሱን መታጠቅ «እብደት ነዉ»
«በዘመናችን፣ ዓለም 16 ሺሕ እንደዚሕ ዓይነት ቦምቦች አሏት።ይሕ እብደት ነዉ።እንዲያዉም ወንጀል ነዉ።ኑክሌር በሚያሰጋበት ዘመን እንደምንኖር ለሰዎች ማሳወቄን አላቆምም።ድምፃችንን ይበልጥ ማሰማት የሚገባንም ለዚሕ ነዉ።ፖለቲከኞቹ አሁንም ተጨማሪ (ቦምብ) እያመረቱ ነዉ።ያኔ አዉዳሚዉ ቦምብ የነበራት አንድ ሐገር ነበረች።አሁን ዘጠኝ ደርሰዋል።ይሕን ሒደት ማቆም አለብን።»
የዓለም መንግሥታት በተለይ ኑክሌር የታጠቁት ግጭት-ጠባቸዉን በድርድር ከማቆም ይልቅ ወደ ጦር ኃይል ዉጊያና ፍጥጫ እያመሩ ነዉ።ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲሕ ደግሞ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ «ሰላማዊ መርሕን» ይከተላሉ የሚባሉት እንደ ጀርመንና ጃፓንን የመሳሰሉ ሐገራት ፖለቲከኞች የወትሮ አቋማቸዉን እየቀየሩ አዉዳሚዉን ቦምብ ማምረትን እንደአማራጭ እያማተሩ፣ሥጋቱንም እያናሩት ነዉ።
የሟች-ቁስለኞች የስቃይ ስሜት መለኪያ አለዉ ይሆን?
በሔሮሺማዉ የአዉቶሚክ ቦምብ የተገደሉት ሰዎች አፅምን የሚመረምሩት የከተማይቱ ዩኒቨርስቲ አጥኚ ሩቡን ካዮ እንደሚሉት ያኔ የደረሰዉን ዕልቂት በቃላት መግለፅ ወይም ሟቾቹን መቁጠር ይቻል ይሆናል።በሟች ቁስለኞቹ ላይ የደረሰዉን ስቃይና ሰቆቃ በትክክል መገንዘብ ግን በርግጥ አይቻልም።
«በአምስቱም የስሜት ሕዋሶቼ ካልተሰማኝ ሰዎች ያኔ የደረሰባቸዉን ሰቆቃ በትክክል መረዳት አልችልም።ምን ዓይነት፣ምን ያክል ሕመም ተስምቷቸዉ ይሆን።እነሱን ከተቀበሩበት የማዉጣት ዕዱል በማግኘቴ የደረሰባቸዉን ስቃይና ሰቆቃ የመረዳት ሐላፊነትም አለብኝ።
የዓለም ፖለቲከኞች የሚያዙት ጦር የሚገድላቸዉ ሰዎችን ስቃይ ሰቆቃ ወይም የሚገደሉ የጦሩ ባልደረቦች የሚደርስባቸዉን ዘግናኝ ስሜት ቢያዩት ወይም ፕሬፌሰር ካዮ እንዳሉት ለመረዳት ቢሞክሩ የዓለም ዕዉነት ይቀየር ይሆን? ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ