1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ማሕደረ ዜና፣ መካከለኛዉ ምሥራቅ ደም ጠጥቶ ደም የሚጠማዉ ምድር

ሰኞ፣ መስከረም 20 2017

የአረብ መሪዎች ይርመጠመጣሉ፣ ኢራን ትፎክራለች።ሐማስ ይሽሎኮሎካል፣ ሒዝቡላሕና ሑቲዎች ይፍጨረጨራሉ።ፍልስጤም ያልቃል።እስራኤል፣ ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ እንዳሉት በረጅም ምህረት የለሽ እጇ፣ ሲሻት ጋዛን፣ ሲያሰኛት ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን፣ ሲፈልጋት ሊባኖስን፣ ካሰኛት ሁዴይዳሕን፣ ቴሕራንን፣ ደማስቆን ታጋያለች

የሒዝቡላሕ መሪ የሐሰን ነስረላሕን መገደል ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ፍልስጤና በሌሎችም ሐገራት በብዙ uIሕ የሚቆጠር ሕዝብ ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉሞታል
የሒዝቡላሕ መሪ የሐሰን ነስረላሕን መገደል በመቃወም ኢራን ርዕሰ ከተማ ቴሕራን ዉስጥ ከተደረገዉ ያደባባይ ሰልፍ በከፊልምስል Majid Asgaripour/WANA/REUTERS

ማሕደረ ዜና፣ መካከለኛዉ ምሥራቅ ደም ጠጥቶ ደም የሚጠማዉ ምድር

This browser does not support the audio element.

300924

መስከረም 27፣ 2024 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አርብ።ኒዮርክ።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመንግሥታቸዉን ጥንካሬና ዕቅድ አስታወቁ።ድፍን መካከለኛዉ ምሥራቅን አስጠነቀቁም።

«የእስራኤል ረጅም እጅ የማይደርስበት ሥፍራ ኢራን ዉስጥ የለም።ይሕ ለመላዉ መካከለኛዉ ምሥራቅም ዕዉነት ነዉ።»

አላበሉም።

ከዩናይትድ ስቴትስና ከምዕራብ አዉሮጳ ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚያንቆረቁሩለት የእስራኤል ጦር ጋዛን አዉድሟል።ቴሕራን፣ደማስቆ፣ቤይሩት፣ሑዴይዳ ዉስጥ «ጠላት» የሚላቸዉን ፖለቲከኞች፣ ጄኔራሎች፤ ተራ ዜጎችን ጭምር ገድሏል።አርብ ደግሞ የኔታንያሁ ማስጠንቀቂያ ከኒዮርክ በተሰማ በሰዓታት ልዩነት የእስራኤል ረጅም እጅ ቤይሩት ላይ ሌላ ግዳይ ጣለ።ሰይድ ሐሰን ነስረላሕን ገደለ።ለእስራኤል፣ ለዓለም ሠላም ይበጅ ይሆን?ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የወዳጆቹ ጠላትነት፣የሒዝቡላሕ ድርጅትነት

እስራኤል እንደሐገር ከተመሰረተች ከ1948 ጀምሮ ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት ሁሉ ጠንካራ ድጋፍ ስትሰጣት የነበረችዉ ኢራን ነበረች።በተለይ በ1973ቱ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት ወቅት አረቦች በመቱት የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ ምክንያት እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቻቸዉ በነዳጅ ጥማት ሲያርሩ የደረሰችላቸዉ ኢራን ነበረች።በ1979 የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የቴሕራን ቤተ መንግሥትን ሲቆጣጠሩ ግን የቴሕራን ቴል አቪቭ-ዋሽግተኖች ወዳጅነት ፈረሰ።

የእስራኤል ጦር ሊባኖስ ዉስጥ የሸመቁ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችን ለማጥፋት በ1982 ደቡብ ሊባኖስን ሲወርር ደግሞ የሁለቱ የጥንት ወዳጆች ግንኙነት ወደ ጠላትነት ተቀየረ።የሊባኖሱ የሺዓ ሚሊሺያ ኃይልም በኢራን ድጋፍ ተመሠረተ።ሒዝቡላሕ-አሉት ስሙንም መሥራቾቹ-የፈጣሪ ፓርቲ እንደማለት ነዉ።ቡድኑ በመተመሠረተ ባመቱ ቤይሩት የሚገኘዉን የዩናይትድ ስቴትስን ጦር ሠፈር በቦምብ አጋየዉ።241 የአሜሪካ ወታደሮችን ገደለ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ በ79ኛዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባለፈዉ አርብ ንግግር ሲያደርጉምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

በ1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የኢራን-ኢራቅ ጦርነት፣ የሊባኖስም የርስበርስ ጦርነት ሲቆም የድርጅቱ የመጀመሪያ መሪ ሱብሒ አል-ቱፋይሊ የቴሕራኖችን ጫና በመቃወማቸዉ ከሥልጣን ተወገዱ።እስከዚያ ጊዜ ድረስ የሒዝቡላሕ ጦር አዛዥ የነበሩት አባስ አል ሙሳዊ  የዋና ፀሐፊነት ሥልጣን ያዙ።1991

አል ሙሳዊ ከ1986 ጀምሮ የእስራኤል ወታደሮችን አስገድለዋል፣ ወይም አሳግተዋል በማለት የምትወነጅላቸዉ እስራኤል አንድም ለማገት ካልሆነ ለማጥፋት ታድናቸዉ ነበር።ጥቅምት 26፣1992 አሜሪካ ሠራሹ የእስራኤል  ሐፓቺ ሔሊኮብተር ደቡብ ሊባኖስ ዉስጥ ተከታትለዉ ይጓዙ የነበሩ ሶስት መኪኖችን በሚሳዬል አጋየ።አል ሙሳዊ፣ ባለቤታቸዉ፣የአምስት አመት ወንድ ልጃቸዉና ሌሎች አራት ሰዎች ተገደሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ይትስሐቅ ሻሚር ይመሩት የነበረዉ የእስራኤል መንግሥት ጠላቱን በመግደሉ ለቴል አቪቭ፣ ዋሽግተኖች ታላቅ ደስታ፣ለአዉሮጳ-አረብ ወዳጆቻቸዉ እፎይታ፣ ለቴሕራን ደማስቆዎች ባንፃሩ በርግጥ ሽንፈት ብጤ ነበር።የድል-ሽንፈቱ ፌስታ ሐፍረት ስሜት 1 ወር አልቆየም።

መጋቢት 17፣1992 ቦኒስ አይሪስ-አርጀቲና የሚገኘዉ የእስራኤል ኤምባሲ ሕንፃ በቦም ጋየ።29 ሰዎች ተገደሉ።ኤምባሲዉን ያጋየዉ ኢስላሚክ ጅሐድ የተባለዉ የሊባኖስ የሺዓ ቡድን ጥቃቱን ያደረሰዉ የአል ሙሳዊን በተለይም የአምስት ዓመት ሕፃን ልጃቸዉን ደም ለመበቀል እንደሆነ አስታወቀ።

የእስራኤል-ሒዝቡላሕ፣የየወዳጆቻቸዉ ዉጊያ፣መገዳደል፣መበቃቀልም ቀጠለ።ሒዝቡላሕ ልክ እንደ ሐማስ፣ እንደ ኢስላሚክ ጀሐድ፣ እስራኤልና አሜሪካኖችን እንደሚቃወሙ እንደ ብዙ ደፈጣ ተዋጊዎች ቡድናት ሁሉ ለእስራኤል፣ ለዩናይትድ ስቴትስ፣ለአዉሮጳ ሕብረት፣ ለብሪታንያና ለተባባሪዎቻቸዉ አሸባሪ ቡድን ነዉ።የዚሕ ቡድን መሪ ባለፈዉ አርብ መገደልም ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ እንዳሉት ለእስራኤልና ለወዳጆችዋ ታላቅ ድል ነዉ።

«የእስራኤል መንግሥት ዋናዉን ገዳይ ሐሰን ነስረላሕን ትናንት ገድሏል።ቁጥር የለሽ እስራኤላዉያን፣ በመቶ የሚቆጠሩ አሜሪካዉያንና በደርዘን የሚቆጠሩ የፈረንሳይ ዜጎች ለመገደላቸዉ ተጠያቂ ከሆነዉ ጋር ሒሳብ አወራርደናል።»

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም የሐሰን የነስረላሕን መገደል «ለብዙ ሰለቦቹ ፍትሐዊ ርምጃ» ብለዉታል።

ይሁንና ሐሰን ነስረላሕም ሆኑ፣ የሚመሩት ቡድን ሒዝቡላሕ ለኢራን፣ ለሶሪያ፣ ለሊባኖስ፣ ለኢራቅ፣ሌላ ቀርቶ ለፓኪስታን በተለይ ለሺዓ ሐራጥቃ ተከታዮች፣ ለፍልስጤም ሱኒዎችም ጭምር የነፃነት ተፋላሚ ነዉ።የሐሰን ነስረላሕ መገደል ከተረጋገጠ ካለፈዉ ቅዳሜ ጀምሮ ከባስራ እስከ ነጃፍ፣ ከቴሕራን እስከ ደማስቆ፣ ከካራቺ እስከ ሰነዓ የተደረገዉ ሐዘን፣ ያደባባይ ሰልፍና የብቀላ ዛቻም ይኽንኑ መስካሪ ነዉ።

     

አል ሙሳዊ በ1992 ሲገደሉ የቡድኑን የዋና ፀሐፊነት ሥልጣን የያዙት ሐሰን ነስረላሕ ያን ቡድን ከተራ ደፈጣ ተዋጊነት ወደ ጠንካራ የፖለቲካ-ጦር ኃይል ድርጅትነት አሳድገዉታል።ሒዝቦላሕ ብዙዎች እንደሚሉት ከሊባኖስ መንግሥት የበለጠ ፖለቲካዊ መዋቅር፣ ከሊባኖስ ጦር ኃይል የጠነከረ ተዋጊ ኃይል አለዉ።

ባለፈዉ አርብ እስራኤል የገደለቻቸዉ የሒዝቡላሕ ዋና ፀሐፊ ሰይድ ሐሰን ነስረላሕ (ከመሐል)ምስል Dohrn Michael/ABACA/picture alliance

ከ20 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ የሚገመተዉ ጦሩ ከ40 ኪሎ ሜትር እስከ 700 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ ያጭርና የረጅም ርቀት ሮኬቶች፣ ሚሳዬሎች፣ ፀረ ታንክ፣ ፀረ-መርከብ ሚሳዬሎች በድምሩ 150 ሺሕ አወንጫፊዎች ታጥቋል።140 ሺሕ ሞርታሮች፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች አሉት።

በ1992 የያኔዎቹ የእስራኤል የፖለቲካና የጦር መሪዎች የሒዝቡላሕ ዋና ፀሐፊ አባስ አል ሙሳዊ ይገደሉ ወይስ ይታገቱ የሚል «ክርክር ገጥመዉ ነበር« አሉ-ሚስጥሩን የሚያዉቁ።የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ኤሁድ ባራክ የሒዝቡላሕ መሪ እንዲገደሉ አጥብቀዉ ሲከራከሩ፣ ተቃዋሚዎቻቸዉ ሒዝቡላሕ «የአንድ ሰዉ ትርዒት አይደለም» በማለት ተሟግተዉ ነበር።የተቀበላቸዉ የለም።

የ11 ወሩ እልቂት፣ ጥቃትና ድል

ከ32 ዓመት በኋላ ዘንድሮ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የነስረላሕን መገደል የአንድ ሰዉ መገደል አላደረጉትም ለእስራኤል  ታላቅ ድል፣ ታሪካዊ እመርታም አሉት እንጂ

«የእስራኤል ዜጎች ሆይ!!! እኒሕ ታላቅ ቀናት ናቸዉ።ከታላቅ ታሪካዊ እጥፋት ላይ ደርሰናል።ከዓመት በፊት ጥቅምት 7 ጠላቶቻችን አጠቁን።እስራኤልም ልትጠፋ ተቃርባለች ብለዉ አስበዉ ነበር።ከዓመት በኋላ ጠላቶቻችንን በዉድመት ላይ ዉድመት እያደረስን፣ ድል በድል (ስንረማመድ) ተስፋቸዉ መደብዘዙን ተገንዝበዉታል።እስራኤል እያንሰራራች ነዉ።እያሸነፍን ነዉ።ጠላቶቻችንን ማጥቃታችንን እንቀጥላል።ዜጎቻችንን ወደ ወደየቤታቸዉ እንመልሳለን።ታጋቾቻችንን በሙሉ እናስለቅቃለን።»

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ አምና መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤልን አጥቅቶ ወደ 1200 የሚሆኑ የእስራኤልና የተለያዩ ሐገራት ዜጎችን ገድሏል።በመቶ የሚቆጠሩ አግቷል።

ጥቃቱን ለመበቀል እስራኤል ጋዛ ሰርጥ ላይ በከፈተችዉ መጠነ ሠፊ ወታደራዊ ዘመቻ 42 ሺሕ ፍልስጤማዉያንን ገድላለች። ጋዛንም ኔታንያሁ እንዳሉት አዉድማለች።ሲቪሎችን አዳኝ የሚባሉት የጋዛ ነብስ አንድን ሰራተኞች እንደሚሉት ጋዛ የሰዉ የሚገደልባት ብቻ አይደለችም።የቅዠት ምድር ጭምርም እንጂ።

«በየስፍራዉ የተሰዉትን ሰዎች እናሸታለን።ስንተኛ፣ ስንበላ፣ ሁል ጊዜም የተበጣጠሱ ሰዉነት ክፍሎችን ሽታ እናሸታለን።ደም እናያለን።ምንም ነገር ባይኖር እንኳ መመገብ እንፈልግም።።»

ጋዛን ያወደመዉ፣ ሊባኖስን አንዴ በመገናኛ መሳሪዎች ፈንጂ፣ ሌላ ጊዜ በሚሳዬልና ቦምብ የሚያሸብረዉ የእስራኤል ጥቃት ቀጥሏል።የሊባኖስ ባለሥልጣናት እንዳሉት እስከ ትናንት ድረስ 1000 ሰዎች ተገድለዋል።ከ600 በላይ ቆስለዋል።

ዛሬ ደግሞ የእስራኤል ጦር ሊባኖስ ዉስጥ የሐማስ፣ ሕዝባዊ ግንባር ለፍልስጤም ነፃነት (PFPL) መሪዎችን፣ የሊባኖስን ወታደርና በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።

ምዕራባዉያን መንግሥታት ደግሞ ዜጎቻቸዉ ከሊባኖስ እንዲወጡ እያሳሰቡ ነዉ።ዘገቦች እንደጠቆሙት የኢትዮጵያ፣የሱዳን፣ የፊሊፒንስና የሌሎች ደሐ ሐገራት ዜጎች መዉጪያ መግቢያ አጥተዉ መጪዉን እየጠበቁ ነዉ።

የሊቢኖስ ዳግማዊት ጋዛነት፣ የከፋ ጦርነት ሥጋት

የፖለቲካና የወታደራዊ ጉዳይ አዋቂዎች እንደሚሉት የእስራኤል የኃይል እርምጃ ሊባኖስ ዳግማዊት ጋዛ እንዳያደርግ፣ መካከለኛዉ ምሥራቅን በየለየለት ጦርነት እንዳያወድም ያሠጋል።ለእስራኤል ከዘመናይ ጦር መሳሪያ እስከ ጠንካራ ዲፕሎማሲ፣ ከቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር እስከ ጥብቅ ስለላ ሁሉን የምታደርግላት ዩናይትድ ስቴትስ አስጊዉን ጦርነት ለማስወገድ እስካሁን ሁነኛ ርምጃ አልወሰደችም መዉሰድ አልፈለገችም ወይም አልቻለችም።

ነገር ስዉጥ የሚላቸዉ የ81 ዓመቱ አዛዉንት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ግን ሙሉ ጦርነት መከፈት የለበትም ይላሉ።

«(ሙሉ ጦርነት) ሊወገድ ይገባል።በእዉነት ልናስወግደዉ ይገባል።መዉጣት የፈለጉ የኤምባሲዎቻችን ሰራተኞች ቤተሰቦች እንዲወጡ የጥንቃቄ ርምጃ ወስደናል።ገና እዚያ አልደረስንም ግን ከፈረንሳዮችና ከሌሎች ጋር አበክረን እየጣርን ነዉ።»

የወታደራዊ ስልት ጉዳይ አጥኚ ፓዉል ሙርክራፍት እንደሚሉት ግን የነስረላሕ መገደል፣ የእስራኤል ገደብ የለሽ ጥቃት መቀጠል፣ የአሜሪካ ዳተኝነት፣የሊባኖስ ዉድመት ወትሮም በግጭት፣ ጦርነት የሚታመሠዉን አካባቢ ካዲስና ሁሉንን ከሚያነካካ  ጦርነት ሊዘፍቀዉ ይችላል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አዉሮፕላን ከመሳፈራቸዉ በፊት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ መልስ ሲሰጡምስል Manuel Balce Ceneta/AP/picture alliance

«ይሕ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የታላቅ ግጭት ማቀጣጠያ ሊሆን ይችላል።ይሕ ምን ማለት ነዉ? በምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዳርቻ ሶስተኛዉ ኢንቲፋዳ ሊቀሰቀስ፣ ተጨማሪ ዉጊያ ሊጫር ይችላል።ሳዑዲዎች ከዚሕ ቀደም የነሱ ቬትናም በሆነዉ የየመን ጦርነት እንደገና ከሁቲዎች ጋር ይገጥሙ ይሆናል።ሶሪያዎች ወደ ጎላን ኮረብታ ሊሔዱ ይችላሉ።ይሕ በጣም ከፍተኛ፣ ከፍተኛ ጦርነት ሊሆን ይችላል።»

የአረብ መሪዎች ይርመጠመጣሉ፣ ኢራን ትፎክራለች።ሐማስ ይሽሎኮሎካል፣ ሒዝቡላሕና ሑቲዎች ይፍጨረጨራሉ።ፍልስጤም ያልቃል።እስራኤል፣ ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ እንዳሉት በረጅም ምህረት የለሽ እጇ፣ ሲሻት ጋዛን፣ ሲያሰኛት ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን፣ ሲፈልጋት ሊባኖስን፣ ካሰኛት ሁዴይዳሕን፣ ቴሕራንን፣ ደማስቆን ታጋያለች።መካከለኛዉ ምሥራቅ።ምን ይከተል ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW