ማሕደረ ዜና፣ መፈንቀለ መንግስትና አፀፋዉ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 26 2015
የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች «ሁለተኛዉ የሩሲያና የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ» ለተባለዉ ስብሰባ ሳይንት ፒተርስበርግ-ሩሲያ ዉስጥ ሲታደሙ የኒዠሩ ፕሬዝደንት መሐመድ ባዙም በልዩ ጠባቂዎቻቸዉ ታገቱ።መፈንቅለ መንግስት።ሮብ።ሚያዚያ 2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጦር ሜዳ የተገደሉትን ያባታቸዉን ሥልጣን በመፈንቅለ መንግስት የወረሱት የቻዱ ጄኔራል መሐሜት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ የኒዤርን ቀዉስ ለማስወገድ ባሉት ጉብኝት አዲሶቹን የኒዠር ወታደራዊ ገዢዎች ኒያሚ ዉስጥ ሲያነጋግሩ ትናንት የምዕራብ አፍሪቃ መሪዎች አቡጃ-ናጄሪያ ዉስጥ ተሰበሰቡ።በቅርብ ዓመታት ማሊ፣ ጊኒና ቡርኪና ፋሶ በመፈንቅለ መንግስት ሲተራመሱ ከዉግዘት፣ድርድር ባለፍ ምንም ያላሉት የምዕራብ አፍሪቃ መሪዎች የኒዠሩን መፈንቅለ መንግስት በጦር ኃይል ጭምር ሊቀለብሱ ዛቱ።የኒዠር መፈንቅለ መንግስት መነሻ፣ ሌሎች መፈንቅለ መንግሥታት ማጣቃሻ፣ የዉጪ መንግስታት ተቃራኒ አፀፋ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
ከፓትሪስ ኢሜሪይ ሉሙምባ እስከ ቶማስ ኢሲዶሬ ኖኤል ሳንካራ የነበሩ በርካታ ተወዳጅ የአፍሪቃ ብሔረተኛ መሪዎች በየዘመኑ ተገድለዋል።ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤና መሰሎቻቸዉ የነፃነት ታጋዮች በየትግል ዘመናቸዉ እየታሰሩ ተሰቃይተዋል።አፍሪቃዉያኑን ፖለቲከኞች ያስገደሉ፣ያሳሰሩ፣ ያሰቃዩት ወገኖች ማንነት፣ ከማስገደል-ማሳሰር ሴራቸዉ ምክንያት ጋር ከብዙ ጊዜ በላይ ብዙ ተብሏል።
ሚያዚያ 2011 የፈረንሳይ ጦር የቀድሞዉን የአይቮሪኮስት (ኮትዲቫር) ፕሬዝደንት ሎራ ባግቦን መኖሪያ ቤት ከብቦ ሰዉዬዉን ለጠላቶቻቸዉ ሲያስረክብ «አበጀሕ» ነዉ የተባለዉ።የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በቅርቡ በትዊተር በተሰራጨ ንግግራቸዉ እንዳሉት በ2011 ለተቀሰቀሰዉ ለሊቢያ ፖለቲካዊ ቀዉስ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የአፍሪቃ ሕብረት 6 የአፍሪቃ መሪዎችን ይወክላል።
ሙሴቬኒ እንደተረኩት መሪዎቹ ከንዋክሾት-ሞሪታንያ ወደ ትሪፖሊ ለመጓዝ አዉሮፕላን ይሳፈራሉ።ሊቢያን የሚደድበዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ አዛቾች መሪዎቹን ተመለሱ አሏቸዉ።
«የአፍሪቃ ፕሬዝደንቶች፣ ለአፍሪቃ ተልዕኮ፣ አፍሪቃ ምድር ላይ ሊቢያ ዉስጥ እንዲያርፉ አልፈቀደላቸዉም።»
ትዕዛዝ አከበሩ።ምናልባት ሕይወታቸዉን አዳኑ።የአፍሪቃ ሕብረት ተልዕኮ ከሸፈ።የሊቢያ የረጅም ዘመን ገዢ ተገደሉ።ዑመር ሙክታር የሚያስተምሩበትን መድ-ሉሕ ጥለዉ ጠመጃ ታጥቀዉ ለነፃነቷ የተፋለሙላት፣ ያ ቺ ሐብታም፣ ሰፊ፣ ስልታዊ አፍሪቃ-አረባዊት ሐገር ፈረሰች።
ዑመር ሙክታር ወይም ኢትዮጵያዊዉ አቡነ ጴጥሮስ እንደ ዘመኑ የአፍሪቃ መሪዎች ትዕዛዝ አክብረዉ ለኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ገብረዉ ቢሆን ኖሮ በየአደባባዩ ተሰቅለዉ ባልተገደሉ ነበር።እነ ፓትሪስ ሉሙምባ እንደነ ሙሴ ቬኒ የተባሉትን አድርገዉ ቢሆን ኖሮ ታሪካቸዉን (አፈሩበትም ኮሩበት) መተረክ በቻሉ ነበር።
ትናንት አቡጃ ናጄሪያ ዉስጥ የተሰበሰቡት የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ (ECOWAS በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) አባል ሐገራት መሪዎች ካለፈዉ ሮብ ጀምሮ ጄኔራል ዑመር ወይም አብዱረሕማን ችያኒ በሚመሯት በኒዠር ላይ ያልጣሉት ማዕቀብ የለም።
«ኒዠርን ከኤኮዋስ አባል ሐገራት ጋር የሚያገናኙ ድንበሮችን መዝጋት።ከና ወደ ኒዠር የሚደረጉ የንግድ በረረዎችን ማገድ።በኤኮዋስ አባል መንግስታትና በኒዠር መካከል የሚደረግ ማናቸዉም የገንዘብ ዝዉዉርን ማገድ።በኒዠርና በኤኮዋስ አባል መንግስታት መካከል የሚደረግ ማንኛዉንም የአገልግሎት ልዉዉጥን ማገድ።በኤኮዋስ ማዕከላዊ ባንኮች ዉስጥ የሚገኝ ማንኛዉም የኒዠር ሪፐብሊክ ሐብትን ማገድ።በንግድ ባንኮች ዉስጥ የሚገኙ የኒዠር መንግስት፣ የመንግስት ኩባንዮችና ከመንግስት ጋር የሚሰሩ ኩባንዮችን ሐብት ማገድ።»
በኒዠር ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ ዝርዝሩ ብዙ ነዉ።ግን ሥልጣን በኃይል መያዝ ወይም መፈንቅለ መንግስት ላፍሪቃ አዲስ ይሆን? ወይስ አፍሪቃዉያን በተለይም የኤኮዋስ መሪዎች እስከ ዛሬ አልነበሩ ይሆን?
በ2011 የሊቢያ መሪ መገደል፣ የአፍሪቃ ሕብረት ሽምግልና መክሸፍም ሆነ ሊቢያ የወርሮበሎች መፈንጫ መሆን ጥርስ-ጥፍር ለሌለዉ ለአፍሪቃ ሕብረት፣ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወይም «ዓለም አቀፍ» ለሚባለዉ ማሕበረሰብ ሲጠብቅ «ተገቢ እርምጃ» ሲሻሻል ከቁብ የማይገባ ዓይነት ነዉ።
የግብፁ ፊልድ ማርሻል አብዱልፈታሕ አል ሲሲ፣ በግብፅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ድምፅ የተመረጡትን ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲን ሐምሌ 2013 በፈንቅለ መንግስት አስወግደዉ የመሪነቱን ሥልጣን ያዙ።የአፍሪቃ ሕብረት መፈንቅለ መንግስቱን በማዉገዝ የአል ሲሲዋን ግብፅ ከአባልነት አግዶ ነበር።
በ2014 የአዉሮጳ ሕብረት ብራስልስ ላይ በጠራዉ የአፍሪቃና የአዉሮጳ ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲገኙ የአዉሮጳ ሕብረት አል ሲሲን ጋበዘ፤ የአፍሪቃ መሪዎችም አልሲሲ በሚካፈሉበት ጉባኤ ለመገኘት ተሽቀዳድመዉ ብራስልስ ገቡ።
የዙምባቡዌዉ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ግን ባለቤታቸዉን ይዘዉ ብራስልስ እንዳይመጡ በመከልከላቸዉ በጉባኤዉ ላይ አልተካፈሉም።የአዉሮጳ ሕብረት ለሙጋቤ ባለቤት የመግቢያ ፈቃድ የከለከለዉ ሕብረቱ ማዕቀብ ጥሎባቸዋል በሚል ነዉ።የአፍሪቃ ሕብረት ማርሻል አል ሲሲ በሚመሯት ግብፅ ላይ የጣለዉ ማዕቀብ ወይም እገዳን በአዉሮጶችም፣ በራሳቸዉ በአፍሪቃዉያንም መሪዎች ዘንድ ዋጋ ቢስነቱ ያኔ ተመሰከረ።
ባግቦ በ2011 በፈረንሳይ ጦር ድጋፍ መያዛቸዉ፣ ሙዓመር ቃዛፊ በNATO ትብብር መገደላቸዉ፣ መሐመድ ሙርሲ በ2013፣ ሮበርት ሙጋቤ በ2017፣ ዑመር አል በሽር በ2019፣ በመፈንቅለ መንግስት ከየስልጣናቸዉ መወገዳቸዉ ለአዲስ አበባ-ብራስልስ፣ ለአቡጃ-ኒዮርክ ማሕበራት፣ለዋሽግተን-ለንደን-ፓሪስ መንግስታትም ተገቢ እርምጃ ነበር።
የማሊ ወጣት የጦር መኮንኖች የጄሪ ሮሊንግስን፣ የቶማስ ሳንካራን ወይም የኦሌሼጎ አባሳንጆን ታሪክ ያዉቁ-አያዉቁምም ይሆናል።ከካይሮ እስከ ሐራሬ፣ከሲርት እስከ ኻርቱም በቅርቡ የሆነዉን፣ እየሰሙ ከሁሉም በላይ በሕዝብና በጦር ባልደረቦቻቸዉ ላይ የሚፈፀመዉን በደል እያወቁ የሩቁን ታሪክ መመርመር በርግጥ አያስፈልጋቸዉም።
አልሲሲ በ2013 ካይሮ ላይ ያደረጉትን ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ባማኮ ላይ ደገሙት።ነሐሴ 2020።የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ (ECOWAS) የአፍሪቃ ሕብረት፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስት ድርጅት፣ የቀድሞዋ የማሊ ቅኝ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ የማሊዉን ወታደራዊ ሁንታ ሲያወግዙ-ሲያስፈራሩ ማሊ ጎረቤት ቻድ ምርጫ ተደረገ።
በምርጫዉ ቻድን ለ30 ጠመናት የገዙት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ አሸነፉ።ግን ብዙ አልቆዩም። ዴቢ ከሸማቂዎች ጋር ሲዋጉ ጦር ሜዳ ተገደሉ።ሚያዚያ 2021።የዴቢ ልጅ ባለ አራት ኮኮቡ ጄኔራል መሐሜት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ የመሪነቱን ሥልጣን ያዙ።ጄኔራል መሐሜት ኢድሪስ ሕግ ጥሰዉ፣የሐገሪቱ ሕዝብ ምርጫን ሽረዉ ከመፈንቅለ መንግስት ባልተናነሰ ስልት ሥልጣን መያዛቸዉን ቀድሞ የደገፈችዉ የማሊን ወታደራዊ ሁንታ በኃይል ጭምር የምታስፈራራዉ የቻድ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረሳይ ናት።
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ለኢድሪስ ዴቢ ለቅሶ ንጃሚና ድረስ ተጉዘዉ ኃያል፣ ሐብታም ቅኝ ገዢ፣ ዴሞክራሲያዊት ሐገራቸዉ «የሽግግር» በሚል ሽፋን በመፈንቅለ መንግስት የተመሠረተዉን የዉርስ መንግስት እንደምትደግፍ አረጋገጡ።
«ፈረንሳይ ያለምንም ማወላወል ቻድን ትደግፋለች።ቻድ ለልጆችዋና ለሁሉም ዜጎችዋ ሠላም ለማስፈን የገባችዉን ቃል ታከብር ዘንድ ፈረንሳይ ድጋፍዋን ትሰጣለች።ሽግግሩም የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል።ከጎናችሁ እንቆማለን።»
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በ2018 ቡርኪና ፋሶ ዉስጥ በፀረ-ሽብር የኮማንዶ ዉጊያ ካሰለጠናቸዉ የአፍሪቃ ወጣት የጦር መኮንኖች የማሊዉ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ አንዱ ነበሩ።የጊኒዉ ሌትናንት ኮሎኔል ማማዴይ ዶምቦያ ሁለተኛዉ።ጎይታ በመፈንቅለ መንግስት የባማኮን ቤተ መንግስትን በተቆጣጠሩ ባመቱ ዶምቦያ የጊኒዉን ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴን ከስልጣን አስወግደዉ የኮናክሪን ቤተ መንግስት ተቆጣጠሩ።
ማማዴይ ዶምቦያ የፈረንሳይ ልዩ ኮማንዶ ጦር አባል በነበሩበት ወቅት ከአፍቃኒስታን እስከ ሊባኖስ በነበረ ዉጊያ ተካፍለዋል።ዶምቦያ በ200ዎቹ መጀመሪያ ፓሪስ-በሚገኘዉ የጦር ትምሕርት ቤት በሚማሩበት ወቅት ከቡኪናፋሶዉ ወጣት መኮንን ፓዉል ሔንሪ ሳንዳጎ ዳሚባ ጋር ይተዋወቃሉ።ዶምቦያ በ2021 ኮናክሪ ላይ ያደረጉትን የድሮ ጓደኛቸዉ ኮሎኔል ፓዉል ሔንሪ ሳንዳጎ ዳሚባ ጥር 2022 ላይ ዋጋዱጉ ላይ ደገሙት።ሌላ መፈንቅለ መንግስት።
ኮሎኔል ዳሚባ ከ8 ወራት በኋላ ሻምበል ኢብራሒም ትራኦሬ በመሩት ሌላ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተወግደዋል።ከ2019 ጀምሮ ሱዳን ሁለቴ፣ ማሊ ሁለቴ፣ ቡርኪናፋሶ ሁለቴ፣ ጊኒ አንዴ፣ ቻድ አንዴ የተደረገዉ መፈንቅለ መንግስት ባለፈዉ ሳምንት ኒዠር ደርሷል።በ2021 የተመረጡትን ፕሬዝደንት መሐመድ ባዙምን ከስልጣን ያስወገደዉ ወታደራዊ ሁንታ መሪ መፈንቅለ መንግስቱን ያደረጉት የሐገሪቱን የፀጥታ፣የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ቀዉሰችን ለማስገድ ነዉ-ባይ ናቸዉ።
የሰማቸዉ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።በተሻሻለ መፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የያዙትና የፈረንሳይ ሁለንተናዊ ድጋፍ ያልተለያቸዉ የቻድ ወታደራዊ ገዢ መሐሜት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ የኒዠር አዲስ መሪዎችን ለማግባባት ሞክረዉ ነበር።ይሁንና የዴቢ ተልዕኮ ዉጤት ሳይታወቅ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ አባል ሐገራት መሪዎች ባወጡት መግለጫ የኒዠርን ሁንታ በሳምንት ጊዜ ዉስጥ ፕሬዝደንት መሐመድ ባዙምን ወደ ስልጣን ካልመለሰ መፈንቅለ መንግስቱን በጦር ኃይል ጭምር ለማክሸፍ ዝተዋል።
« (ECOWAS) ያቀረበዉን ጥያቄ በአንድ ሳምንት ዉስጥ መልስ ካላገኘ በኒዠር ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ለማስከበር አስፈላጊዉን ርምጃ ሁሉ ይወስዳል።እርምጃዎቹ የወታደራዊ ኃይልን ሊጨምሩ ይችላሉ።ለዚሕም ሲባል የኤኮዋስ አባል ሐገራት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች በቅርቡ ይሰበሰባሉ።»
መፈንቅለ መንግስት ብዙዎች እንደሚሉት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያጠፋ፣ የሐገርና የሕዝብ ሰላምን ላደጋ የሚያጋልጥ፣ ምጣኔ ሐብትን የሚያቀጭጭ ከሁሉም በላይ የሰዉ ደምና ሕይወት የሚያጠፋ ነዉ።ግን በቅርቡ ዘመን ሲርት፣ ካይሮ፣ ሐራሬ፣ ካርቱም፣ ንጃሚና ላይ ልክ የሆነዉ፣ባማኮ፣ ኮናክሪ፣ ዋጋዱጉ ላይ ጥፋት የሆነበት፣ ኒያሚ ላይ ወንጀል ሆኖ ጦር የሚያዘምትበት ምክንያት በርግጥ እንደገና ሊያነጋግር ይገባል።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ