1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ ኢትዮጵያ የስምምነት ማግስት ጠብና ዉጥረት

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 1 2015

የኤርትራና የአማራ ኃይላት ወዳጅነትና የወዳጅነቱ ደረጃ ለጊዜ ሒደት የሚተዉ ነዉ።የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግስት «የክልሎች ልዩ ኃይላትን ዳግም ለማደራጀት» ባለዉ ዘመቻ የአማራ ታጣዊዎችን ትጥቅ ማስፈታት ከጀመረበት ካለፈዉ ወር ወዲሕ ግን በመንግስትና በአማራ ኃይላት መካከል የተፈጠረዉ ጠብ እየተካረረ መምጣቱን ለማወቅ አስተንታኝ አያስፈልግም።

Äthiopien Gondar | Bilder zur aktuellen Sicherheitslage
ምስል Nebiyu Sirak/DW

ማህደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ ዉጥረት የሚረግበዉ መቼ ነዉ?

This browser does not support the audio element.

ትግራይ አማራና አፋር ክልል ዉስጥ መቶ ሺዎችን ያረገፈዉ፣መላዉ ኢትዮጵያን ቁልቁል የደፈቀዉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት ከቆመ ባለፈዉ ሳምንት ስድተኛ ወሩን ደፈነ።የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ ኦሮሚያ በጣሙን ምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ የተጫረዉን ግጭት፣ጥቃትና ማፈናቀል ለማቆም የተደረገዉ ድርድር ግን እስካሁን ተጨባጭ ዉጤት አላመጣም።በጥያቄዎች የታጀበ ተስፋ ግን ፈንጥቋል።የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግስት ሰሜንና ምዕራብ ላይ ከሸመቁ ጠላቶቹ ጋር ሰላም ሲያወርድ ወይም ሰላም ለማዉረድ ሲደራደር «የጠላቴ ጠላት» በሚል ስልት ከተጣመራቸዉ ከኤርትራ መንግስትና ከአማራ ኃይላት ጋር አዲስ አተካራ መግጠሙ የጥንታዊቱን፣ የመቶ ሃያ ሚሊዮኖቹን ሐገር መከራ ማብቂያ የለሽ አስመስሎታል።የጦርነት ማግስቱ ዉጥረት፣የድርድር መሐሉ ጥያቄ፣ ግፊትና የኢትዮያ ፈተና ያጭር ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

እትጌ ጣይቱ ከምኒሊክ ቤተ-መንግስት ወደ እንጦጦ ከተጋዙ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ምሽት ከትልቁ ጉብታ ቁል ቁል ሲመለከቱ፣ አዲስ አበባ በተለይ ቤተ-መንግስቱ  በኤሌክትሪክ ብርሐን ተንቆጥቁጦ ሲያዩ «ይኽ ደግሞ የት ነዉ» ብለዉ-ጠየቁ አሉ-አፈታሪክ አቀባባዮች።

አጠገባቸዉ ከነበሩ ደንገ ጡሮቻቸዉ አንዷ -ቀጠሉ ተራኪዎቹ «አይ እሱማ የእመቤቴ እልፍኝ የነበረዉ ነዉ» እያለች አስረዳች።እትጌም ጥቂት ተከዝ ብለዉ «ነበር ለካ እንዲሕ ቅርብ ነዉ?» አሉ-አሉ-ተራኪዎች።

ከግራ ወደ ቀኝ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ንጉስ ሳልማን፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድምስል picture-alliance/AP Photo/SPA

ለዘመኑ የኢትዮጵያ-የኤርትራ ፖለቲከኞች የፍቅርና ጠብ-ፍርርቅ  ደግሞ «ነበር» ከማሰኘትም በላይ ቅርብ ነዉ።የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች በ2010 አጋማሽ በድብቅ የመሰረቱት ወዳጅነት «ፍቅሬ ፍቅሬ በዛን» አስዘፍኖ ሳያበቃ በቃል ኪዳን መተሳሰራቸዉን አስመራና አዲስ አበባ ላይ ለወዳጅ-ጠላታቸዉ አበሰሩ ወይም አረዱ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ።

 «ማንም ማንም፣ ፍቅራችንና ስምምነታችንን፣ ልማትና ዕድገታችንን ለማደናቀፍና ለማዉደም እንዲፈታተነን እንፈቅድለትም።»

በሁለተኛ ዓመቱ።ጥቅምት 23፣ 2013 ትግራይ ላይ የተጫረዉ ዉጊያ የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎች  ወዳጅነትን «ለነበር ዝክር» ወርዉሮ ጠላነታቸዉን ሲያረጋገጥ፣ አዲስ አበባ ላይ ቃል የተገባለት የአስመራ-አዲስ አበባ መሪዎችና የአማራ ታጣቂዎች ፍቅር «የጋራ ጠላትን» በጋራ በመዉጋት የደም-ግብር  ገቢር ሆነ።

ጦርነቱ ያደረሰዉ ጥፋት እስካሁን በትክክል አይታወቅም።በትግራይ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰዉን ግፍ የሚያጣራዉ  ኮሚሽን ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ ባለፈዉ ጥር እንዳሉት ግን «እብደት ነዉ»ትግራይ ዉስጥ በኤርትራ ወታደሮች ስለተፈፀመ ግድያ የዓይን እማኝ መረጃ

በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉ ግፍም በተደጋጋሚ እንደተነገረዉ ከትግራዩ አይተናነስም።እንደገና በሁለተኛ ዓመቱ። ጥቅምት 23፣ 2015። የአዲስ አበባ መሪዎች የአስመራና የአማራ ወዳጆቻቸዉን ጥለዉ ከመቀሌዎች ጋር «ፍቅርን እንደገናን» ፕሪቶሪያ ላይ ሲያንጎራጉሩ በወታደሮች ደም-አጥንት የተለሰነ ይመስል የነበረዉ የአዲስ አበባ-አስመራ-አማራ ወዳጅነት ይሰነጣጠቅ « ወድዶ የጠላ ሰዉን» ያስዜም ያዘ።

የፕሪቶሪያዉ ስምምነት ያስቀየማቸዉ የኤርትራና ስምምነቱ ጥያቄያችንን «አልመለሰም» የሚሉት የአማራ ታጣቂ፣ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና  የፖለቲካ አቀንቃኞች ቅሬታ አሳስቧቸዉ አሰባስቧቸዉ ይሆን-አይሆንምም ይሆናል።

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ሳምንት «በኢትዮጵያ የዉስጥ ጉዳይ የሚፈተፍቱ» እና «ኢትዮጵያዉያን ያልሆኑ» ያሏቸዉ ወገኖች፣ ብዙዎች እንደሚሉት ኤርትራን  ግብፅን ወይም ሌሎች ወገኖችን ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።

ፖለቲካ በጠመንጃ በሚዘወርበት በአፍሪቃ ቀንድ ስምምነቱ ያስኮረፋቸዉ ወገኖች ቢቀራረቡ በርግጥ አያስደንቅም።በጆርጅ ዋሽግተን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰርና በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ከወራት በፊት እንዳሉት ግን በአስመራና በአማራ ልዩልዩ ኃይላት መካከል ግንባር ከተፈጠረ የፌደራሉን መንግስትን ባያሰጋ እንኳን ችግር መፍጠሩ አይቀርም።

«ለማዕከላዊዉ መንግስት ወደፊት ስጋት ስለመሆን አለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።ችግር መፍጠሩ ግን ምንም አያጠራጥርም።ማዕከላዊዉ መንግስት ይህን ሁኔታ መቆጣጠር አለበት።ኤርትራ ከፋኖ ወይም ከአማራ ሚሊሺያ ጋር ሥላላት ግንኙነት አላዉቅም።ይሁንና ኤርትራዎች ፋኖን የሚደግፉ ከሆነ በኤርትራና በትግራይ ኃይላት መካከል መተማመን ለመፍጠር ያለዉን ዕድል በሙሉ የሚያጠፋ ነዉ።ኤርትራ የሰላም ስምምነቱን ገቢር ለማድረግ ተባባሪ እንዳልሆነች የሚያመለትም ነዉ።»

ከግራ ወደ ቀኝ አቶ ጌታቸዉ ረዳና ዶክተር አብይ አሕመድምስል Office of Prime Minister of Ethiopia

የኤርትራና የአማራ ኃይላት ወዳጅነትና የወዳጅነቱ ደረጃ  ለጊዜ ሒደት የሚተዉ ነዉ።የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግስት «የክልሎች ልዩ ኃይላትን ዳግም ለማደራጀት» ባለዉ ዘመቻ የአማራ ታጣዊዎችን ትጥቅ ማስፈታት ከጀመረበት ካለፈዉ ወር ወዲሕ ግን በመንግስትና በአማራ ኃይላት መካከል የተፈጠረዉ ጠብ እየተካረረ መምጣቱን ለማወቅ አስተንታኝ አያስፈልግም።

የተለያዩ የአማራ አካባቢዎች በተቃዉሞ ሰልፍ፣ በአድማ፣ መንገድ በመዝጋት፣ አልፎ አልፎም ቢሆን በተኩስ እየታወኩ ነዉ።የፈደራሉ መንግስት የፀጥታና የደሕንነት የጋራ ግብር ኃይል በተከታታይ በሚያወጣቸዉ መግለጫዎቹ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ ወይም ለመፈንቅለ መንግስት «ያሴሩ» ያላቸዉን የአማራ ታጣቂ፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኛና የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን ማሰሩን ወይም እንዲታሰሩ ማዘዙን እያስታወቀ ነዉ።

ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅወያ እንደሚሉት ከጎንደር ከተማ እስከ ሰሜን ሸዋ ይምሎ ጉብታ እየገንፈል-የሚሰክነዉ ዉጥረት አዲስ አበባ ዉስጥ ብዙም አይሰማም።ዐቢይ «ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ» ያሏቸው ማን ናቸው?

«እዉነቱን ለመናገር አዲስ አበባ ዉስጥ ቁጭ ብለሕ የምታየዉና የምታስተዉለዉ በጣም የተቆጠበ ነዉ።ነገሮች እየተከሰቱ ነዉ ከሚባልበት ቦታ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ምንም ዓይነት መረጃ አይመጣም።ጋዜጠኞች ከቦታዉ የሚያስተላልፉት መረጃም የለም።ትልቅ ዉጥረት መኖሩን ነዉ እንጂ የምገምተዉ የዉጥረቱን ወርድና ስፋት  ማወቅ አይቻልም።»

የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾች እንደሚሉት ኢንተርኔት በተዘጋበት፣የጋዜጠኞች መብት በተገደበበት፣ ህዝብ በፀጥታ ስጋት፣በጎሳ ጥቃት ጭንቀትና በኑሮ ዉድነት በተቃረጠባት ኢትዮጵያ ነፃና ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች ሳይቀሩ በተከታታይ እንደዘገቡት በአማራ ክልል የገዢዉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን ግርማ የሽጥላ ከተገደሉ ካለፈዉ ሚያዚያ 19 ወዲሕ ዉጥረቱ ተባብሷል።

ለጠቅላይ ሚንስትር ዐባይ የድጋፍ ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

የአማራ ክልል ዉጥረት በናረበት መሐል የኢትዮጵያ መንስግት ኦነግ ሸኔ በሚል ስም ባሸባሪነት ከፈረጀዉ ነገር ግን ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሰ) ብሎ ከሚጠራዉ አማፂ ቡድን ጋር የጀመረዉን ድርድር «ፌንጥ« ባዮች «የራስ ለራስ ንግግር» ፣ አንዳዶች «አንዱን ጥሎ-ሌላዉን አንጠልጥሎ» እያሉ ተችተዉት ነበር።ሌሎች ደግሞ መንግስት ከተጋባዉ ጋር እየተፋታ ከተፋታዉ ጋር እንደ ሙስሊሞቹ ወግ «ረጃዕቱ» የማለቱ አባዜ አድርገዉ አፊዘዉበታል።

ያም ሆኖ የአዲስ አበባና የአማራ፣የአዲስ አበባና የአስመራ ፍቅር ወይም የአዲስ አበባና የመቀሌ ጠላትነት «ነበር እንዲሕ ቅርብ ነዉ» በሚያሰኝበት መሐል ዛንዚባር-ታንዛኒያ ላይ የተጀመረዉ ድርድር ለሳላም አንድ ግን በጎ እርምጃነቱ አላጠራጠረም።

በፕሪቶሪያዉ ድርድር ስሜትና ሒደት የተቃኘዉ የዛንዚባሩ ድርድር ለቀጣይ ድርድር የተስፋ መሰረት መጣሉ አልቀረም።ይሁንና የፕሬቶሪያዉን ዉጤት የሚያስታዉሰዉ ወይም የሚጠብቀዉ ወገን  የመንግስትና የኦነሰ ተወካዮች ከ9ኝ ቀናት ድርድር በኋላ የሰላም ስምምነት ሳይፈራረሙ መለያየታቸዉን አሌ ብሎታል።

የሕግ ባለሙያና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅ ወያ ግን የተፋላሚ ኃዕላት ተወካዮች ፊት ለፊት መነጋገራቸዉ ራሱ ጥሩ ነዉ ባይ ናቸዉ።

«ዘጠኝ ቀናት ሙሉ ቁጭ ብለዉ ማዉራታቸዉ አዉንታዊ ገፅታዉን ነዉ የሚያሳየዉ ንግግሩን።ሀሳብ ለሐሳብ የማይግባቡበት ነገር ቢኖር ኖሮ ድርድሩ ከመጀመሪያዉ ይቆም ነበር።ሁለቱም ወገኖች ምን እንደተነጋገሩ፣ ምን ላይ እንደተስማሙ፣ምን ላይ እንዳልተስማሙ አለማዉራታቸዉም ደግሞ ፖሰቲቭ ነዉ።ይሕም ተግባብተዋል ማለት ነዉ።ላለማዉራት።»

የአማራ ክልል ልዩ ኃይልምስል Eduardo Soteras/AFP

ተደራዳሪዎች በየፊናቸዉ ባወጡት መግለጫ ድርድሩን ለመቀጠል ተስማምተዋል።መቼ፣ የትና  እና በምን ላይ እንደሚደራደሩ ግን ያዉ እንደ ዘጠኝ ቀኑ ድርድር ሒደትና ዉጤት ሁሉ በግልፅ አልተናገሩም።በድብቅ ተቀጣጥረዉ፣ በድብቅ ተነጋግረዉ፣ የተናጋገሩበትን ዉጤት ደብቀዉ፣በድብቅ ጊዜ ለድብቅ ዳግም ድርድር መቀጣጠራቸዉ ብዙዎች እንደሚሉት «እንወክልሐለን» የሚሉትን በተለይ በሁለቱ ጠብ ወገኑ የተገደለ-የተፈናቀለዉን ሕዝብ  የማወቅ መብት የሚጋፋ ነዉ።አቶ ባይሳ ግን የድርድሩን ዉጤትና የመጪዉን ድርድር ዕቅድ ይፋ ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ናቸዉ።

 የድርድሩ ሒደት፣ ዉጤትና የሚቀጥልበት ጊዜ አልታወቀም።የኢትዮጵያና የኤርትራ የወደፊት ግንኙነት እንዴትነት አልታወቀም።አማራ ክልል ያረበበዉ ዉጥረት የሚረግብበት ብልሐት አልታወቀም።ዛሬ ምስራቅ ሸዋ ዉልጪቲ አጠገብ የአፋር ክልል የአንድ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ተወካይ በሰዉ እጅ ተገድለዋል።የገዳዮች ማንነት አልታወቀም። የኢትዮጵያ ሰላም፣ የፖለቲካዊ ጉዞዋ ወዴትነትም እንደሁ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW