1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና ዝክረ-2017 ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2018

2017 ዓመትም ላይመጣ ሔደ።ግጭት፣ዉዝግብ፣ የተፈናቃዮች ሮሮ የደመቀበት፣የኑሮ ዉድነት-የደሞዝ ጭማሪ ተስፋን ያጠወለገበት፣እገታ፣ ዘረፋ፣ ሥርዓተ-አልበኝነት፣ የጋዜጠኞች እስራት የተደጋገመበት ዓመት ነበር

አንካራ ታሕሳስ 2017።ከግራ ወደ ቀኝ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማህሙድ፣ የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ
አንካራ ታሕሳስ 2017።ከግራ ወደ ቀኝ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማህሙድ፣ የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድምስል፦ Murat Kula//TUR Presidency/Handout/Anadolu/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ ዝክረ-2017 ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

This browser does not support the audio element.

ያዉ እንደ ብዙ ሺሕ ቀዳሚዎቹ የኢትዮጵያዉኑ 2017 ዓመትም ላይመጣ ሔደ።ግጭት፣ዉዝግብ፣ የተፈናቃዮች ሮሮ የደመቀበት፣የኑሮ ዉድነት-የደሞዝ ጭማሪ ተስፋን ያጠወለገበት፣እገታ፣ ዘረፋ፣ ሥርዓተ-አልበኝነት፣ የጋዜጠኞች እስራት የተደጋገመበት ዓመት ነበር።በ2017 የባሕር-ወደብ እሰጥ-አገባ -ከግድብ ምረቃ ፌስታ ጋር ሲላተም፣ የኢትዮ-ሶማሊያ ስምምነት እፎይታ፣ በኢትዮ-ኤርትራ መዛዛት፣በግብፆች ቀረርቶ ሲጣፋ ሌላም ሌላ ብዙ አይተንበታል።ሲሰናበትም አየን።ዛሬ አምስተኛ ቀኑ።«ሰዉ ለነበረበትና ላለበት ዘመን እንጂ ላልነበረበትና ላለፈ ዘመን አላፊ አይሆንም» እንዲሉ ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሐብተወልድ፣ ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ በነበር የምንዘክረዉን የ2017ን አበየት ፖለቲካዊ ክንዉኖች በወፍበረር እንቃኛቸዉ፤ ከቻላችሁ አብራችሁኝ ቆዩ።

ግድብና ወደብ፣ የዉኃ ጥቅምና ጉዳት

2017 ኤርትራን፣ ሶማሊላንድን፣ ሶማሊያንና ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር አስማማም-አጣላ፣ ቱርክን ለሽምግልና ጋበዘም-ጣልቃ አስገባ፣ከበኒ ሻንጉል ጉሙዝ እስከ አዲስ አበባ ኢትዮጵያዉያንን አስደሰተም-አስከፋ ሰበብ ምክንያቱ ሁለትም-አንድም ነዉ ወደብና ግድብ።ዉኃ

ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ አምና በምንለዉ 2017 የኮሪደር ልማትን አዲስ አበባ ላይ ክፉኛ የተፈተነዉ ጎርፍ ነዉ።-ዉኃ፣ ቢሾፍቱዎችን በጨለማ ያዳፈነዉ፣ ወለጋና ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ በትንሹ 10 ሰዎችን የገደለዉ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ላይ ሺዎችን ያፈናቀለዉ፣ ደቡብ ወሎ ዉስጥ የተፈናቃዮችን መጠለያ ጣቢያ ያጠፈዉ ጎርፍ ነዉ-ዉኃ።ሥደተኞችን የበላዉ-ባሕር።

በተለያየ ቅርፅና ሥም-የሚታይና የሚጠራዉ ዉኃ ቢያንስ በ2017 ለኢትዮጵያዉያን የጠብም-የፍቅርም፣ የደስታም-የሐዘንም፣ የጉዳትም-የጥቅምም ሰበብ ምክንያት መሆኑን ያስተዋለዉ ፈይሰል አብራር በ,ፌስ ቡክ ባሰፈራት አጭር ፅሑፍ ዓመቱን «የዉኃ ዘመን ብንለዉስ» ዓይነት ይላል።ያስኬዳል።ዓመቱ የጀመረዉ ግን በመሬት መንቀጥቀጥ ነበር።

መሬት መንቀጥ-አፋር፣ ሹም ሽር አዲስ አበባ

መስከረም አጋማሽ አዋሽ-ፈንታሌን ያርገፈገፈዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ያንድ ቀን ምናልባት ያንድ ሰሞን አስደንጋጭ አደጋ መስሎ ነበር።ግን አልቆመም።የመሬት መንቀጥቀጥ ለአዋሽ፣ ለመተሐራ፣ ለዱለቻ፣ለዶፈን-ቦለሐሞ ከተሞችና ለየአካባቢዉ ነዋሪዎች ጭንቀት፣ ለሩቁ ኢትዮጵያዉ ሥጋት፣ ለተቀረዉ ዓለምም ርዕሥ እንደሆነ እስከ መጋቢት ማብቂያ ድረስ ቀጠለ።

አዋሽ-ፈንታሌና አካባቢዉን በተደጋጋሚ የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ካወደማቸዉ ሕንፃዎች አንዱ።በሬክተር መለኪያ እስከ 5.9 የደረሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ 330 ጊዜ ተደጋገሟልምስል፦ private

በሬክተር መለኪያ እስከ 5.9 የደረሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ 330 ጊዜ ተ,ደጋገመ።በትንሽ ግምት 3 ሰዉ ገደለ።የስኳር ፋብሪካ፣ 25 ትምሕርት ቤቶች፣ በርካታ የንግድ መደብሮችና በሺ የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች አወደመ።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቃለ።

የአፋር፣ የአሮሚያና የአማራ ክልሎችን የሚያዋስኑ አካባቢዎች ነዋሪዎች በመሬት መንቀጥቀጥ መደናገጥ፣ መፈናቃል እንደጀመሩ አዲስ አበባ ለዓመቱ የመጀመሪያዉን ሹም ሽር አደረገች።ወይም ዲፕሎማትዋ ፕሬዝደንት ወይዘሮ ሳሕለወርቅ ዘዉዴ በዲፕሎማቱ ሚስትር ታዬ እፅቀ ሥላሴ ተተኩ።መስከረም 27 ነበር።

በ1984 ፎሮም 84 በተባለዉ ሥብስብ በኩል የኢሕአዲግን ፖለቲካ የተቀየጡት ታዬ እፅቀ ሥላሴ፣ በተለያዩ ሐገራት በዲፕሎማትነት፣በአምባሳደርነትና ኋላም ለ8 ወራት ግድም በዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነት አገልግለዋል።የፕሬዝደንትነቱን ሹመት ላፀደቀላቸዉ ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በፖለቲካ ቀዉስ የምትናጥ ሐገር መሆኗን አልካዱም።

«የምትሻገር ሐገር በማይሻገር ሐሳብ እየተናጠች ቆይታለች።የሚታረምና የሚታረቅ የፖለቲካ ልዩነት እንደማይታረምና እንደማይታረቅ ተደርጎ በመሰራቱ ሐገር በማይጠራ የፖለቲካ ሳንክ እንድትንገላታ ተገድዳለች።»

ኢትዮጵያ ከትግራይ እስከ ኦሮሚያናሶማሊያ ክልሎች በፖለቲካ ዉዝግብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በነፍጥ ግጭት፣ በብዙዎቹ አካባቢዎች በእገታ፣ ዘረፋና ሥርዓተ አልበኝነት እንደተናጠች በ2017ም ቀጥላለች።

ሹም ሽሩም ቀጠለ።ጥቅምት 8 የፍትሕ ሚንስትር የነበሩት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ አምባሳደር ታዬ የለቀቁትን የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነት ሥልጣን ሲይዙ፣የዶክተር ጌድዮን ባለቤት ወይዘሮ ሐና አርአያ ሥላሴ የባለቤታቸዉ የነበረዉን የፍትሕ ሚንስርነትን ሥልጣን ተሾሙ።ከአንድ ቤት ሁለት ሹመት ታዛቢን ማነጋገሩ አልቀረም።

የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ታዬ እፅቀ ሥላሴ።የመስከረም ማብቂያ 2017 የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሆነዉ ተሾሙ።የፕሬዝደንትነቱን ሹመት ላፀደቀላቸዉ ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በፖለቲካ ቀዉስ የምትናጥ ሐገር መሆኗን አልካዱምምስል፦ Solomon Muchie/DW

የዚያኑ ቀን  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚንስትር ደ ኤታ የነበሩት ሰላማዊት ካሳ የቱሪዝም ሚንስትር ሆነዉ ተሾመዋል።

ከሶማሊያ ጋር ሠላም፣ ከኤርትራ ጋር ጠብ

ታዬ እፅቀ ሥላሴ እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የጀመሩት ድርድር ለስምምነት በቃ።ኢትዮጵያ ታሕሳስ 2016 ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ሥምምነት በመፈራረሟ ከሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ጋር የገጠመችዉ ጠብ በቱርክ ሸምጋይነት በስምምነት አበቃ ታሕሳስ 2፣ 2017 ማታ።አንካራ።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን የአንካራ መግለጫ (Declaretion) የተባለዉን ሥምምነት ያፈራረሙት የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን ሥምምነቱ «ወዳጅ» ያሏቸዉን የሁለቱን ሐገራት «የወደፊትግንኙነት» እንጂ ያለፈዉን ጠብ የሚመለከት አይደለም።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽማሕመድም መንግስታቸዉ ከኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝብ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ቃል ገቡ።

«ለጋራ ጥቅማችን ሥንል በጋራ ለመልማት እንሰራለን።ለዚሕ ስኬት ሶማሊያ አስተዋፅኦ ታደርጋለች።ከኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝብ ጋር ለመስራት ዝግጅቱ ነን።»

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ሠላማዊ እንደሆነ አ,ረጋገጡ።

«ኢትዮጵያ ደሕነቱ የተረጋገጠና አስተማማኝ የባሕር መድረሻ የማግኘት ፍላጎትዋ ሰላማዊ መሆኑን  እንዳረጋግጥ ይፈቀድልኝ።»

ሶማሊላንድም አዲስ መሪ መረጠች።ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችዉ የመግባቢያ ሰነድ ይፍረስ-ይቀጥል ግን በግልፅ አልተነገረም።ግብፅና ኤርትራን ከሞቃዲሾ ጎን ያሰለፈዉ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾዎች ጠብ ግን በመሪዎች የጉብኝትና አፀፋ ጉብኝት ካንጀትም ሆነ ካንገድ እንደረገበ ዓመቱ በአ,ዲስ ዓመት ተተክቷል።

ከግራ ወደ ቀኝ የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ።ሞቃዲሾ የካቲት 2017 ምስል፦ Presidency of Somalia/Anadolu/picture alliance

በ2010 ጣራ ነክቶ የነበረዉ የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎች ጠብ እየናረ ነበረ።መስከረም መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኘዉን መሥመር መዝጋቱ ተነገረ።ከዚያ በ,ፊት በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ፍቅር ላይ የተመሠረተዉ የሁለቱ ሐገራት አዲስ ወዳጅነት ምልክት ከነበሩት አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከና ወደ አሥመራ በቀን ሁለቴ የሚያደርገዉን በረራ አቋርጦ ነበር።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሥፍን ጣሰዉ 2017 ሊብት ዕለታት ሲቀሩት እንዳስታወቁት ኩባንያቸዉ በረራዉን ለማቆም የተገደደዉ አየር መንገዱ ኤርትራ ባንክ ዉስጥ የሚገኝ ገንዘቡን እንዳያንቀሳቅስ የኤርትራ መንግሥት በማገዱ ነዉ።

የኢትዮጵያ የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸዉ በሰጡት መግለጫ ግን የሁለቱ ሐገሮች ግንኙነት ሠላማዊ ብለዉታል።

«ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ሠላማዊ ነዉ።ግንኙነቱ እንደቀጠለ ነዉ።ግንኙነቱ በነበረበት ሁኔታ እንደቀጠለ ነዉ።»

መስከረም 30 ነበር።

«የቀይ ባሕር ሥሕተት ይታረማል» ጠቅላይ ሚንስትር ዐባይ አሕመድ

ኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግን የግንኙነት መሻከር ሊሸሽጉት አልቻሉም።ጥቅምት ላይ ያኔ ከኢትዮጵያ ጋር ለጠብ የምትጋበዘዉን የሶማሊያንና  እስካሁንም ኢትዮጵያን በክፉ የምታየዉን የግብፅ መሪዎችን አሥመራ ላይ አስተናገዱ።ሕዳር ላይ በሰጡት መግለጫ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ፕሪቶሪያ ላይ የተፈራረሙትን የሰላም ሥምምነትን አጣጥለዉ ነቀፉት።

«ፕሪቶሪያ መጣ፣ ፕሪቶሪያ አልመጣ ፕሪቶሪያ እኛን አይመለከተንም።የፕሪቶሪያ ሥምምነት እንደግፈዋለን አንደግፈዉም ብለን የምንናገርበት ምክንያት የለም።ጦርነቱን የሚያስቆም ሁኔታ መጣ።እሺ ከፕሪቶሪያ በኋላስ ምንድነዉ?»

ጠየቁ አንጋፋዉ ገዢ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ፣ የኤርትራ 33ኛ  የነፃነት ዓመት ግንቦት 16 ቀን ሲከበር ለሕዝብ ያደረጉት ንግግር ደግሞ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጠብ ጠመንጃ ሊያማዝዝ ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል።ፕሬዝደንት ኢሳያስ በዚሕ ንግግራቸዉ ኦሮሙማ፣ ብልፅግና፣ አፋር፣ ቀይ ባሕር እያሉ መጠቃቀስና መተቸታቸዉ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን አስቆጥቷልም።

በ2010 ጣራ ነክቶ የነበረዉ የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎች ጠብ እየናረ ነበረ።መስከረም መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኘዉን መሥመር መዝጋቱ ተነገረምስል፦ DW

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ በየአጋጣሚዉ በሰጧቸዉ መግለጫዎችና ማብራሪያዎች ኤርትራን በተለይም ጠቅላይ ሚንስትሩ «ኢሱ» እያሉ ያቆለጳጵሷቸዉ የነበሩትን ፕሬዝደንት ኢሳያስን መዉቀስ-ማጣጣላቸዉ ሥጋቱን አንሮታል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃምሌ ማብቂያ የሰጡት መግለጫ ደግሞ መንግሥታቸዉ የወደብ በተለይም የቀይ ባሕር በርን ለማግኘት ቁርጥ ፍላጎት ያሰደረ መሆኑን ጠቋሚ፣ አስመሮችን አበሳጪ ብጤ ነበር።

«ቀይ ባሕር እኮ የዛሬ 30 ዓመት ነበር እኛ እጅ።የቀይ ባሕር የዛሬ 30 ዓመት-የትናንትና ታሪክ ነዉ።የተፈጠረዉ ሥሕተት ትናንትና ነዉ።ነገ ይታረማል ከባድ አይደለም።የሺ ዓመት ያልተሞከረ ነገር ነዉ የተፈታዉ።እነ ቀይ ባሕር ያሉ ካባይ ያነሰ ነገር ነዉ።»

ፕሬዝደንት ኢሳያስ ሕዳር ላይ ሥለ ከፕሪቶሪያ ሥምምነት በኋላ ምን ተከተለ በማለት ያነሱት ጥያቄ ግን ተገቢ መልስ የሚያሻዉ ይመስላል።ሥምምነቱ በእርግጥ መቶ ሺዎችን የፈጀዉን፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉን ትግራይን፣ አማራንና አፋር ክልሎችን ያወደመዉን ጦርነት አቁሟል።

የሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ሲቆም አማራ ክልል ላይ የተጫረዉ ግጭት በ2017ም ቀጥሏል።ግጭቱ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አሳጥቷል።በሺ የሚቆጠሩ አፈናቅሏል።ትምሕርት ቤቶች፣ ሐኪም ቤቶች፣ ሌሎች የመሠረተ ልማት አዉታሮች ወድመዋል።

አንድ የፋኖ ቃል አቀባይ እንዳሉት ቡድናቸዉ «የብልፅግና ሥርዓት ካሉት መንግሥት ጋር አይደራደርም።

«ከብልፅግና ሥርዓት ጋር እኛ የማንደራደረዉ ብልፅግና ሥርዓት ለድርድር የማይቀርብ ፈፅሞ የረከሰ ሥርዓት ሥለሆነ ነዉ።»

ድርድር የለም።አሸናፊና ተሸናፊም የለም።ሕዝብ ግን ይሰቃያል።ይገደዳል።ይዘረፋል።ይሰደዳል።ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት የተጀመረዉ በኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሰራዊትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የሚደረገዉ ዉጊያም እንቀጠለ ነዉ።

ሽም-ሽር፣ ዉዝግብና እሰጥ አገባ- መቀሌ

የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ባበቃ ማግሥት ሕወሓት ከፌደራል መንግሥት ጋር የገጠመዉ ዉዝግብ አጉዞ አጉዞ አንጋፋዉን ፓርቲ ከፓርቲነት አሳግዶታል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት ሕወሓት የፖለቲካ ፓርቲ እዉቅና የለዉም።የካቲት 6 አለ።

የሕወሓት ፖለቲከኞች በጋራ ከፌደራሉ መንግስት ጋር የገጠሙት ዉዝግብ ሲቀጥል እርስበርስ የሚያደርጉት የስልጣን ሽኩቻ ግን መጋቢት 30 ላይ አበቃ። ሲቪሉ፣ የሕግ ባለሙያዉ፣ ወጣቱ ጌታቸዉ ረ,ዳ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ ፕሬዝደንትነት ሥልጣን ተወግደዉ ጄኔራሉ፣ የጦር ኃይል አዛዡ፣ ሽማግሌዉ ታደሰ ወረደ ተሾሙ።

አቶ ጌታቸዉ የመሠረቱት ስምረት ፓርቲ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር፣ የሕወሓት የፌደራል መንግስቱ የገጠሙት ዉዝግብ ግን ለዉጊያ እንዳሰጋ 2017 ተጠናቀቀ።የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሥርዓት ለወጥ እንዲደረግ  ጠንካራ ጥሪ አስተላልፈዉም ነበር።

የሥርዓት ለዉጥ የትግል ጥሪ-ኮኮስ

ባለፈዉ ኃምሌ ወደ 30 የሚጠጉ ኢትዮጵያዉን የአደን ባሕረ ሰላጤን ለመሻገር ሲሞክሩ አደን ባሕረ ሰላጤ ዉስጥ ማለቃቸዉን ምክንያት በማድረግ ኮኮስ የተባለዉ ስብስብ የሚያስተናብራቸዉ 7 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሥርዓት ለዉጥ ለማድረግ ሕዝቡ ለሰላማዊ ትግል እንዲነሳ ጠይቀዋል።የንቅናቄዉ አባል የሆነዉ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አማኑኤል ሞጊሶ

ነሐሴ 2 ነበር።የኢትዮጵያ ሐኪሞች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸዉ በመበራዊ መገናኛ የከፈቱት ዘመቻ፣ በየሐኪም ቅጥር ግቢዉ ያደረጉት ሰልፍና አንዳድ ሥፍራ የጠሩት አድማ ብርዥ ጥርዥ ከማለቱ የአድማ አስተባባሪዎችና ሐኪሞች ታሰሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በከፊል።ግድቡ ባለፈዉ ጳጉሜ 4 ቀን 2017 በይፋ ተመርቋል።ግብፅ የግድቡን ግንባታና ምረቃ ተቃዉማለችምስል፦ Luis Tato/AFP

በርካታ ጋዜጠኞች የታሰሩበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ለረሐብ መጋለጣቸዉን በተደጋጋሚ ያስታወቁበት፣ በርካታ ሰዎች የታገቱ፣ የተዘረፉበት፣ የኑሮ ዉድነት ብዙ ህዝብን ያሰቃየበት ዓመት ሲገባደድ የመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግላቸዉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቃል ገቡ።

በሹም ሽር የተጀመረዉ ዓመት ነሐሴን በሽር አበቃ።በብሔራዊ ባንክ ገዢነት ሁለት ዓመት ያገለገሉት ማሞ ምሕረቱ ከሥልጣን ተሻሩ ወይም አንዳዶች እንደዘገቡት በፈቃዳቸዉ ሥልጣን ለቀቁ።ነሐሴ 28 ነበር።ጳግሜ 4 2017 የሕዳሴ ግድብ ተመረቀ።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ።

«የሕዳሴ ግድብን የሚተካከል፣ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚዉል የኑክሌር ፕላንት በቅርቡ ሥራ ትጀምራለች።»

2018 የብዙ ግዙፍ የልማት አዉታሮች መመረቂያ፣ ወይም መጀመሪያ ተስፋን አንጠልጥሎ ባተ።መልካም አዲስ ዓመት

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW