ማሕደረ ዜና፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ምሥቅልቅል፣ የአሜሪካ ተቃራኒ አቋም
ሰኞ፣ ነሐሴ 20 2016ማሕሙድ አባስ እንደ መሪ ከመኖራቸዉ ይልቅ አለመኖራቸዉ ደምቋል።አል ሲሲ፣ ንጉስ አብደላሕ፣ አልጋወራሽ ቢን ሠልማን፣ ሌሎች የአረብ መሪዎችም የየሕዝባቸዉን ቁጣ በኃይልም፣ በይስሙላ ዲፕሎማሲም ለማዳፈን ይባትላሉ።ሐሰን ነስረላሕ ግን ይፎክራሉ።አያቶላሕ ዓሊ ኻሚኒ ይዝታሉ።ቤንያሚን ኔታንያሁ «ጠላት» የሚሉትን ጋዛ ዉስጥ ይጠለል፣ ደማስቆ ኤምባሲ ይሰብሰብ፣ ቤይሩት ይሸሸግ፣ ቴሕራን እንግዳ ማረፊያ ይተኛ ተራ በተራ ያስገድላሉ።ጆ ባይደን ዲፕሎማቶቻቸዉን በአዉሮፕላን፣ ጦር መሳሪያቸዉን በመርከብ ያዝመታሉ።ጋዛም የአሜሪካ ቦምብ-ሚሳዬል፣መድፍ-አዳፍኔ እየዘነበባት፣ ሞት እየተዘራ አስከሬን ይታጭድባታል።11ኛ ወር።የየሐገሩ ሕዝብ ጩኸት፣የዓለም ፍርድ ቤት ዉሳኔ፣ የዲፕሎማት-ፖለቲከኞች ምክር-ዝክር ሰሚ ጆሮ አላገኘም።መካከለኛዉ ምሥራቅ ደም እየጎረፈበት ደም የሚጠማዉ ምድር።የሰሞኑ እዉነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።
ሠላም አይፈለግ ይሆን?
የእስራኤል መሪዎች ጥቃት፣የኢራን መሪዎች፣ የፍልስጤም፣ የሊባኖስ፣ የየመን ደፈጣ ተዋጊዎች ፉከራ አላባራም።ጋዛ ትወድማለች። ፍልስጤሞች ያልቃሉ።በቅጡ መቀበሪያ፣ ሲቆስሉ ወይም ሲታመሙ መታከሚያ፤ ሲሸሹ መሰደጃ ሌላ ቀርቶ ሲራቡ የሚበሉት የላቸዉም።ኢጣሊያዊቷ እዉቅ ጋዜጠኛ ኦሪያና ፋላቺ በ1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) Intervista con la Storia (ታሪክን ቃለ መጠየቅ ማድረግ ማለት ያስኬዳል) ባሚል ርዕስ ባሳተመችዉ መፅሐፏ በቢሊዮን የሚቂቆጠረዉን የዓለምን ሕዝብ መኖር አለመኖር የሚወስኑት የአምስት ሐገራት አምስት መሪዎች ናቸዉ ዓይነት ብላ ነበር።
የያኔዎቹ የዋሽግተን፣ የሞስኮ፣የቤጂንግ፣ የለንደን ወይም የፓሪስ መሪዎች።ዛሬም ብዙ የተለየ አይደለም።ዓለም ብዙ ድርጅቶች፣ በርካታ ማሕበራት፣ የፍትሕ ተቋማት አሏት።ከ1948 ጀምሮ መካከለኛዉ ምሥራቅን ዉስጥ የሚደረገዉን መገዳደል፣ መበቃቀል፣መተላለቅ ለማስቆም ግን የሕዝብ የአደባባይ ሰልፍ፣የዓለም ድርጅት፣ ማሕበራት፣ የፍርድ ቤት ዉሳኔም አንዳቸዉም አልተከሩም።በተለይ ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ ብዙ ጊዜ እንደሚባለዉ እልቂት ፍጅቱን በሰላም ይሁን በማስፈራራት ማስቆም የሚችሉት የዋሽግተን መሪዎች ናቸዉ።ዋሽግተኖች ግን እንደ ገለልተኛ ሸማጋይ፣ እንደ እስራኤል ፅኑ ወዳጅ የእስራኤል አስታጣቂ ሆነዉ በተቃራኒ አቋማቸዉ መሐል ከመዋዠቅ ባለፍ እስካሁን ለሰላም የፈየዱት የለም።ከእንግዲሕስ?
ኢትዮጵያዊዉ የፖለቲካ ተንኝና ደራሲ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት የከእንግዲሑን የማዉቀዉ ፈጣሪ ብቻ ነዉ።
ሌለኛዉ ግንባር፣ የእስራኤልና ሒዝቦላሕ ዉጊያ
እስራኤል እንደሰነዘረችዉ በሚታመን ጥቃት የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቦላሕ ወታደራዊ አዛዥ ሞሕሲን ሰይድ ሞሕሲን ወይም ፉዓድ ሽኩር ቤይሩት፣ የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ ዑስማኢል ሐኒያ ቴሕራን ዉስጥ ከተገደሉ ካለፈዉ ወር ማብቂያ ወዲሕ ከቤይሩትና ቴሕራን የሚሰማዉ የብቀላ ዛቻና ፉከራ ብዙዎችን በጣም አስግቶ ነበር።
ሥጋቱ በተለይ ሊባኖስ ላይ አይሎ ምዕራባዉያን መንግስታት ዜጎቻቸዉን ከሊባኖስ እንዲወጡ ሲያዙ የቤይሩትን አዉሮፕላን ማረፊያዎች አጨናንቀዉት ነበር።ሥጋቱ ወትሮም የተገራገጨዉን የሊባኖስ ምጣኔ ሐብትን አሽመድምዶታል።የጀርመኑ የኮንራድ አደናወር መታሰቢያ ጥናት ተቋም የቤይሩት ቢሮ ተጠሪ ሚሻኤል ባወርም እንደ አብዛኛዉ ምዕራባዊ ዜጋ የቤይሩት ቢሯቸዉን ዘግተው ወደ አማን-ዮርዳኖስ ለመሰደድ ተገድደውል።ባወር እንደሚሉት የከፋ ይመጣል ከሚል ሥጋት ጭንቀት ሌላ የሰላም ተስፋ የለም።
«ግጭቱ ይበልጥ ይቀጣጠላል የሚለዉ ሥጋት ከፍተኛ ነዉ።የሐገሪቱ (የሊባኖስ) ሕዝብ በጣም ተጨንቋል።የሥጋቱን ንረት የሚያሳዩ ምልክቶችም ይታያሉ።አዉሮፕላኖች በረራ አቁመዋል።ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ወደ ቤይሩት የሚያደርጉትን ጉዞ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል።መንግስታት ዜጎቻቸዉ (ወደ ሊባኖስ) እንዳይጓዙ በየኤምባሲዎቻቸዉ በኩል የሚሰጡት ማስጠንቀቂያ እየተደጋገመ ነዉ።»
የተፈራዉ፣ የተፈራዉን ያክል አልሆነም እንጂ አልቀረም።ትናንት እስራኤል ሳይቀድሙ መቅደም ባለችዉ ጥቃት የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የሒዝቦላሕ ይዞታ ያለቻቸዉን አካባቢዎች በአብዛኛዉ በጦር ጄት ደብድባለች።የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀዉ ትናንት ጎሕ ሲቀድ ደቡባዊ ሊባኖስን የደበደቡት100 ተዋጊ ጄቶቹ የሒዝቡላሕን የሚሳዬልና የሰዉ አልባ አዉሮፕላን (የድሮን) ማወንጨፊዎችን፣ የጦር መሳሪያ ማከማቻና ምሽጎችን አዉድመዋል።የጦሩ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሐጋሪም ጦራቸዉ አብዛኛዉን የሒዝቡላሕን የጦር መሳሪዎች አዉድሟል ባይ ናቸዉ።
«ሒዝቡላሕን በቴክኖሎጂ ዉጤቶችና በአየር ኃይል አዉሮፕላኖች የአየር ቅኝት ለተከታታይ ሳምንታት ስንከታተለዉ ነበር።ሒዝቦላሕ ጥቃት ለማድረስ ማቀዱን ደርሰንበት፣ አብዛኛ (መሳሪያዎቹን) አዉድመናቸዋል።»
የእስራኤል ጦር ድል በዓለም መገናኛ ዘዴዎች ሲናኝ አብዛኛ አቅሙ «ተሰብሯል» የተባለዉ ሒዝቡላሕ ሰሜን እስራኤልን በሚሳዬልና ድሮን ይደበድብ ያዘ።የሒዝቡላሕ መሪዎች እንደሚሉት ቡድናቸዉ ከ350 በሚበልጡ ሚሳዬሎችና ድሮኖች እስራኤን ደብድቧል።የቡድኑ መሪ ሐሰን ነስረላሕ ትናንት ማምሻ እንዳሉት እስራኤል ባለፈዉ ወር ማብቂያ የገደለቻቸዉን የቡድኑን የጦር አዛዥ የሞሕሲን ሰይድ ሞሕሲንን ወይም ፉዓድ ሽኩሪን ደም ለመበቀል የከፈተዉ የመጀመሪያ ዙር ጥቃት አብቅቷል።ካስፈለገ ግን ይቀጥላል።
«በእኛ አስተያየት ዉጤቱ አይበቃም ብለን ካሰብን ሌላ ጊዜ ተጨማሪ ርምጃ የመዉሰድ መብታችን የተጠበቀ ነዉ።አሁን ግን ሕዝቡ ይረፍ፣ ወደየቤቱ መመለስ የሚፈልግ መመለሥ ይችላል።ሐገሪቱ አሁን መረጋጋት አለባት።ምክንያቱም መላ ሐገሪቱ ዉጥረት ላይ ናት።ስነልቡናዊዉ ጦርነትና ሐጂ ሞሕሴን ሰይድ ሞሕሴን ከተገደሉ ወዲሕ የሚነዛዉ አሉባልታም ዉጥረቱን አባብሶታል።»
የእስራኤል ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሐጋሪ እንዳሉት ጦራቸዉ በከፈተዉ ጥቃት «አሸባሪ» ያሏቸዉን 6 የሒዝቡላሕ ታጣቂዎች ገድሏል።ሒዝቡላሕ የከፈተዉ አፀፋ ጥቃት ግን በእስራኤል ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያደረሰዉ ጉዳት እንደሌለ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።ይሁንና ትናንት ቢያንስ አንድ የእስራኤል የባሕር ኃይል ወታደር መገደሉ ተዘግቧል።ሌላ ቆስሏል።
ፍሬ አልባዉ ድርድር፣ የአሜሪካኖች ተቃራኒ አቋም
እስራኤልና የሒዝቡላሕ ከ2006 ወዲሕ ከፍተኛ የተባለዉን ዉጊያ የገጠሙት የጋዛዉን እልቂት ለማስቆም «ተኩስ አቁም» የተባለዉ ድርድር ካይሮ ግብፅ ዉስጥ ሲደረግ ነዉ።በአሜሪካኖች ግፊትና ይሁንታ የሚደረገዉ ድርድር ልክ እንደ ጦርነቱ ሁሉ ለ11ኛ ወር ቀጥሏል።እስካሁን የተገኘ ዉጤት ግን ዜሮ ነዉ።የጋዛዉ እልቂት መቀጠሉ ከፍልስጤሞች ጎን የቆሙ በዩሱፍ ያሲን አገላለፅ የሐማስ «አጋዥ» የሚባሉ ኃይላትን ወደ ግጭቱ እየሳበ መገዳደል፣ ሥጋት፣ ዉጥረቱን እያናረዉ መቀጠሉ አይቀርም።
«በእስራኤልና ሐማስ መካከል በአሜሪካ ሸምጋይነት፣ በአረቦች ተባባሪነት ይደረጋል የተባለዉ ተኩስ አቁምና የታጋቾች መፈታት ይሆናል፣ ይሆናል እየተባለ እንደገና እየራቀ፣ እንደገና እየተፋለሰ የመጣበት ሂደት ነዉ የምናየዉ።አጋዦቹ ይሕንን (ግጭቱ) ዉስጥ ከገቡ በኋላ ድሮ ከነበረዉ ይበልጥ እየተዘጋጁበት፣ ይበልጥ ደግሞ በጥንቃቄ የሚሔዱበት---»
የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንደሚሉት እስራኤል ባለፈዉ መስከረም 26 ሐማስ ያደረሰባትን ጥቃት ለመበቀል ጋዛ ላይ በከፈተችዉ ጥቃት ከ40 ሺሕ በላይ ሕዝብ ፈጅታለች።ከ80 ሺሕ በላይ ሕዝብ ቆስሏል።አብዛኞቹ ሟች ቁስለኞች ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋዉያን ናቸዉ።
እስራኤል ዩናይትድ ስቴቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ፣ ባለፈዉ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤልን ወርሮ 1200 ያክል የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎችን መግደሉን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።ሐማስ ካገታቸዉ መካከል 105ቱ ሰዎች እስካሁን አልተለቀቁም።
የእስራኤል መሪዎች ያኔ እንዳሉት ጦራቸዉ የሐማስን ጥቃት ለመበቀል ጋዛ ላይ የከፈዉ መጠነ ሰፊ ዘመቻ አላማ ሐማስን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት፣ ታጋቾቹን ማስለቀቅ ነበር።እስካሁን ብዙ የሐማስ መሪና ተዋጊዎች መገደላቸዉን የእስራኤል ባለሥልጣናት አስታዉቀዋል።ቡድኑ ግን አልጠፋም።
በሰላማዊ ድርድር ከተለቀቁት ዉጪ በኃይል የተለቀቀ ታጋችም የለም።አንዴ ዶሐ፣ ሌላ ጊዜ ካይሮ ይደረጋል የሚባለዉ ድርድር፣ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት አረቀቁት የተባለዉ የድርድር ዕቅድ ወይም የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ያስገኘዉ ሰላም የለም።አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ለግጭት-እልቂቱ ሰላማዊ መፍትሔ ማጣት አንዱና ምናልባት ዋናዉ እንቅፋት የአሜሪካ እንቆቅልሽ አቋም ነዉ።
«አሜሪካኖች ባንድ በኩል የእስራኤል ደሕንነት አስጠባቂዎች ነን ባዮች ናቸዉ።ጠላቶችዋ እንዳያሸንፏት ወይም ገፍተዉ እንዳያጠቋት ሞግዚትነን ማለታቸዉ ነዉ ይኸን ሁሉ እንቆቅልሽ የምናየዉ።አንዳድ ፕሬዝደንቶች መጀመሪያ ሲመረጡ በእስራኤል ላይ ትንሽ ግፊት ያደርጋሉ፣ ነገር ግን በአረቦቹ ቸልተኝነት ወይም በፍልስጤሞች መዳከም----ያነዉ እንግዲሕ ዉኃ ቅዳ ዉሐ መልስ የሚሆነዉ።»
አቅመ ቢሱ የሩቁ ዓለም አስከሬን እንደቆጠረ፣የእናቶች ሰቆቃ፣ የሕፃናት ዋይታ፣ የአዛዉንቶችን ሲቃ እንደታዘበ ሌላ ቀን ይጠብቃል።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ