1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካኤርትራ

ማሕደረ ዜና፣ ኤርትራ ድግስ ወይስ ረብሻ

ሰኞ፣ ነሐሴ 29 2015

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ለካቢኔያቸዉ አባላት እንደነገሩት የኤርትራዉያን ድብድብና ረብሻ «ቀይ መስመር ያለፈ ነዉ» ረባሾች ከእስራኤል መባረር አለባቸዉ።

ቴል አቪቭ-እስራኤል ዉስጥ በተደረገዉ የኤርትራ አወዛጋቢ ድግስ ላይ የተነሳዉ ድብድብ
ቴል አቪቭ-እስራኤል ዉስጥ በተደረገዉ የኤርትራ አወዛጋቢ ድግስ ላይ የተነሳዉ ድብድብምስል Ohad Zwigenberg/AP/picture alliance

«የኤርትራዉያንን ባሕልና መከባበርን ሥርዓቱ መትቶታል» ተንታኝ

This browser does not support the audio element.

ኤርትራ። የሕዝቧን ብዛት በትክክል የቆጠረዉ የለም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚገምቱት ግን የሕዝቧ ቁጥር ሲበዛ 5 ሚሊዮን ሲያንስ ከ4 ሚሊዮን ያነሰ በዉ።ነፃነቷን ካወጀች 30 ዓመቷ።በሐገር ታሪክ በዚሕ አጭር ጊዜ፣ ካላት ትንሽ ሕዝብ ሚሊዮኖችን በማሰደድ ግን፣ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደመሰከሩት ከ10 የዓለም ሐገራት አንዷ ሆናለች።ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋርና  ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ የነፃነት ጦርነት፣ የድንበር ጦርነት፣ የትብብር ጦርነት እየተባለ  በጦርነት ማግስት በሌላ ጦርነት ወገኑን የሚገብረዉ ኤርትራዊ ሲሰደድ የባሕርና የበረሐ ሲሳይ፣ በሕይወት ሲገባ ደግሞ  እርስበርሱ ከመደባደብ፣ ከየተሰደደበት ሐገር ፀጥታ አስከባሪ ጋር ከመጋጨት አለማምለጡ ነዉ ዚቁ።ላፍታ እንዴት ለምን እንላለን አብራችሁን ቆዩ።

እነሱ «ፌስቲቫል» ነዉ የሚሉት።አዉሮጳ ዉስጥ ድሮ ቦሎኛ፣ ኢጣሊያ ኋላ ደግሞ የኤርትራ የነፃነት በዓል፣ ኤርትራዉያን የነፃነት ትግል የጀመሩበት እየተባለ በተለያዩ ሐገራት በየዓመቱ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ በጋ ይደገሳል።ከ2011 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በኮሮና ስርጭት ሰበብ ከመቋረጡ ዉጪ) ብዙ የኤርትራ ስደተኞች በዓሉን የሚያከብሩት ጊሰን ከተማ፣ ሔሰን ግዛት፤ ጀርመን ዉስጥ ነዉ።

ቴል አቪቭ-እስራኤል ዉስጥ በተደረገዉ የኤርትራ አወዛጋቢ ድግስ ላይ የተነሳዉ ድብድብምስል Ilia Yefimovich/dpa/picture alliance

                                                 ድግስና ድብድብ

ድግሱን የሚያዘጋጁና የሚደግፉት የድግሱ ዓላማ ባሕላዊና መዝናኛ ነዉ ባዮች ናቸዉ።

»ፖለቲካዊ ድግስ አይደለም።የማንኛዉም ሐገር (ስደተኛ) እንደሚያደርገዉ እኛም ፌስታ እናደርጋል።መብታችንም ነዉ።»

እሱም ቀጠለ።

«የኤርትራ ሰዎች ባሕል አለን።ምግብ፣ሙዚቃ ነዉ።ፖለቲካዊ አይደለም።»

ተቃዋሚዎች ግን ተቃራኒዉን ነዉ የሚሉት።ድግሱን የሚያዘጋጀዉ፣ታዳሚዎችን  የሚጋብዘዉ፣ በየድግሱ ከሚዋጣ፣ ከሚሸጥ ከሚለወጠዉ የሚገኘዉን ገንዘብ የሚወስደዉ የኤርትራ መንግስት ነዉ ባዮች ናቸዉ።እሷ አንዷ ናት።

«ምግብና መጠጥ ይሸጣል።ለኤርትራ ሥራዓት ገንዘብ ይዋጣል።»

የኤርትራዉያን ልዩነት ወደ ጠብ ንሮ በ2022 የጊስኑ የድግስ ስፍራ ሔሰንሐለን የኤርትራዉያን መደባደቢያ መድረክ ሆነ።ኤርትራዊ ስደተኛ ከኤርትራዊ ብጤዉ ጋር በዱላ፣በፍልጥ፣ በድንጋይ፣ በጠርሙስ፣ በጩቤና ቢላ ሳይቀር ይከታከት ያዘ።ፖሊስ እንዳስታወቀዉ በድብድቡ 33 ሰዎች ቆስሉ።ሰባቱ ፖሊሶች ናቸዉ።ድብድቡን ለማስቆም 300 ፖሊሶች መሠማራት ነበረባቸዉ።

የሔሰን ክፍለ ግዛት በተለይም የጊሰን ከተማ አስተዳደር በየዓመቱ የሚደረገዉን ድግስ ለመዝጋት ወስኖ ነበር።ነገር ግን ፍርድ ቤት ዉሳኔዉን ዉድቅ በማድረጉ ዘንድሮ ሐምሌ ሌላ ድግስ፣ ሌላ ድብድብ፣ ሌላ ጉዳት።በግጭት የታጀበው የኤርትራውያን የባህል ዝግጅት በጊሰን፣ ጀርመን

 «ድብድና ትርምስ በኤራትራ ፌስቲቫል-ጊስን ዉስጥ»-------ይላል ጋዜጠኛዉ።»

በድብድብ ረብሻዉ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ቆሰሉ።26ቱ ፖሊሶች ናቸዉ።መኪኖች፣ አዳራሾች፤ ለድግሱ የተዘጋጁ ንብረቶች ወደሙ።ፖሊስ ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰዉ አስሯል።ጥቂቱን ከስሷል።በሶስተኛ ሳምንቱ ተመሳሳይ ድግስ ስቶክሆልም-ስዊድን ዉስጥ ተዘጋጅቶ ነበር። ተመሳሳይ ድብድብ፣ ረብሻና ጥፋት።ስቶክሆልም-የኤርትራዉያን ግጭት በስዊድን

ጩቤ፣ ድንጋይ፣ዱላ፣ ክብሪት ወይም የታጠቁት ኤርትራዉያን ባበቀሉት ረብሻ 53 ሰዎች ቆስሉ።የስቶክሆልም ፖሊስ እንዳስታወቀዉ ከቁስለኞቹ ስምንቱ ክፉኛ ተጎድተዋል።ተደባዳቢዎችን ለመገላገል መሐል የገቡ 3 ፖሊሶችም ቆስለዋል።መኪኖች፣ዛፎችና ሌሎች ንብረቶች ጋዩ ወይም ተሰባበሩ።

የኤርትራ ድግስ ወደ ድብድብና ረብሻ ተቀየረ-ጊስን፣ ጀርመንምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

ኤርትራዊቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና በዌስት ለንደን  ዩኒቨርስቲ የስነ ልቡና መምሕርት ዶክተር ሰላም ኪዳኔ ኤርትራዊ ስደተኛ ከኤርትራዊ ወገኑ ጋር በየድግሱ መደባደብ፣መጎዳት፣ሌሎቹን መጉዳቱን «አሳዛኝ« ይሉታል።

«ድብድቦችም፣ አንዳድ ሥፍራ ቃጠሎዎችም፣ የድንኳን መፍረሶችም ነበሩ።የንብረት መዉደምም ነበረ።ይኸ ሁሉ በጣም እሚያሳዝን ነገር ነዉ።እነዚሕን ኢቬንቶችን እሚያዘጋጀዉ ኤርትራ ዉስጥ ሥልጣን የያዘዉ ሥርዓት ነዉ።ይኸ ሥርዓት አብዛኛዉን ነገር ከሕግ አግባብ ዉጪ ሆኖ ነዉ የሚያደርገዉ።»

 

                                                            የድብድብ ረብሻዉ መሠረት

ባለፈዉ ቅዳሜም ለኤርትራዉያን ዝክር ነበር።ሐሚድ ኢድሪስ አዋቴና ተከታዮቻቸዉ በ1961 ኤርትራን ከኢትዮጵያ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት የነፍጥ ዉጊያ የጀመሩበት 52ኛ ዓመት ዝክር ነበር።የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት ኤርትራዉያን ያደረጉት የነፍጥ ትግል ብዙ ጊዜ የፈጀ፣ ብዙ መስዕዋትነት የተከፈለበት ነዉ።

«የትጥቅ ትግል ሲጀመር ዋናዉ ዓላማ ሐገሪቱን ከኢትዮጵያ ሚሊታሪ ኦኮፔሽን ነፃ አዉጥቶ አንድ ዴሞክራሲያዊት ሐገር ለመፍጠር ነበር።ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል።»  

ሊዘከር የሚገባዉ።ዘንድሮም ቅዳሜ ተደገሰ።በርገን-ኖርዌ፣ዙሪክ-ስዊዘርላንድ የነበረዉ ድግስ ያለ ብዙ ረብሻና ድብድብ አበቃ።ኦፕፊኮንና ካንቶናል፣ ስዊዘርላንድ ለድብድብ የተሰላለፉት ኤርትራዉያን በፖሊስ ኃይል ተገላገሉ።የካንቶን ፖሊስ ቃል አቀባይ ራልፍ ሒርት

«ፖሊስ በርካታ ኃይል ነዉ ያሰፈረዉ፣ የካንቶናል ፖሊስና የሌሎች አካባቢዎች የፖሊስ ባልደረቦች ባደረጉት ጥረት እነዚሕን ቡድናት መለያየትና በመጨረሻም አካባቢዉን በሰላም እንዲለቁ ማግባባት ችለናል።»

የቴል አቪቭ እስራኤሉ ግን በርግጥ ከእስከ ቅዳሜዉ ሁሉ የከፋ ነበር።በድግሱ የታደሙና ድግሱን የሚቃወሙ ኤርትራዉያን ዘነዘና በሚያክል ዱላ ይናረቱ፣ በድጋይ ይፈነካከቱ፣ፖሊሶችን ሳይቀር ይደብድቡ ያዙ።ፖሊስ አንዳስታወቀዉ 150 ተደባዳቢዎች ቆስሉ።19ኙ ክፉኛ ተጎድተዋል።ፖሊስ እንዳለዉ 49 ባልደረቦቹ ተጎድተዋል።39 ተጠርጣሪዎች ታስረዋል።

መኪኖች፣ ለድግሱ የተዘጋጁ ንብረቶች ወደሙ።ድብድብ፣ ረብሻዉን ለማስቆም ፖሊስ ሔሊኮፕተር ሳይቀር ማዝመት ግድ ነበረበት።አቶ አብዱረሕማን እንደሚሉት ኤርትራዉያን ወጣቶች በየደረሱበት፣ በየድግስ ትርዒቱ የመደባደብ መጎዳዳት መሰረታዊዉ ምክንያት የአስመራ መንግስት የአገዛዝ ስርዓት ነዉ።

«ወጣቱ ሌላ ዓይነት ኑሮ እንዳይኖር ወደየወታደሮቹ ካምፕ ገብቶ እዚያ ልክ እንደባሪያ እንዲያገለግል ነዉ የተደረገዉ።የሰከንደሪ ስኩል መልቀቂያ ፈተና ራሱ በወታደራዊ ካምፕ ነዉ የሚያደርገዉ።ከዚያ በኋላ እንግዲሕ ወደጦርሜዳ ይላካል ወይም እዚያ እንደባሪያ ያገለግላል ማለት ነዉ።----ኤርትራዊዉ ባሕሉንና መከባበሩን ጠላት አድርጎ ነዉ ሲመታዉ የነበረዉ-ሥርዓቱ። የሱ ዉጤት ነዉ እንግዲሕ አሁን የምናየዉ ቫዮለንስ።»

በርካታ ኤርትራዉያን ስደተኞች አዉሮጳ የሚደርሱት አደገኛዉን የባሕር ጉዞ አቋርጦ ነዉምስል Joan Mateu Parra/AP/dpa

የሰባዊ መብት ተሟጋች ሰላም ኪዳኔም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸዉ።

«የሐገራዊ አገልግሎት ሚሊተሪ ሰርቪሱን ኢንዴፊኒት አድርጎ እነዚሕ በየጎዳናዉ የምናያቸዉን ወጣቶች በግፍ ካሐገራቸዉ እንዲወጡ ያደረገ ሥርዓት ነዉ።»

የኢጣሊያ የረጅም ዓመታት ቅኝ አገዛዝ፣ የብሪታንያ የ10 ዓመታት የበላይ ጠባቂነት አገዛዝ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ፌደሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ዉህደት፣ ከኢትዮጵያ ነፃ ለመዉጣት የ30 ዓመታት ጦርነት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የ2 ዓመታት የድንበር ጦርነት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የመተባበር ጦርነት።እና 30 ዘመናት ሕገ-መንግስት የለም።ፓርላማ የለም።ነፃ ፕረስ የለም።የኤርትራ አጭር ታሪክ።እንደገና ሰላም ኪዳኔ።በኤርትራውያን የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ 22 የጀርመን ፖሊሶች ተጎዱ

«የፕሬስ ይሁን፣ የኃይማኖት ነፃነት ይሁን፣ የመሰብሰብ ነፃነት ይሁን የለም።የኤርትራ ፓርላማ ከተሰበሰበ ፌብሪዋሪ 2002----ስለዚሕ እነዚሕ ልጆች ሸሽተዉ ወጥተዉ፣ ምድረበዳ፣ ባሕር ከዚያ ሁሉ ሰርቫይቭ አድርገዉ አሁን ከዚያ ሥርዓት አምልጠናል።ሕይወታችንን እንመራለን በሚሉበት ጊዜ ተመልሶ ይኸ ሥርዓት የሐገራቸዉ ሪፕሬዘንታቲቭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ባሉበት ኮሚኒቲዎች እንደ ሕገኛ፣ ያለምንም ከልካይ ገንዘብ ሬይዝ ሲያደርግ፣ ፖለቲካዊ ማኑቨርም ሲያደርግ---- እነዚሕ ልጆች ንዴታቸዉ እየበዛ  ነዉ የመጣዉ።»  

አቶ አብዱረሕማን።

ጊስን-ጀርመን በተደረገዉ የኤርትራ አወዛጋቢ ድግስ የተነሳዉ ድብድብ ለፖሊስም ተርፏልምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

«አዉሮጳ ዉስጥ 35 ዓመታት ተቀምጬያለሁ።ኤርትራዉያን የምንታወቀዉ በፒስፉልነስ ነበር።-----በነፃነት ትግሉ ጊዜ እንኳ በኢትዮጵያዉያንና በኤርትራኖች መካከል አንድም ጊዜ ቫዮለስ አልነበረም። ይኸ አዲስ ቫዮለንስ እንግዴሕ ሥርዓቱ ነዉ ያመጣዉ።ፌስቲቫሉ ለሴፕቴምበር ወይም ለነፃነት በዓል ሳይሆን ሥርዓቱ የሚያደርገዉ በሁለት ምክንያት ነዉ።----የዉጪ ምንዛሪ የሚሰበስብበት ነዉ።»    ወጣቱ ኤርትራዊ የአውቶብስ ሾፌር በቦን 

                                                               ኤርትራዉያን ይባረሩ ይሆን?

                           

የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናትን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካልንም።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ለካቢኔያቸዉ አባላት እንደነገሩት የኤርትራዉያን ድብድብና ረብሻ «ቀይ መስመር ያለፈ ነዉ» ረባሾች ከእስራኤል መባረር አለባቸዉ።

«ትናንት የሆነዉ ቀይ መስመር ያለፈ ነዉ።ረብሻ ነዉ።ደም ማፍሰስ ነዉ።ይሕ ልንቀበለዉ የማንችል ረብሻ ነዉ።ስለዚሕ የማደርገዉ የመጀመሪያዉ ነገር ህግ ለማስከበር ሲሞክሩ ለቆሰሉት ፖሊሶች ፈጥነዉ እንዲያገግሙ መመኘት ነዉ።በረባሾቹ ላይ ከሐገር ማባረርን ጨምሮ ጠንካራ ርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን።»

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW