1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካእስያ

ማሕደረ ዜና፣ ሕንድና ፓኪስታን የዝንተ ዓለም ጠላቶች

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017

ሌሎች ተንታኞች ወደ ከፋ ግጭት ከመግባት በተለይም ኑክሌር ቦምብ ከመማዘዝ፣ እኩል የታጠቁት «ራሱ ኑክሌሩ አስፈራቸዉ፣ አገዳቸዉም ይላሉ።»ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ሁለቱም ቢያንስ ላሁኑ በርግጥ ዘየዱ።ከጋዛ እስከ ኪቭ እንደምናየዉ ሰለማዊ ሰዉ በመፍጀት፣በምግብ መድሐኒት እቀባ በመቅጣት የሚመጣ «ድል»፣ የሽንፈት-ሽንፈት መሆኑን አስተማሩ።

የህንድና የፓኪስታን ዉጊያ እንዳባባስ የ30 ሐገራት መንግሥታት የዲፕሎማሲ ግፊት አድርገዋል።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ሁለቱ ጠላቶች ተኩስ እንዲያቆሙ ያግባቡት እሳቸዉና ባለሥልጣኖቻቸዉ እንደሆኑ አስታዉቀዋል።
ከግራ ወደ ቀኝ የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ሼሕባዝ ሸሪፍምስል፦ Hindustan Times/Samuel Corum/Ahmad Kamal/picture allianc

ማሕደረ ዜና፣ ሕንድና ፓኪስታን የዝንተ ዓለም ጠላቶች

This browser does not support the audio element.

ሕንድና ፓኪስታን ለአምስት ቀን ተዋጉ፣ ብዙ ፎከሩ፣ ተዛዛቱ፣ አብዛኛ ዓለምን አንጫጩ ና ተኩስ አቆሙ።ቅዳሜ።ብዙዎች እንደሚሉት የኒዉ ደልሒና የኢስላማባድ መሪዎች ዘየዱ።80 ዘመን የዘለቀዉ ጠባቸዉ ግን ደግሞ ለሌላ ግጭት በነበረበት ቀጠለ።የሁለቱ ኑክሌር የታጠቁ ጠላቶች የሰሞኑ ግጭትና ተኩስ አቁም  መነሻ፣ ዘመናት ያስቆጠረዉ ጠብ ምክንያት ማጠቃሻ፣ የቅኝ ገዢዎች ሴራ መድረሻችን ነዉ፣ ላፍት አብራችሁኝ ቆዩ።

«ድል ብዙ ወላጅ አላት፣ ሽንፈት ግን---»

ሁለቱም ድል አደረግን አሉ።የሕንድ ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ሌትናት ጄኔራል ራጂቭ ጋኒ።

«በአዕምሮዬ ምንም ጥርጥር የለኝም።አስደናቂ ድል አስመዝግበናል።በዘጠኝ የአሸባሪዎች መከመቻ ላይ በከፈትነዉ ጥቃት ከአንድ መቶ በላይ አሸባሪዎች ተገድለዋል።»

ሕንድ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ወታደሮች አሏት።መንበሩን ስቶክሆልም ስዊድን ያደረገዉ የግጭት፣ የጦር መሳሪያና የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ጥናት ተቋም SPRI (በእንግሊዝኛ በምሕፃሩ) እንደሚለዉ ሕንድ በ2024 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ብቻ ለጦር መሳሪያ መግዢያ ከ88 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሸምታለች።

ብዙ ጦር መሳሪያ በመሸመት ከዓለም ሁለተኛ ናት።አብዛኛ ጦር መሳሪሪዋን የምትሸምተዉ ከሩሲያ፣ ከፈረንሳይና ከእስራኤል ነዉ።ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጠዉ ጦር ኃይሏ ከ3 ሺሕ በላይ ታንኮች፣ 2 ሺሕ 230 ተዋጊ ጄቶች፣ 293 ተዋጊ መርከብና ጀልባዎች፣ ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች፣ ከሁሉም በላይ 180 ግድም የኑክሌር ቦምቦች ታጥቋል።

ከሕንድ ጋር ሲነፃፀር በቆዳ ሥፋት፣በሕዝብ ብዛት፣ በሐብትም ብዙ የምታንሰዉ ፓኪስታን የጦር መሳሪያ በመሸመት ከሕንድ በሶስት ደረጃ ዝቅ ብላ 5ኛ ናት።አብዛኛ ጦር መሳሪያዋን የምትገዛዉ ከቻይና ነዉ።ለጦር መሳሪያ ብዙ ገንዘብ በማዉጣት ከህንድ 27 ደረጃ ዝቅ ብላ ከዓለም 29ኛ ናት።በ2024 ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ አዉጥታለች።

የፓኪስታን የወታደሮች ብዛት ከሕንድ ጋር ሲነፃፀር በሶስት እጅ ያነሰ ነዉ።1 ሚሊዮን 704 ሺሕ።የታኮቿ ቁጥር ከሕንድ በግማሽ ያክል ያንሳል።1 ሺሕ 800።የተዋጊ ጄቶች ብዛት 1 ሺሕ 400 ግድም።የተዋጊ መርከብና ጀልባ ብዛት 129።ኒኩሌር 170 ግድም።የሰዉ አልባ አዉሮፕላን አይታወቅም።

ሁለቱ ሐገራት ያላቸዉ የኑክሌር ቦምብ ብዛት በግልፅ አይታወቅም።የሁለቱ ሐገራት ባለሥልጣናትን ዋቢ የሚጠቅሱ ምንጮች እንደሚሉት ግን ሕንድ 180 ግድም፣ ፓኪስታን 170 ያክል አስፈሪዉን ቦምብ ታጥቀዋል።

ኢስላማባድም እሳት አለ።የፕሮፓጋዳ አፀፋም በሽ ነዉ።የፓኪስታን ማስታወቂያ ሚንስትር አታቱላሕ ጣሐር እንዳሉት የሐገራቸዉ ጦር በቁጥር፣ በጦር መሳሪያ ዓይነትና ብዛት ብዙ በሚበልጠዉ ጠላቱ ላይ የተቀዳጀዉ ድል ታላቅ ነዉ።

ኢስላማድ-ፓኪስታን ሕንድ ፓኪስታንና ፓኪስታን የምትቆጣጠረዉን የጃሙ ካሽሚር ግዛትንመደብደቧን በመቃወም ፓኪስታን ዉስጥ ከተደረጉ የአደባባይ ሰልፎች አንዱምስል፦ Anjum Naveed/AP Photo/picture alliance

«ሁለቱ ሐገራት የሚቆጣጠሩትን ግዛት በሚለየዉ መስመር ላይ ከ40 እስከ ሐምሳ የሚደርሱ የህንድ ወታደሮችን ገድለናል።ይሕ ብቻ አይደለም የነሱን ብርጌድ ዋና ዕዝ ደምስሰናል።የምወራዉ ሥለ አንድ ጓድ ጦር አይደለም።አንድ ሙሉ ብርጌድን መደምሰስ በመደበኛ ዉጊያ ትልቅ ድል ነዉ።ይሕ ታላቅ ድል ነዉ።»

«ከፊል አሐጉር» የሚባለዉን የእስያ ግዙፍ ግዛት ከ200 ዓመታት በላይ የገዛችዉ ብሪታንያ የዛሬዎቹ ሕንድ፣ ፓኪስታንና ባንግላዱሽ በየዘሙኑ የሚናጩ፣ የሚጋጩ፣ የሚጫረሱበትን ቦምብ ቀብራ ከአካባቢዉ ከወጣች ከ1947 ወዲሕ እዚያ ምድር ሠላም ሰፍኖ አያዉቅም።

የጃሙ ካሽሚር ግድያ መዘዝ፣ የሞዲ ርምጃ ክሽፈት

የሰሞኑ ግጭት የተጫረዉ ሕንድ፣ ፓኪስታንና ቻይና በተቀራመቱት በካሽሚር ግዛት ሰዎች በመገደላቸዉ ሰበብ ነዉ።ሕንድ የምትቆጣጠረዉን የካሽሚር ግዛት ይጎበኙ የነበሩ 25 የሒንዱ እምነት ተካታይ ሐገር ጎብኚዎችና አንድ ሙስሊም አስጎብኚያቸዉ ባለፈዉ ሚያዚያ 22 በታጣቂዎች ተገደሉ።

ግድያዉ፣ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ ከፈጠረዉ ሐዘን-ድንጋጤም በላይ ለሒንዱ አክራሪ ብሔረተኛ ለጠቅላይ ሚንስትር ሼሪ ናሬድራ ሞዲ፣ ለፓርቲያቸዉና ለሚመሩት መንግስትም ታላቅ ሐፍረት ነዉ።ሞዲ «አሸባሪ» የሚሏቸዉን የካሽሚር ሙስሊም ደፈጣ ተዋጊዎችን ለማጥፋት በሚል ከ2019 ጀምሮ የግዛቲቱን የራስ-ገዝ አስተዳደር መብት ገፍፈዋል።

የሞዲ መንግሥት የወሰደዉ ርምጃ ከሐገር ዉስጥ ሕዝባዊ ቁጣ፣ ከዉጪ ተቃዉሞ ገጥሞታል።ሕዝባዊዉ ቁጣዉን ለመደፍለቅ የግዛቲቱን ሕዝብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀፍድዶ ሕዝቡ ለተከታታይ ወራት እንዲይንቀሳቀስ፣ በሥልክና ኢንተርኔት እንዲይገናኝ ዘግቶ፣ በተለይ ፓኪስታንን በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቅ ነበር።

ሚዚያ 22 የተፈፀመዉ ግድያ ከአምስት ዓመታት በላይ የዘለቀዉ ቁጥጥር፣ እመቃና አፈና ለሕንድ ሠላም ያለመጥቀሙ ምልክት-መሆን አለመሆኑ በሚተነተንበት መሐል የሞዲ መንግሥት፣ ተንታኖች «ሥሕተቱን ለመሸፈን» ባሉት ርምጃ የፓኪስታንን እና ፓኪስታን የምትቆጣጠረዉን የካሽሚር ግዛት በሚሳዬል ያነጉደዉ ገባ።

ፓኪስታን ጦርም ለአፀፋ አላመነታም።የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ሼሕባዝ ሸሪፍ ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት ጦራቸዉ ከማክሰኞ ሌሊት እስከ ሮብ ማርፈጃ ብቻ 5 የሕንድ ተዋጊ ጄቶችን መትቶ ጥሏል።ፓኪስታን እራሷን ለመከላከል ያላትን ፅናት አስመስክረናል አሉም።ጠቅላይ ሚንስትሩ።

 «ሕንድ የዋሕ ሰዎችን ኢላማ በማድረግ ጀግንነቷን ለማሳየት የምትሞክር ፈሪ ጠላት ናት።ባለፈዉ ሌሊት ግን በፈጣሪ ፈቃድና ምሕረት ፓኪስታን ተገቢ አፀፋ መስጠት እንደምትችል አስመስክረናል።»

የብሪታንይ የሕንድ ግዛት ይባል የነበረዉ ሰፊ ግዛት በ1947 ለሁለት ተገምሶ  ሁለት ነፃ መንግሥታት ከመሠረቱ ወዲሕ ሕንድና ፓኪስታን ያልተጋጩ፣ ያልተቆራቆሱ፣ ያልተወዛገቡበት ዘመን ጥቂት ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ያደረጉት ዉጊያ ግን በ1999 ከጠሙት ዉጊያ ወዲሕ ከፍተኛዉ ነዉ።

ፓኪስታን እንዳስታወቀችዉ የሕንድ ጦር ፓኪስታንን በሚሳዬል መደብደብ በጀመረበት ወቅት 27 የመንገደኞች አዉሮፕላኖች በፓኪስታን የዓየር ክልል ላይ እየበረሩ ነበር።የተመታ የመንገደኞች አዉሮፕላን ግን የለም።በዉጊያዉ ከሁለቱም ወገን በትንሹ 100 ሰዎች ተገደለዋል።በንብረት ላይ የደረሰዉ ጉዳት መጠን ግን ከፍተኛ ከመባሉ ሌላ በዝርዝር ገና አልታወቀም።

የተኩስ አቁም ሥምምነት መደረጉ ከታወጀ በኋላ ስሪናጋር-ሕንድ የሠፈረዉ ጦርና የከተማይቱ ነዋሪዎች ለርግቦች ጥሬ በመበተን ደስታቸዉን ሲገልጡምስል፦ Mukhtar Khan/AP Photo/picture alliance

የዲፕሎማሲ ርብርብ፣ ትራም ወይስ ኑክሌር

ዉጊያዉ እንዳይቀጥል ከ30 የሚበልጡ መንግሥታት ሁለቱን ባለኑክሌር ጠላቶች ለማግባባት ሞክረዋል።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴያቸዉ እንደፃፉት ግን ሁለቱ መንግሥታት ተኩስ እንዲያቆሙ ያግባባት እሳቸዉና ባለሥልጣኖቻቸዉ ናቸዉ።አንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የኒዉደሊሒ ባለሥልጣናት ከኢስላማድ የሚገጥማቸዉን አፀፋ አቃለዉ ገምተዉት ነበር።

ሌሎች ተንታኞች ደግሞ ሁለቱም ወደ ከፋ ግጭት ከመግባት በተለይም ኑክሌር ቦምብ ከመማዘዝ፣ እኩል የታጠቁት «ራሱ ኑክሌሩ አስፈራቸዉ፣ አገዳቸዉም ይላሉ።»ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የሞተዉ በርግጥ ሞተ፣ የጠፋዉም ጠፋ እና ሁለቱም ቢያንስ ላሁኑ በርግጥ ዘየዱ።ከጋዛ እስከ ኪቭ እንደምናየዉ ሰለማዊ ሰዉ በመፍጀት፣በምግብ መድሐኒት እቀባ በመቅጣት የሚመጣ «ድል»፣ የሽንፈት-ሽንፈት መሆኑን አስተማሩ።ተኩስ አቆሙም።

ኢስላማባድ፣ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ሼሕባዝ ሸሪፍ።ቅዳሜ።

«ለዓለም፣ ለአካባቢዉ ሠላምና መረጋጋት፣ በአካባቢዉ ለሚኖረዉ በሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ ሕይወት ሐላፊነት እንዳለበት መንግስት መልስ ሰጥተናል።ተኩስ እንዲቆም በቅን መንፈስ የቀረበዉን ሐሳብ (ተቀብለናል)»

የሕንድ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቪክራም ሚስሪም መንግስታቸዉ ተኩስ ለማቆም መስማማቱን አረጋገጡ።

«የሁለቱ ሐገራት (የጦር አዛዦች) ሁሉንም አይነት ተኩስና ወታደራዊ ርምጃዎችን ለማቆም ተስማምተዋል።በሕንድ የሰዓት አቆጣጠር ከዛሬ ከ17:00 ሰዓት ጀምሮ በምድር፣በዓየርና በባሕር የሚደረጉ ወታደራዊ ርምጃዎች ይቆማሉ።ይመግባባት ገቢር እንዲሆን ለሁለቱም ወገኖች መመሪያ ተሰጥቷል።»

ሰላም ለማታዉቀዉ ዓለም ላፍታም ቢሆን እፎታ ነዉ።ለሕንድና ፓኪስታን አዋሳኝ ደንበር ነዋሪዎች ደግሞ ደስታ።ዳር ይዘልቅ ይሆን?

በጊዜዉ የሚፈነዳዉ «ቦምብ» ቀባሪዎች

በ1579 ራልፍ ፊች፣ በ1594 ጀምስ ላስነር የተባሉ የብሪታንያ ሐገር አሳሾች ያንን ምድር እስከረገጡበት ጊዜ ድረስ ሒንዲዎች፣ መንጎሎች፣ ቻይኖች፣ ፋርሶች፣ ሙስሊሞች ፖርቱጋሎችም ተፈራርቀዉበታል።ሁለቱ የብሪታንያ ሐገር አሳሾች የዚያን አሐጉር አከል ግዛት የቅመም፣ የዱር እንስሳ፣ የተራራ ክምርና  የማዕድን ሐብት ለብሪታኒያዎች ካስተዋወቁ በኋላ አንዴ የምሥራቅ ሕንድ ኩባንያ ሌላ ጊዜ ደግሞ የታላቅዋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛት እየተባለ የህዝቡ ነባር አስተዳደር፣ ነፃነት፣ ሕይወት ጭምር ተደፍልቋል።

የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች የህዝቡን ሐብት ለመመዝበርና የነፃነት ጥያቄዉን ለማፈን ሲመቻቸዉ በጎሳ፣ ካልሆነ በኃይማኖት፣ እየከፋፈሉ እርስበርስ አፋጅተዉታል።ጥናቶች እንደጠቆሙት ከ1880 እስከ 1920 በነበሩት 40 ዓመታት ብቻ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አልቋል።

ሕንድና ፓኪስታን የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረጋቸዉ የተደሰተዉ የፓኪስታን ሕዝብ ደስታዉን ለመግለጥ የጣፋጭ ስጦታ ሲለዋወጥምስል፦ SHAHID SAEED MIRZA/AFP

በ1947 ብሪታንያ ከዚያ ግዛትለቅቃ ለመዉጣት ስትወስን ለዘመናት ኮትኩታ ያሳደገችዉ የሒንዱና የእስልምና እምነት ተከታዮች ጠብ የሁለት ምናልባትም የሶስትና የአራት መንግስታት የዘመናት ጠብ መነሻ የሚሆንበትን ሴራ ተክላ ነበር።በጥቅሉ ሕንድ ተብሎ የሚጠራዉ ሰፊ ግዛት የመጨረሻ ገዢ በነበሩት በሎርድ ሉዊስ ማዉንትባተንም አማካይነት ግዛቱ ሕንድና ፓኪስታን በሚል ለሁለት ተገመሰ።

ክፍፍሉ ጠቀመ ወይስ ጎዳ

የሒንዱ፣የሲክና የቡዳሐ አማኞች በብዛት የሚኖሩበት ግዛት ሕንድ ሲባል፣ ሙስሊሞች የሚበዙበት የዛሬዎቹ ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ግዛቶች ደግሞ ፓኪስታን ሆኑ።ክፍፍሉ ሲደረግ ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩበት የጃሙ ካሽሚር ካሽሚር ግዛት ግን የሒንዱ እምነት የሚከተሉት የግዛቱ አገረ-ገዢ እንደጠየቁት ነፃ መንግስትም ሳይሆን፣ ከፓኪስታንና ሕንድም ሳይጠቃለል  ለወደፊቱ ግጭት እንዲመች ተንጠልጥሎ ቀረ።

ወዲያዉ ያቺ ተራራማ ዉብ ምድር ጃሙ ካሽሚር በደም አበላ ትጨቀይ ያዘች።አገረገዢ ሐሪ ሲንጌሕም በፓኪስታን የሚታገዙ ሙስሊሞች ወጉኝ በሚል ሰበብ የግዛቱን አብዛኛ ደቡባዊ ክፍል ከኒዊደልሒ አስተዳደር ጋር ቀየጡት።30 በመቶ የሚሆነዉ ከፓኪስታን እጅ ገባ።ከ1959 ጀምሮ ደግሞ ከግዛቱ 15 በመቶዉን ቻይና ተቆጣጥራዋለች።

እስከ 1971 ድረስ ምሥራቅ ፓኪስታን ይባል የነበረዉ ግዛት ተወላጆች ከፓኪስታን ተገንጥለዉ ባንግላዴሽ በሚል ሥም የራሳቸዉን ነፃ መንግስት አዉጀዉ አነሰም በዛ ከጎረቤቶቻቸዉ ጋር በሰላም ይኖራሉ ይኖራሉ።የካሽሚር ይገባኛል ጥያቄ ግን ሕንድና ፓኪስታንን በየጊዜዉ፣ ሕንድና ቻይናን አልፎ አልፎ እንዳጋጨ እነሆ 78ኛ ዓመቱን ደፈነ።ከእንግዲስ?

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW