ማሕደረ ዜና፣ ሽብርም ያጣላል?
ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016
የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን «ነብሰ ገዳይ» እና «ናዚዎች» ያሏቸዉ ታጣቂዎች ባለፈዉ አርብ በጥይት ቦምብ-የፈጁት የሩሲያ ወጣቶችን፣ ያሸበሩት ሞስኮን፣ ያወደሙት የአራስ አጋላሮቭ ንብረትን ነዉ።በገዳይ አሸባሪነት የተጠረጠሩት የተያዙት ሩሲያ ዉስጥ፣ ያዢዎቹም መርማሪዎቹም የሩሲያ ፀጥታ አስከባሪዎች ናቸዉ።አሸባሪዎቹን ያዘመተዉ እራሱን የእስላማዊ መንግስት ኬ (ISIS-K) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን እንደሆነ ለዓለም የተናገሩት ግን «የቡድኑ» የተባሉ አምደ መረቦች እና የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ናቸዉ።እርግጥ ነዉ የሩሲያ ባለሥልጣናት ተጠርጣሪዎቹ ወደ ዩክሬን ሊሻገሩ ሲዘጋጁ መያዛቸዉን አስታዉቀዋል።
ቡድናችዉን ግን ቢያንስ አስከ ዛሬ ድረስ ገና «እያጣራን ነዉ» ከማለት አልፈዉ ሞስኮዎች አልተናገሩም።ሩሲያዎች ሥላለቁበት ሞስኮ ሥለተፈፀመ ሽብር፣ ሩሲያ ዉስጥ ሥለተያዙ አሸባሪዎች ማንነት ሞስኮዎች ሳያዉቁ ወይም ሳይናገሩ ዋሽግተኖች እንዴት አወቁ? ለምንስ ተናገሩ? ላፍተ አብረን እንጠይቅ?
አሁን መኖር-አለመኖሩን አላረጋገጥኩም።ቀደም ባሉት ዘመናት ግን ኢትዮጵያዉያን አማርኛ ተናጋሪዎች አንድ አባባል ነበራቸዉ።«ከባለቤቱ ያወቀ----» የሚል።ለፖለቲከኞች በጣሙን ለሐብታም-ኃያል ሐገራት ፖለቲከኞች ግን «ነዉር» ወይም፣ ለሌሎች ክብር»ን ጠቋሚ ብሒልና መርሕ ብዙ መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የዓለምን አንደኛ ሐብታምነት ደረጃ ከያዘች 60፣ ልዕለ ኃያልነቷን ካረጋገጠች 30 ዓመት አለፋት።
የድሕረ 1990ዎቹ አስተሳሰብ
አጥኒዎች እንደሚሉት የዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ የሐገር ዉስጥ ምርት (GDP) 26 ትሪሊዮን፣ ሐብቷ ደግሞ 146 ዶላር ትሪሊዮን ነዉ።ሐይቲ የምትባለዉ የድሆች ድሐ ሐገር ሚያሚ ከምትባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጠረፍ 680 ኪሎ ሜትር ቢርቅ ነዉ።የሐይቲ ሕዝብ ድሕነት፣በሽታ፣ የተፈጥሮ መቅሰፍት አልበቃ ያለዉ ይመስል በፖለቲከኞች ሴራና ሸር ፣ በአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች ክፋት አሁን ደግሞ በወርሮ በሎች ጭካኔ እየተገደለ፣ እየተዘረፈ፣ እየተሰደደ ነዉ።
የዓለም ሐብታም ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር መሪዎች ከሐገራቸዉ ድንበር 600 ኪሎ ሜትር የሚሻገር ፀጥታ አስከባሪ ማዝመት አቅቷቸዉ፣ ዘማች አጥተዉ ወይም ተጠይፈዉ 12 ሺሕ ኪሎሜትር የምትርቀዉ፣ደሐ፤አሪቃዊቱ የጥቁሮች ሐገር ኬንያ ለጥቁሪቱ የካረቢክ ህዝብ ደሕንነት ፖሊስ እንድታዘመት ተጠይቃለች።ኬንያ ጥግ ቀይ ባሕርና አደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ግን የኃያሊቱ ሐገር ኃይል ጦር ሕይወት ሳይሆን «መርከብ ጥበቃ» ይርመሰመሳል።
የሶቭየት ሕብረት ኮሚንስታዊ ሥርዓት ከተደረመሰ ከ1990ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) West is Best እያለ፣ እየተባለለት ወይም እንዲል ተገድዶ ያደገዉ ትዉልድ የተቃርኖዉን ሐቅ አይጠይቅም።ከጠየቀም አልተሰማም።
ባለፈዉ አርብ ሞስኮ መዳረሻን ያሸበረዉ ጥቃትም ለምንደረሰ ከሚለዉ ጥያቄ በላይ የሞስኮ፣ ኪቪ-ዋሽግተኖች መሻኮቺያ መሆኑ ከ1990ዎቹ ወዲሕ ዓለም የምትከተለዉ መርሕ አልባ-«መርሕ» ዉጤት መሆኑ ሊያነጋግር በተገባ ነበር።
የአሸባሪዎቹ ቡድን ምንነት
የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሥለጥቃቱ በሰጡት ማብራሪያ የአሸባሪዎቹን ማንነትም ሆነ የቡድናቸዉን ምንነት አልጠቀሱም።ሊያመልጡ የነበረበትን አቅጣጫ ግን ጠቁመዋል።
«የሽብር ጥቃቱን በቀጥታ ያደረሱት፣ሰዎችን የገደሉት 4ቱም ተጠርጣሪዎች ተይዘዉ ታስረዋል።የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ እንደሚያመለክተዉ ለመደበቅ ሞክረዉ ነበር።ወደዩክሬን ለመንቀሳቀስ ሞክረዉ ነበር።ከዩክሬን ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር በኩል ወደዩክሬን እንዲሻገሩ መተላለፊያ ተዘጋጅቶላቸዉ ነበር።»
ዋሽግተኖች ግን ሞስኮዎች ያልተናገሩትን፣ ወይም የደበቀቱን ተሽቀዳድመዉ ተናገሩ።ሩሲያ ዉስጥ የሆነዉን ከሩሲያዎች ቀድመዉ የመናገራቸዉ ድፍረት ማንአህሎኝነት፣ የመረጃቸዉ አስተማማኝነት ፣ እብሪትም ሊሆን-ላይሆንም ይችላል። የሞስኮ፣ ዋሽግተኖች ጠብ ነፀብራቅ፣ ዩክሬንን የመደገፍ ብልጠት፣ «ስለናንተ ከናንተ-በላይ እኛ እናዉቃለን» የማለት ግብዝነት አብነት ከሁሉም ጋር «ከባለቤቱ ያወቀ---» ዓይነት መሆኑ ግን በርግጥ አያጠራጥርም።
ባለፉት 3 ዓመታት በዋይት ሐዉስ ፖለቲካ ዲፕሎማሲ ብዙም የማይታዩት ምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ የምርጫ ዘመቻ ከተጀመረ ወዲሕ በየቴሌቪዥን ካሜራዉ ፊት ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።ትናንትም አሸባሪዎቹ «ወደ ዩክሬን ሊጓዙ ነበር» የሚለዉን የፕሬዝደንት ፑቲንን መግለጫ ለማስተባበል፣ዩክሬንን ለመደገፍና የአሸባሪዉን ቡድን ማንነት በርገጥኝነት ለመናገርም አላመነቱም።
«አይደሉም፣ መጀመሪያ የሆነዉ የሽብር ጥቃት ነዉ።የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አሳዛኝ መሆኑ ግልፅ ነዉ።ለቤተሰቦቻቸዉ በሙሉ ሁላችንም ሐዘናችንን መግለፅ አለብን።(ዩክሬን አለችበት) የሚለዉ ምንም መረጃ የለም።ሥለጉዳዩ የምናዉቀዉ ምንድነዉ በየተኛዉም መመዘኛ ለሆነዉ ተጠያቂዉ ISIS-K ነዉ»
በዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ የሚደገፉት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ ግን በአሸባሪዉ ማንነት ላይ አንድም ከዋሽግተኖች አልገጠሙም፣ ወይም ሊናገሩ የሚገባቸዉን የዋሽግተን ብራስልስ ጠባቂዎቻቸዉ አልመከሯቸዉም።ዘለንስኪ ለጥቃቱ ተጠያቂዉ የፕሬዝደንት ፑቲን መንግስት ነዉ ባይ ናቸዉ።
«ትናንት ሞስኮ የሆነዉ ምንድነዉ፣ የታወቀ ነዉ።ፑቲንና ሌሎች ትርኪሚርኪዎች ተጠያቂነቱን በሌሎች ለማሳበብ ይሞክራሉ።ሁልጊዜ ተመሳሳይ ዘዴ ነዉ ያላቸዉ።ከዚሕ በፊት ሆኗል።ከዚሕ ቀደምም ቤቶችን አጋይተዉ፣ ተኩስ ከፍተዉ፣ አፈንድተዉ ሁል ጊዜ ሌሎችን ያወግዛሉ።»
የቀድሞዉ ቀልደኛ ዘለንስኪ ምናልባት ትርኪሚርኪ ካሏቸዉ አንዷ የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቫ ኮምሶሞልስካያ ፕራቭዳ በተሰኘ ጋዜጣ ባሳተሙት መጣጥፍ ዩናይትድ ስቴትስ ISISን እንደ «ማስፈራሪያ ጭራቅ» የጠቀሰችዉ ለኪቭ «ዘብ» መቋሟን ለመሸፈን ይላሉ።ቃል አቀባይዋ ለአንባቢዎች አንድ ነገር ማስታወስ አፍልጋለሁ በማለት፣ «በ1980 አፍቃኒስታን ዉስጥ ሶቭየት ሕብረትን ይወጉ የነበሩ ሙጃሒዲያንን ዩናይትድ ስቴትስ ስትደገፍ ነበር።»እያለ ቀጠሉ ፀሐፊዋ።
የክሮከስ ከተማ አዳራሽ
የዋሽግተን፣ኪቭ-ሞስኮን መሪዎች ሁለት ዓመት ለበለጠዉ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጦርነታቸዉ መጠቀሚያ ያዋሉት የአርቡ ጥቃት በርግጥ ብዙዎች እንዳሉት በአብዛኛዉ በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ የዋሆችን ሕይወት የቀጨ፣ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ፣ ዘግናኝም ነዉ።
«በቅርቡ ሴት ልጃችንን አጥተናል።በዚሕ ጥቃት ልጆቻቸዉን ያጡ ወላጆች የሚሰማቸዉን አዉቃለሁ።ፅናትና ትዕግስቱን እንዲሰጣቸዉ እመኛለሁ።ፈጣሪ ይርዳቸዉ።ከሐዘኑ ጋር መኖርን መልመድ አለብን።መኖር አለብን።»
የአዘርበጃኑ ቱጃር አራስ አጋላሮቭ በ2009 ያስገነቡት ሰፊ፣ትልቅ፣ ዉስብስብ ዘመናይ የትርዒት አዳራሽ እንደ እሱዉ ሁሉ በጣም የገዘፉ የገበያ አዳራሾች፣ ዘመናዊ ሆቴሎችና ሌሎች መዝናኛዎች አጅበዉታል።አዳራሹ በሸቀጦች መሸጪያና ማረገፊያ ሥፍራ መከበቡ ገዳዮቹ በተለያዩ መኪኖች ያጨቁትን ጠመንጃ፣ጥይትና ቦምብ በቀላሉ ለማስገባት ሳይረዳቸዉ አልቀረም ነዉ-የሚባለዉ።
የክሮከስ ከተማ አዳራሽ 6,200 መቀመጫዎች አሉት።የዚያን ቀን ትርዒት ሊያሳይ የነበረዉ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በጣም የታወቀዉ ተወዳጁ የፒክኒክ የሙዚቃ ጓድ በመሆኑ ትኬቱ አስቀድሞ ተሸጧል።ትርዒቱ የሚጀመረዉ ከምሽቱ 2 ሰዓት ነበር።
ከግድያዉ የተረፈዉ ዴቪድ ፒሪሞቭ እንደሚለዉ አዳራሹ ግን ካንድ ሰዓት ጀምሮ ካፍ እስከገደፉ ሞልቷል።፣«ሁለት ሰዓት ሊሆን 7 ወይም 10 ደቂቃ ሲቀረዉ» ቀጠለ ዴቪድ «ከፊት ፍንዳታ ሰማሁ፣ርችት መስሎኝ ነበር።» ከጓደኛዬ ጋር ከመቀመጫችን ብድግ ሥንል «ካኪ የለበሱ ሰዎች---ተመልካቹ ላይ ጥይታቸዉን ሲያርከፈክፉት አየሁ---» ይላል።ሌለኛዉ በእድሜ በሰል ያሉት ደግሞ
«ልቤ ዉስጥ የሆነ ቦምብ የፈነዳ ነዉ የመሰለኝ።ታዉቃለሕ ልክ የክሮከስ ከተማ አዳራሽን ያጋየዉ ቦምብ አይነት ነገር ልቤን የገመሰዉ ነዉ የመሰለች።ያስፈራል።ልብ ይሰብራል።»
ጓደኛሞች፣ ፍቅረኞች፣ አዲስ ተዋዋቂዎች በሙዚቃ ትርዒት ሊደሰቱ፣ሊዛናኑ ጎን ለጎን እንደተቀመጡ ወይም እንደቆሙ ከዚያ ዉብ አዳራሽ ወለል-ወንበር ላይ ወደቁ።137ቱ እስከመጨረሻዉ አሸለቡ።180 ቆሰሉ።ሩሲያ መስከረም 2004 ቢስላን ትምሕርት ቤት በደረሰዉ እገታና ሽብር ከ330 በላይ ሰዎች ከተገደሉ ወዲሕ ባንድ ጊዜ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሲገደሉ የአርቡ የመጀመሪያዉ ነዉ።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት እንደሚሉት አፍቃኒስታን ዉስጥ የተደራጀዉ የISIS ቅርንጫፍ ISIS-K ሩሲያ ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ በሞስኮ የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈዉ መጋቢት መጀመሪያ ላይ ለሩሲያ ባለስልጣናት ጠቁሞ ነበር።አሜሪካኖች እንደሚሉት ሩሲያዎች ጥቆማዉን አልተቀበሉትም።እና ፕሬዝደንት ፑቲን ለአምስተኛ ዘመነ-ሥልጣን መመረጣቸዉ በተረጋገጠበት፣ ክሪሚያን ከሩሲያ የተቀየጡበት 10 ዓመት ድል በተዘከረበት በአምስተኛዉ ቀን፤ የሩሲያ፣ የዩክሬን-ዩናይትድ ስቴትስና ምዕራብ አዉሮጳ መንግስታት ጦርነት ሁለተኛ ዓመት በተዘከረ በወሩ ሩሲያ ዳግም ተሸበረች።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ