1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ ሱዳን «የጅል ዉጊያ» ሐገር

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ግንቦት 28 2015

ከዚሕ በተጨማሪም ጦርነቱ ከራስዋ ከሱዳን ቀጥሎ የሚጎዳዉ ጎረቤቶችዋን በመሆኑ የኢጋድ ዉሳኔ ተገቢና ግዴታም መሆኑ በርግጥ አላጠያየቀም።ይሁንና ለሽምግልና የተመረጡት የኢጋድ አባል ሐገራት መሪዎች ከናይሮቢ፣ከጁባና ጅቡቲ ኻርቱም ለመድረስ መንገድ አጥተዉ ቀን ሲቆጥሩ የአደራዳሪነቱን ኃላፊነት የዋሽግተንና የሪያድ ባለስልጣናት ወሰዱት።

Tschad Flüchtlingscamp Borota Sudan
ምስል Blaise Dariustone/DW

ሱዳን፣ የድርድር ማግስት ዉጊያ

This browser does not support the audio element.

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ የሱዳን ጄኔራሎች የገጠሙትን ዉጊያ የጅሎች ይሉታል።የአሜሪካ ባለስልጣናት ባንፃሩ ጄኔራሎቹን የምናደራድረዉ ለመደራደር ሲፈልጉ ነዉ ይላሉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልዩ ተልዕኮዉን ጊዜ አራዝሟል።የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ እንደሚለዉ የዉጊያዉ መበርታት ዕርዳታ አቅርቦቱን አዉኮበታል።በሩቶ አገላለፅ ትርጉም የለሹ ጦርነት ሞቅ፣ ቀዝቀዝ እያለ ሺዎችን እየገደለ፣ ሚሊዮኖችን እያፈናቀለ፣ ሱዳንን እያወደመ ቀጥሏል።ጦርነቱ፣ የአፍሪቃዉያን ጥረት መሳናከልና የድርድሩ መፋረስ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

                             

ሐይባ አል ረሺድ መሐመድ አሕመድ የምትደብቀዉ የላትም።ቤቷ ነድዷል፤ ንብረቷ ጋይቷል፤ ልጆጅዋ ታመዋል።ተርበዋልም።ምኗን ትደብቅ? «ቅረፁ» አለች የካሜራ ባለሙያዎቹን ረሐብና በሽታ ወዳጠወለጋቸዉ ልጆችዋ እያመለከተች።

«ፈጥኖ ደራሾች በቦብ ደበደቡን፣ሐብት ንብረታችንን አነደዱት።ያለንበትን ሁኔታ ተመለክቱ።የታመሙ ልጆቻችንን ተመልከቱ።»

የሱዳን መከላከያ ሰራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ጦርን የሚያዙት የቀድሞ የሱዳን ዋና እና ምክትል ገዢዎች የስልጣን ሽኩቻ ንሮ ዉጊያ ከተጫረ ወዲሕ ለችግር ለተጋለጠዉ ሕዝብ እርዳታ ለማቀበል ከሚባትሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለይ ከፍተኛዉን መድሐኒት የሚሰጠዉ የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ነዉ።

ምስል Bandar Algaloud/Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ኮሚቴዉ እንደሚለዉ ጦርነቱ ለጎዳዉ ሕዝብ የሚሰጠዉ ምግብ፣መድሐኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ከፈላጊዉ ሕዝብ ጋር ሲነፃጸር አነስተኛ ነዉ።የከፋዉ ደግሞ፣ የኮሚቴዉ ቃል አቀባይ አልዮና ሲኔንኮ በቀደም እንዳሉት ያለዉንም ለፈላጊዉ ማድረስ አለመቻሉ ነዉ።የፊት ለፊቱ ዉጊያ-አንድ፣ በሰራተኞች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት-ሁለት ዘረፋና ስርዓተ አልበኝነት---ሶስት።ይቀጥላሉ ቃል አቀባይዋ።

«ለመስራት እጅግ ሲበዛ አስቸጋሪ ነዉ።ምክንያቱም ለወራት ያለማቋረጥ የሚደረግ ዉጊያ አለ።ከዚሕ በተጨማሪ ደግሞ ሥርዓተ-አልበኝነት ነግሷል።ዘረፋዉ ልክ የለዉም።የሚፈፀመዉ ወንጀል አለቅጥ ተባብሷል።ይሕ እንግዲሕ ርዳታ የማከፋፈሉን ሥራ አደገኛ አድርጎታል።አሁን ባለዉ ችግር ርዳታዉ ከመጋዘን ወጥቶ ለፈላጊዉ መድረሱን ማረጋገጥ አይቻልም።»

ከ2019 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አጋማሽ ጀምሮ ሱዳንን የሚገዛዉ የሐገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት የተባለዉ ስብስብ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሐንና ምክትላቸዉ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምዲቲ) አንድ-መስለዉ፣ ባንድ ቆሞዉ ከሐገሪቱ የሲቢል ፖለቲከኞ ጋር ለወራት ሲወዛገቡ፤ ብዙዎች እንደሚያምኑት ተቃዉሞ ሰልፈኞችን በሚያዟቸዉ ወታደሮች ሲያስገድሉ፣ ሲያሳፍሱ፣ሲያሳስሩም ነበር።

 

ሁለቱ ጄኔራሎች የሚመሩት ወታደራዊ መንግስት ከሲቢል ፖለቲከኞች ጋር የገጠመዉን አተካራ ለማስወገድ የአፍሪቃ ሕብረት፣ የኢጋድ፣ የአረብ ሊግ፣ የኢትዮጵያ፣የግብፅ፣የሳዑዲ አረቢያ፣ የዩናትድ ስቴትስና  የሌሎችም  ማህበራትና መንግስታት ዲፕሎማቶች ብዙ ደክመዋል።ተወዛጋቢ ኃይላትም፣ የኋላ ኋላ ቢከሽፍም የወታደር-ሲቢል ቅይጥ አስተዳደር መስረተዉም ነበር።ያኔ አንድ እስኪመስሉ ድረስ ባንድ ቆመዉ የነበሩት ሁለቱ ጄኔራሎች የሚያዟቸዉ የሱዳን መከላከያ ሠራዊትና የሐገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ባለፈዉ ሚያዚያ 7 ዉጊያ ሲገጥሙ ተፋላሚዎችን የሚሸመግሉ መሪዎችን ከሁሉም ቀድሞ ወደ ኻርቱም ለመላክ የወሰነዉ የምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ነበር።

ሱዳን የኢጋድም የአፍሪቃ ሕብረትም መስራች አባል ሐገር ናት። ከዚሕ  በተጨማሪም ጦርነቱ ከራስዋ ከሱዳን ቀጥሎ የሚጎዳዉ ጎረቤቶችዋን በመሆኑ የኢጋድ ዉሳኔ ተገቢና ግዴታም መሆኑ በርግጥ አላጠያየቀም።ይሁንና ለሽምግልና የተመረጡት የኢጋድ አባል ሐገራት መሪዎች ከናይሮቢ፣ከጁባና ጅቡቲ ኻርቱም ለመድረስ መንገድ አጥተዉ ቀን ሲቆጥሩ የአደራዳሪነቱን ኃላፊነት የዋሽግተንና የሪያድ ባለስልጣናት ወሰዱት።

ምስል Mohamed Nureldin Abdallah/REUTERS

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶም ለሱዳን ጄኔራሎች ኻርቱም ላይ ሊነግሩ ያሰቡትን ወይም የሚነግሩበት መንገድ ሲጠፋቸዉ ባለፈዉ ወር ለደቡብ አፍሪቃ ምክር ቤት ዘረገፉት።

«የሱዳን ጄኔራሎች ሁሉንም ነገር በቦምብ እየደበደቡ ነዉ።መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ሆስፒታሎችን አዉሮፕላ ማረፊያዎችን ያወድማሉ።ሁሉንም የሚያወድሙት በአፍሪቃዉያን ገንዘብ በተገዛ ጦር መሳሪያ ነዉ።አስቡት።እነዚያ ጄኔራሎች ይሕን ጅልነት እንዲያቆሙ ልንነግራቸዉ ይገባል።»

 

ሩቶ ይሕን የተነጋሩት ከሁለት ሳምንት በፊት ነዉ።ባለፈዉ አርብ አፍሪቃ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ላይ የሆነዉን ሲሰሙ ያሉት ካለ በርግጥ አልሰማንም።የሰማነዉ የህዝብ ሰላም እንዲያስከብር ከህዝብ የተሰበሰበ ገንዘብ ደሞዝ የሚከፈለዉ የኢትዮጵያ ወታደር ወይም ፖሊስ፣በህዝብ ገንዘብ የተገዛ ጥይት ፈጣሪዉን ሊማፀን ለሶላት በታደመ፣ ባልታጠቀ አማኝ ላይ ማዝነቡን ነዉ።

 

የአፍሪቃ ፖለቲከኞች ለአፍሪቃ ችግር አፍሪቃዊ መፍትሔን ሲዘምሩ ሲያዘምሩ 60 ዓመታት በልጧቸዋል።ለሱዳን ዉጊያም አብነቱ አፍሪቃዊ በጣም ደግሞ ከሱዳን ጋር ድንበር፣ ባሕል፣ቋንቋ የሚጋሩ ሐገራት ሽምግልና ነዉ የሚሉ ብዙ ናቸዉ።ነገር ግን የየራሳቸዉን ህዝብ የሚረግጡ፣ ገናለገና ይቃወሙናል የሚሏቸዉን የሚያፍኑ ወይም የየራሳቸዉን መንግስት በቅጡ የማይመሩ ፖለቲከኞች ለጎረቤቶቻቸዉ ይጨነቃሉ ብሎ ማሰብ በርግጥ ከዉጊያዉም በላይ ጅልነት ነዉ።

 

የጁባ ገዢዎች 10 ሺዎችን ከፈጀዉ የርስ በርስ ጦርነት ያላገገመች አዲስ ደሐ ሐገር እያስታመሙ ነዉ።የኢትዮጵያ ብጤዎቻቸዉ ከመቀሌ እስከ ሸዋሮቢት መቶ ሺዎችን የፈጀዉ ጦርነት ጢስ ጠለሱ ሳይሰክን ከቶሌ እስከ መርካቶ አስከሬን እያስቆጠሩ ነዉ።ኤርትራ አንዴ ከሞስኮ ሌላ ጊዜ ከቤጂንጎች ጋር እየተሞሸረች-ትፋረሳለች።

ምስል Sudanese Armed Forces/REUTERS

ሶማሊያ ከራሷ ጋር የሚያስታርቃት መሪ፣ደጋፊ፣ረዳትም አጥታ ከሶማሌዎችም አልፋ የዩጋንዳ፣ የኬንያ፣ የብሩንዲ ወታደሮችን አስከሬን ትሸኛለች።በቀደም ብቻ 54 የዩጋንዳ ወታደር ተገደለባት።ቻድ የመሪዋን ሕይወት የቀማ ግጭትና መፈንቅለ መንግስት ይፈራረቅባታል።

ጅቡቲ ትንሽ ናት።በዚያ ላይ የባሕር ዳርቻይቱን ሐገር ፈጥርቀዉ የሚገዙት ኢስማኢል ዑመር ጉሌሕ እንደ ኤርትራዉ ብጤያቸዉ ከወገኖቻቸዉ ጋር መደራደርን ሳያዉቁ ሌሎችን ሊያደራድሩ አይችሉም።ግብፅ፣ ከተፋላሚ ኃይላት መካከል አንዱን እየረዳች ከሌላዉ ጋር ልታሸማግል አትችልም።ሩቶ አድናቂ፣አሞጋሽ አጨብጫቢም አላጡም ግን ብቻቸዉን ናቸዉ።

 

«ወታደራዊ ኃይል ወንጀለኞችንና አሸባሪዎችን ለመዋጋት እንጂ ልጆችንና ሴቶችን ለመዉጋት፣ የራሳችንን የመሰረተ ልማት አዉታር ለማዉደም አይደለም።ይሁንና በገዛ አሐጉራችን የሚፈፀመዉን ይህንን ቂልነት ለማቆም አቅም የለንም።ምክንያቱም ለራሳችን ሰላምና ፀጥታ የሚሆነዉ ወጪ የሚመደበዉ በሌሎች ነዉ።ችግር አለብን።ግን ይህን ችግር ማረም አለብን።ሌላ አይመጣም ራሳችን ነን።»

ይሳካላቸዉ።

ምስል Britta Pedersen/dpa/picture alliance

ለሱዳን ህዝብ ግን እስካሁን የደረሰለት የለም።ሩቶ እንዳሉት የሱዳን ጄኔራሎችን አፍሪቃዉያኑ ማደራደር ሲያቅታቸዉ ጣልቃ የገቡት ዩናይትድ ስቴትስና ሳዑዲ አረቢያ ለሳምንታት የመሩት ድርድር ያለዉጤት አብቅቷል።የሁለቱ ጄኔራሎች ተወካዮች ጂዳ ላይ ባደረጉት ድርድር መሰረት የታወጀዉ ጊዚያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ትናንት በይፋ አብቅቷል።

ኻርቱም፣እንዱሩማን፣ የዳርፉር የተለያዩ አካባቢዎች ከትናንት ጀምሮ እንዳዲስ በቦምብ-መድፍ-ሚሳዬል እየታረሱ ነዉ።ዳርፉር ዉስጥ ብቻ ትናንት ብቻ 40 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።እሷ ግን ተርፋለች።የተረፋት የለም እንጂ።«ቤታችን ጋየ። ንብረታችንን በሙሉ ነደደ።ርዳታ እንሻለን።» ትላለች።

 

ዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት እንዳሉት የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያዉን በድርድር ለማቆም ከልባቸዉ አይፈልጉም።የጂዳዉ ድርድር የፈረሰዉም ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ተወካዮች ባለፈዉ ሮብ ራሳቸዉን ከድርድሩ በማግለላቸዉ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝድንት የብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ደርድሩ መቋረጡን «አሳዛኝ» ብለዉታል ግን  ይቀጥላል የሚል ተስፋ አላቸዉ።

ምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

«ድርድሩን በማቋረጣቸዉ በጣም እናዝናለን።ለሰላም የሚደረገዉን ጥረት ከልብ እንዲያጤኑት እንፈልጋለን።እኛ ከምራችን ነዉ።በዚሕ ድርድር እንዲካፈሉና ድርድሩ እንዲቀጥል እየረዳናቸዉ ነዉ።በዚሕም መሰረት ዳግም ልናገኛቸዉ እንፈልጋለን»

ድርድሩ ከተስፋ ባለፍ የሚቀጥልበት ጊዜ አይታወቅም።ዉጊያዉ ግን አላባራም።እስካሁን በሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በብዙ አስር ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏል።ግማሽ ሚሊዮን ተሰድዷል።

በዚሕ መሐል የሱዳን ወታደራዊ ገዢዎችን ከሲቢል ፖለቲከኞች ጋር ያደራድር የነበረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ተልዕኮ ሱዳን የሚቆይበት ጊዜ በ6 ወራት እንዲራዘም የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት ወስኗል።ማንን ሊያደራድር?

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW