1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የሁለት ጉባኤዎች አጭር ወግ

ሰኞ፣ የካቲት 10 2017

የሐገራት መሪዎች፣ ሚንስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የማሕበራት ሊቃነ መናብርት፣ ባለሙያዎች፣ የሠላምን ጥቅም፣ የዴሞክራሲን ፋይዳ፣ ተባብሮ የመሥራትን አስፈላነትን፣ ግጭት፣ጦርነት፣ አለመግባባት ያደረሱና የሚያደርሱትን ጉዳት የሚገልፁ፣ዉብ፣አማላይ፣ ማራኪ ቃላትን በየአዳራሹ አዘነቡት።በነዚያዉ ቃላት ተጠዛጠዙባቸዉም

የጀርመኑ አንጋፋ ፖለቲከኛ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሥለ ዓለም ያለዉ ዓመለካከት ከአብዛኛዉ ዓለም የተለየ መሆኑን አስታዉቀዋል።
የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር።ሽታይንማየር 61ኛዉን የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ባለፈዉ አርብ በንግግር ሲከፍቱ።ምስል፦ Boris Roessler/dpa/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የሁለት ጉባኤዎች አጭር ወግ

This browser does not support the audio element.

 

ካለፈዉ አርብ እስከ ትናንት ዕሁድ ድረስ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ፣ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ ደግሞ ሙኒክ-ጀርመን ላይ ተደርገዋል።የሁለቱ ጉባኤዎች ዐብይ ትኩረት ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እስከ ዩክሬን የሚደረጉ ጦርነቶች የሚቆሙበትን ብልሐት መፈለግ ነዉ።የሐገራት መሪዎች፣ ሚንስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የማሕበራት ሊቃነ መናብርት፣ ባለሙያዎች፣ የሠላምን ጥቅም፣ የዴሞክራሲን ፋይዳ፣ ተባብሮ የመሥራትን አስፈላነትን፣ግጭት፣ጦርነት፣ አለመግባባት ያደረሱና የሚያደርሱትን ጉዳት የሚገልፁ፣ዉብ፣አማላይ፣ ማራኪ ቃላትን በየአዳራሹ አዘነቡት።በነዚያዉ ቃላት ተጠዛጠዙባቸዉም። ጉባኤተኞች ሥለሠላም፣ የጋራ ትብብር እየሰበኩ በሐሳብ፣ አላማና ግብ መለያየት፣ በተቃራኒ አቅጣጫ ለመጓዝ መወራረፍቸዉ ነዉ ዚቁ።ጦርነቶቹም ቀጥለዋል።የሁለቱ ጉባኤዎች አንድነት-ልዩነት ቁንፅል ወግ መነሻ፣ የጦርነቶቹ መቀጠል ማጣቃሻ፣ የዓለም ሠላም መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

የጉባኤ ሳምንት ትናንት አበቃ።ዛሬ ግን ፓሪስ-ፈረንሳይ የአዉሮጳ መሪዎችን ጉባኤ እያስተናገደች ነዉ።ሪያድ-ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ነገ የዩናትድ ስቴትስና የሩሲያን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባን ለማስተናገድ ጠብ-እርግፍ እያለች ነዉ።የሁለቱ ጉባኤዎቹ ሳምንት፣ በጉባኤ-በስብሰባ ሳምንት ተተካ።የፓሪስ-ሪያዱ ጉባኤ-ሥብሰባዎች ዐብይ አላማ ሩሲያና ዩክሬን የገጠሙት ጦርነት በሰላም የሚፈታበትን ብልሐት መፈለግ ነዉ።

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፊሌክስ ሼሴኬዲ ሐገራቸዉ ዉስጥ በሚደረገዉ ጦርነት ምዕራባዉያን መንግሥታት ለመንግስታቸዉ ድጋፍ እንዲሰጥ ለመጠየቅ በሙኒኩ ጉባኤ ላይ ተገኝተዉ ነበር።ምስል፦ Michaela Stache/AFP

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዜለንስኪ ግን ባለፈዉ ሳምንት ሙኒክ-ጀርመን ላይ ተስይሞ በነበረዉ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ ላይ እንዳሉት ዩክሬን ባልተወከለችበት |ሥለዩክሬን የሚደረግ ሥምምነትን አትቀበልም።

«ዩክሬን፣  እኛ ባልተሳተፍንበት ከጀርባችን የሚደረግ ዉልን ጨርሶ አትቀበልም።»

ዛሬ ፓሪስ በተደረገዉ ጉባኤ ላይ ዩክሬን ተካፍላለች።የሪያዱ ስብሰባ ግን የአሜሪካና የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንጂ ዩክሬን ሥለመጋበዝ-አለመጋበዟ እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በግልፅ የተዘገበ ነገር የለም።ሩሲያ ባንፃሩ በሙኒኩም በዛሬዉም  ጉባኤ ላይ አልተጋበዘችም።ሪያድ ግን ዋና ተሳታፊ ነች።

የሰላም ጥሪ ከአዲስ አበባ ጦርነት ካርቱም

ዓለም ወትሮም የድንቅ ፖለቲካዊ ድራማ መድረክ ናት ይባላል።ሠሞኑን ደግሞ ይበልጥ እያስደመች ነዉ።አዲስ አበባ ግን ዛሬ እንግዶችዋን ሥትሸኝ ዉላለች።

በየጊዜዉ የሚደረገዉ የፖለቲከኞች ጉባኤ፣ ሽኩቻ፣ንትርክ፣የነዋሪዎች የኑሮ ጥድፊያ በቅርቡ ደግሞ የኮሪዶር ልማት የሚያካልባት አዲስ አበባ ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ዲፕሎማቶች፣ጋዜጠኞች፣የመብት ተሟጋቾች ሲርመሰመሱባት ነበር።

ዘግየት ብለዉ ከአርብ ጀምሮ ደግሞ፣ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች እንዳሉት፣ 29 ፕሬዝደንቶች፣ ሶስት ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ አራት ጠቅላይ ሚንስትሮች፣ አንድ ንጉስ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሚንስትሮች፣አምባሳደሮች፣ጋዜጠኞች፣አቀንቃኞችንና ተንታኞች አጨናንቀዋት ነበር።ከእንግዶችዋ አንዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ነበሩ።ከጉባኤተኞቹ ዋና ዋና ርዕሶች ደግሞ ሁለተኛዉ የሱዳን ሠላም።ጉቴሬሽ ሱዳንን በሚመለከት ብዙዎቹ መሪዎች በብዙ ቃላት ያሉትን ባጭሩ ቀመሩት።

«ሱዳን እጅግ የከፋ ቀዉስ የሚንጣት ጭካኔ የሚፈፀምባት ሐገር ሆናለች።ቀዉሱ ወደ አካባቢዉ በፍጥነት እየተዛመተ ነዉ።እና ቀዉሱ የአፍሪቃ ሕብረትንና የተቀረዉ ዓለም አቀፍ ማሕበረብን ሰፊ፣ ዘላቂና አስቸኳይ ትኩረት ይሻል።በተለይ ዉጊያ በሚደረግበት አካባቢ ሰብአዊ ርዳታ ማቅረብ ሲበዛ አስቸጋሪ ሆኗል።»

የአፍሪቃ መሪዎች ለሱዳን ሕዝብ መርጃ ገንዘብ አዋጥተዋል።የሱዳን ተፋላሚዎች ዉጊያ እንዲያቆሙ ጠይቀዋልም።አዲስ አበባ ላይ የሱዳን ሕዝብ ሥለመገደል፣ መበደል፣ መሰደዱ፣ ሥለርዳታ፤ ጦርነቱ ሥለሚቆምበት መንገድ ቃላት ሲንቆረቆሩ ርዕሠ ከተማ ካርቱም፣ አል-ፋሻር፣ ዘምዘም መድፍ-አዳፍኔ ያጓራባቸዉ ነበር።

የሱዳን መከላከያ ጦር የካርቱምን ሰሜናዊ ቀበሌና ምሥራቃዊ ካርቱምን ከደቡባዊ ካርቱም ጋር የሚያገናኘዉን ድልድይ መቆጣጠሩን አስታዉቋል።ጦርነቱ ቀጥሏል።የአዲስ አበባ ጉባኤተኞች ቀዳሚ ርዕሰ ምሥራቃዊ ኮንጎ ዉስጥ የሚደረገዉ ጦርነት ነበር።

የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ።በጉባኤዉ ላይ 29 ፕሬዝደንቶች፣ ሶስት ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ አራት ጠቅላይ ሚንስትሮች፣ አንድ ንጉስ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሚንስትሮች፣አምባሳደሮች፣ጋዜጠኞች፣አቀንቃኞችና ተንታኞች ተገኝተዉ ነበርምስል፦ Solomon Muchie/DW

የሼሴኬዲ ጉዞ፣ የM23 ድል፣ የአፍሪቃ ሕብረት ማሳሰቢያ

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ሼሴኬዲ ጠቅላይ ሚንስትራቸዉን አዲስ አበባ ልከዉ እሳቸዉ አርብ ሙኒክ ነበሩ።የሙኒክ ጉባኤተኞች በቋፍ፣ድግፍግፍ ለቆሞዉ የሼሴኬዲ መንግሥት ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።ይሁንና ሼሴኬዲ እንደተመኙት ሐገራቸዉን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ትወጋለች የምትባለዉ ርዋንዳ ለመቅጣት በግልፅ ያሳለፈዉ ዉሳኔ የለም።

የአዲስ አበባ ጉባኤ ግን የምሥራቃዊ ኮንጎን አብዛኛ አካባቢዎች የተቆጣጠረዉ የM23 አማፂ ቡድንና ደጋፊዎቹን በግልፅ አዉግዟል።ትጥቅ እንዲፈቱ ጠይቋልም።የአፍሪቃ ሕብረት የፖለቲካ፣የሠላምና የፀጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዮኢ ርዋንዳን በስም አልጠቀሱም።ይሁንና  እንደዲፕሎማሲዉ ወግ «የM23 ደጋፊዎች» ብለዋታል።

«እኛ ሁላችንም፣ በምሥራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሰበብ ግልፅ አካባቢያዊ ጦርነት ይጫራል ብለን በጣም በጣም እንሠጋለን።ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ M23 ና ደጋፊዎቹ ትጥቅ እንዲፈቱ፣ ከጎማ አዉሮፕላን ማረፊያና ከሌሎች በኃይል ከያዟቸዉ አካባቢዎች ለቅቀዉ እንዲወጡ በድጋሚ እናሳስባለን።»

የአፍሪቃ መሪዎች ዉሳኔ፣ መግለጫ ከአዲስ አበባ ሲናኝ የሙኒክ ጉባኤተኞች የፕሬዝደንት ሼሴኬዲን ማብራሪያ ያዳምጡ ነበር።እዚያዉ ምሥራቃዊ ኮንጎ ግን በሩዋንዳ የሚደገፈዉ M23 አርብ የቡካቩ አዉሮፕላን ማረፊያን ቅዳሜ ከተማይቱን ተቆጣጠረ።

የአዉሮጳ አሜሪካኖች ንትርክ

ሼሴኬዲ ሙኒክ ከገቡበት ካለፈዉ አርብ ጀምሮ የድጋፍ ጥያቄያቸዉን በይፋም-በአንድ ለአንድ ዉይይትም ለማቅረብ ካንዱ አዳራሽ ወደ ሌላዉ ሲሽከረከሩ የአዉሮጳና የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጆች በቃላት ይጠዛጠዙ ነበር።61ኛዉን ጉባኤ በይፋ የከፈቱት የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ናቸዉ።የዓለም ሕግና ሥርዓት ሊከበር ይገባል አሉ አንጋፋዉ የጀርመን ፖለቲከኛ።

 «እርግጠኛ የሆነዉ ነገር፣አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ሥለዓለም ከኛ የተለየ አመለካከት አለዉ።መሠረት ለያዙ ደንበች፣ወዳጅነትና መተማመን ደንታ የለዉም።ይሕን ልንቀይረዉ አንችልም።መቀበል አለብን።ለንጋፈጠዉ ይገባል።ይሁንና  ይሕ የዓለም አመለካከት ዋና ተፅዕኖ አድራጊ እንዲሆን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፍላጎት እንደሌለዉ አምናለሁ።ለሕግና ደንብ አለመገዛት የዓለም ሥርዓት አብነት ሊሆን አይገባም።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝደንት JD ቫንሴ አፀፋ ለብዙዎች አስደንጋጭ፣አስፈሪ፣ ግን ያልተጠበቀ አልነበረም።ቀኝ አክራሪዉ ፖለቲከኛ በአዉሮጶች ላይ የቃላት ናዳቸዉን ያወረዱት ቅኝ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች አዉሮጳ ዉስጥ ያሻቸዉን ለምን አያደርጉም በሚል ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝደንት JD ቫንሴ በ61ኛዉ የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ።ቫንስ አዉሮጳን የሚያሰጋዉ እራስዋ ከአዉሮጳ ዉስጥ የሚታየዉ ነባር እሴትን የመሸርሸር አዝማሚያ ነዉ ይላሉ።ምስል፦ THOMAS KIENZL/AFP

ሩሜንያ ዉስጥ ተደረጎ በነበረዉ ምርጫ ቀኝ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ያሸንፋሉ ሲባል፣ ዉጤቱ መሠረዙን  አሜሪካዊ ፖለቲካኛ ነቀፉት።በሙኒኩ ጉባኤ ቀኝ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች አለመጋበዛቸዉን ተቃወሙ።እና የመናገር ነፃነትን አዉሮጳ ዉስጥ እየተሸረሸረ ነዉ-አሉ።ሰዉዬዉ በዚሕ አላበቁም።ለአዉሮጳ የሚያሰጋዉ አዉሮጳ ነባር እሴቷን ማጣቷ እያሉ ቀጠሉ።

«አዉሮጳን በተመለከተ በጣም የሚያሰጋዉ ሩሲያ፣ቻይና ወይም ማንኛዉም የዉጪ ኃይል አይደለም።እኔ በጣም የማያሳስበኝ ከዉስጥ የሚመጣዉ ሥጋት ነዉ።አዉሮጳ ከአሜሪካ ጋር ከምትጋራዉ መሠረታዊ እሴቶችዋ ማፈግፈጓ ነዉ።»

የትራምፕ መርሕ፣ የአዉሮጳ ዝግጅት

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምፕየፖለቲካ መርሕ መሠረት አሜሪካ ትቅደም ነዉ።የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሜሪካንን ለማስቀደም የሚከተሉት መርሕ፣ የሚሰጡት አስተያየት የሚወስዱት ርምጃም የቅርብ ነባር ወዳጆቻቸዉን ምዕራብ አዉሮጶችን ሳይቀር እያስቀየመ ነዉ።

የጋዛ ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ ዩክሬን ጦርነት የሚፈታበት ሥልት፣ ከሩሲያና ከቻይና ጋር የሚኖራቸዉ ትብብር፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ተልዕኮና ወጪ፣ የዓለም ንግድ ሥምነት፣ የተፈጥሮ ጥበቃ፣ የቴክኖሎጂ ልዉዉጥ ለአዉሮጳ-አሜሪካኖች ፅኑዕ ወዳጅነት መሰረት እንደነበሩ ሁሉ አሁን የጠብ ሰበብ እየሆኑ ነዉ።

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያዉ ዘመነ ሥልጣናቸዉ ወቅት አዉሮጶችን መተቸት፣ መግፋት፣ማቃለል ሲጀምሩ የአዉሮጳ መሪዎች በተለይ ፀጥታን ለማስከበር ከአሜሪካ ጥገኝነት የሚላቀቁበትን ብልሐት እያነሱ ሲጥሉ ነበር።ባለፈዉ ሳምንት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ ለጉባኤተኞች በግልፅ ተናገሩት።

«አዉሮጳ የራስዋ የጋራ ጦር ኃይል እንደሚያስፈልጋት ብዙ መሪዎች ተናግረዋል።የአዉሮጳ ጦር ኃይል የሚመሠረትበት ጊዜ መምጣቱን ከልብ አምንበታለሁ።ይኽ ጦርነት በጥቂት መሪዎች ብቻ ሊወሰን አይችልም።በትራምፕና ፑቲን፣ በኔና በፑቲን፣ እዚሕ ሙኒክ ያሉት መሪዎች ከፑቲን ጋር ብቻ በመምከር ሊወሰን አይችልም።ሁላችንም አንድ ላይ ሆነን ግፊት ማድረግ አለብን።»

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዜሌንስኪና የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝደንት የመሯቸዉ የሁለቱ ሐገራት መልዕክተኞች JD ቫንሴ ከሙኒኩ ጉባኤ ጎን ለጎን ሲነጋገሩ የፓሪሱ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት።ምስል፦ TOBIAS SCHWARZ/AFP

በሙኒኩ ጉባኤ 60 ርዕሳነ ብሔራትና መራሕያነ መንግስታት፣ 150 ሚንስትሮች፣ ከ700 በላይ ዲፕሎማቶች፣ የጦር አዣዦች፣ዲፕሎማቶች፣ ተንታኞች፣ የመብት ተሟጋቾች  ተገኝተናዋል።ከጉባኤዉ በጎ ዉጤት ይልቅ የጎላዉ ግን ንትርኩ ነዉ።

የአዲስ አበባ ጉባኤተኞች ለአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት፣ የሙኒክ ጉባኤተኞች ደግሞ ለጉባኤዉ አስተናጋጅ ድርጅት ዋና ፀሐፊነት አዳዲስ ዲፕሎማቶችን  መምረጡ ግን ተሳክቶላቸዋል።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2005 ጀምሮ የጅቡቲ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ከ7 ዙር ድምፅ አሰጣጥ በኋላ፣ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነዋል።የቀድሞዉ የኖርዌ ጠቅላይ ሚንስትርና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ  ዋና ፀሐፊ፣ የቅርቡ የኖርዌ ገንዘብ ሚንስትር የንስ ሽቶትልበርግ የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ሊቀመንበር ሆነዋል።

የዓለም ሠላም፣ የፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ሥርዓት፣ ሒደትና እንዴትነት እንዳጠያየቀ ዓለም የጉባኤ ሳምንት አሰናብታ፣ የሌላ ጉባኤ ሳምንት ተቀብላለች።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW