1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ማሕደረ ዜና፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ እልቂትና የአሜሪካኖች ተቃራኒ መርሕ

ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2017

ዘንድሮም «ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም እንዳለዉ» የዚያ ምድር ጠቢብ ጉልበተኞች ገድለዉ፣ ወይ አስገድለዉ ይፉክሩበታል።ያዉ ሌላ ገዳይ እስኪተካ።ከጦረኞቹ የመጨረሻዉ ሟች ያሕያ ሲንዋር ናቸዉ።ባለፈዉ ሳምንት ከዋሽግተን፣በርሊንና ሌሎች አካባቢዎች እንደሰማነዉ እስራኤል የሐመሱን መሪ መገደሏ ሰላም በማያዉቀዉ ምድር ሠላም ለማዉረድ ጠቃሚ ነዉ

ጋዛ ዉስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ መጠለያ ጣቢያዎች፣ መኖሪያ አካባቢዎችና ትምሕርት ቤቶች ወድመዋል
የእስራኤል ጦር ባለፈዉ ሳምንት ካወደማቸዉ የጋዛ የሥደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች አንዱ።ዴር አል ባላሕምስል Omar Ashtawy/APA Images/Zumapress/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ እልቂትና የአሜሪካኖች ተቃራኒ መርሕ

This browser does not support the audio element.

ጋዛ ከሰዎች መኖሪያነት ወደ አስከሬን ማምረቻነት ተለዉጣለች።የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ከተማ፣ ቀበሌ፣ የተፈናቃይ መንደሮች የሰዎች መገደያ፣መታሠሪያ፣መሠቃያ ማዕከላት ሆነዋል።ሊባኖስ አስከሬን፣ ቁስለኛ፣ ተፈናቃይ ትቆጥራለች።ሰሜን እስራኤል በሮኬት፣ሚሳዬል፣ ድሮን ወዠቦ ትሸማቀቃለች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣የአዉሮጳ ሕብረትና ሌሎችም ዛሬም እንዳምናዉ ተኩስ ይቁም ይላሉ።ዩናይትድ ስቴትስ ጦር መሳሪዎችዋን በመርከብ፣ ዲፕሎማቶችዋን በአዉሮፕላን ወደ እስራኤልን ትልካለች።ኢራንና የእስራኤል ለቀጥታ ዉጊያ ይዛዛታሉ።መካከለኛዉ ምሥራቅ።የጦርነት ትርምስ ምድር።

«ልዩ ቀን»-1948 ሐይፋ

ሰኔ 1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሐይፋ ወደብ ላይ ለዘመናት  የተዉለበለበዉ የብሪታንያ ባንዲራ ወረደ።የብሪታንያ የበላይ ጠባቂነት አገዛዝም አበቃ።

በፍልስጤም የብሪታንያ የመጨረሻዉ ኮሚሽነር (አገረ ገዢ) ጄኔራል ሠር አለን ጎርደን ካኒንገሐም ባንዲራዉን ሲያወርዱ «የ31 ዓመት ዉጊያ፣ መስዋዕትነት፣ሙግትና ዉዝግብ---ለዚሁ ነበር?» ዓይነት አሉ-አሉ የፃፉ።

በብሪታንያ ባንዲራ ምትክ የአዲሲቱን ሐገር ባንዲራ የሰቀሉት የመጀመሪያዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ቤን ጎርዮን ግን «በእስራኤል ሐገረ-መንግሥት ታሪክ ከሚዘከሩ ታላላቅ ዕለታት አንዱ» አሉት።ያ ምድር የአገዛዝ ጀንበሩ የጠለቀችበትን ሽሮ አዲስ ሾመ።

ከክርስቶስ ልደት 1900 ዓመታት በፊት ከሜሶፖታሚያ ወይም ከሌቬት የፈለሰዉ ጥንታዊ የሒብሩ ነገድ ከሰፈረበት ጊዜ ጀምሮ የሚደረገዉ ዉጊያ፣ መገዳደልም ቀጠለ።

የሰላም በጎነት፣ የዉጊያ-መገዳደል ተቃርኖ ምድር

 

እንደ ሙሴ ሁሉ ፈርዓኖች፣ከዳዊት ዝማሬ-ከሰለሞን ጥበብ እኩል ተዋጊዎች፣ ከክርስቶስ ስብከት፣ ፀሎት-ምሕላ እኩል የመስቀል ጦረኞች፣ ከመሐመድ ስግደት-ሩሕሩሕነት ባልተናነሰ ገዳዮች ተፈራርቀዉበታል።

ጁዳይዝም፣ክርስትና እስልምና ለሰዉ ልጅ በጎ የማድረግን አስፈላጊነት እንደተሰበኩበት ሁሉ ዳዊት፣ ፈርኦን፣ ሴንክራይብ፣ ናቡከደናፀር፣ፔቶሎሚ፣ ሔሮድ፣ ጎድፍሬይ፣ ሳላሒዲን ሌሎችም ገድለዉ፣አስገብረዉ፣ ገዝተዉ፣ ለሌላ ተረኛ ገብረዉ፣ተሰናብተዉበታል።መካከለኛዉ ምሥራቅ።

የቤተሰባቸዉ አባል፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ የታገቱባቸዉ እስራኤላዉያን ታጋቾቹ እንዲለቀቁ በየሳምንቱ የሚያደርጉት የአደባባይ ሰልፍ እንደቀጠለ ነዉምስል Violeta Santos Moura/REUTERS

«ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም»

ዘንድሮም «ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም እንዳለዉ» የዚያ ምድር ጠቢብ ጉልበተኞች ገድለዉ፣ ወይ አስገድለዉ ይፉክሩበታል።ያዉ ሌላ ገዳይ እስኪተካ።ከጦረኞቹ የመጨረሻዉ ሟች ያሕያ ሲንዋር ናቸዉ።ባለፈዉ ሳምንት ከዋሽግተን፣በርሊንና ሌሎች አካባቢዎች እንደሰማነዉ እስራኤል የሐመሱን  መሪ መገደሏ ሰላም በማያዉቀዉ ምድር ሠላም ለማዉረድ ጠቃሚ ነዉ።ቀዳሚዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን።

«የሐማስ መሪ መሞት የፍትሕ መስፈንን ያሳያል።የእሱ እጅ የአሜሪካኖችና የእስራኤሎች፣ የፍልስጤሞችና የጀርመኖች የሌሎች የብዙዎች ደም አለባቸዉ።ይሕንን ዕድል ለሰላም፣ሐማስ ለማይኖርባት ጋዛ የተሻለ መፃኤ ዕድል ለማስፈን እንድነጠቀምበት ለእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ነግሬያቸዋለሁ።የኢራንንም ጉዳይ ለመነጋገር ተስፋ አደርጋለሁ።»

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ ባሸባሪነት የሚወነጅሉት ሐማስ የተመሠረተዉ በ1987 ማብቂ ነዉ።ሰዉ ታሪክን መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቤን ጎሪዮን «ታላቅ ና ታሪካዊ» እስካሉት ዕለት ድረስ ያ ምድር ሠላም አያዉቅም።ከታሪካዊዉ ዕለት ሐማስ እስከተመሠረበት ጊዜ ድረስ ብቻ አረቦች፣እስራኤሎች፣ፈረንሳዮች፣ ብሪታንያዎች፣አሜሪካኖች፣ ፋርሶች ተዋግተዉበታል።

እስራኤል ከ1972 ጀምሮ ከቤይሩት-እስከ ፓሪስ፣ ከለንደን እስከ ቱኒስ፣ ከአቴንስ እስከ ዱባይ እስከ ደማስቆ የተሰደዱ፣ እዚያዉ ፍልስጤም ዉስጥ የተሸሸጉ፣ በዊልቸር የሚጓዙ በሽተኞችን ሳይቀር በርካታ የፍልስጤም ቡድናት መሪዎችን ገድላለች።ሺዎችን አስራለች።ከሲንዋር በፊት አምና ዘንድሮ ብቻ ዑስማኢል ሐንያሕንና ሐሰን ነስረላሕን ጨምሮ 16 የሐማስና የሒዝቡላሕ መሪዎችን ገድላለች።

ባይደን ያሉት ሰላም ግን እስከ ሲንዋር መገደል ድረስ አንዳልንበረ ሁሉ ከሲንዋር መገደል በኋላም እስካሁን የለም።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ጆሴፍ ቦርየል ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ደግሞ እስራኤል ታጋቾች አልተለቀቁም።ከሞት የተረፈዉ የጋዛ ሕዝብ ግን በረሐብ ጭምር እየተቀጣ ነዉ።

«ይሁንና ታጋቾቹ እስካሁን አልተለቀቁም።ወደ ጋዛ የሚገባዉ የሰብአዊ ርዳታ በሚገቡ ካሚዮኖች ቁጥር ሲለካ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲሕ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነዉ።ሥለዚሕ ረሐብ እንደ ጦር መሳሪያ እያገለገለ ነዉ።400 ሺሕ ህዝብ ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን እንዲሔድ ታዝዟል።እነዚሕ ሰዎች ተዳክመዋል።እንደገና መጓዝ አይችሉም።»

የልዕለ ኃያሊቱ ሐገር መሪ ጆ ባይደን ዛሬ ዉሎ ማዳሩን ለማያዉቀዉ ለጋዛ ሕዝብ የወደፊቱ ኑሮዉ እንድስተካከል የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትርን በጎ ፍቃድ ይጠይቃሉ።ዕዉቁ አሜሪካዊ የምጣኔ ሐብት አዋቂ ጄፍሬይ ሳክስ በቅርቡ እንዳሉት የአሜሪካ የፖለቲካ ሥርዓት ክሕደት፣ ጭካኔ፣በኃይል የማንበርከክን ሥልት የወረሰዉ ከብሪታያ ኢምፓየር ነዉ።

የእስራኤል ጦር ባለፈዉ ሳምንት የገደላቸዉ የሐማስ መሪ ያሕያሕ ሲንዋር።ሲንዋር ከዚሕ ቀደም በነብሰ ገዳይነት ተወንጅለዉ እስራኤል ዉስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ታስረዉ ነበርምስል Ashraf Amra/ZUMA/picture alliance´

በ1948 የእስከያኔዉን ፍልስጤም ለተጨማሪ ትርምስ አጋልጣ የወጣችዉ ብሪታንያ ለዘመናት እንደኖረችበት ሁሉ ዛሬም ከዋሽግተን-ቴልአቪቭ መሪዎች ጎን ቆማ እልቂት ፍጅቱን ታጋግማለች።የብሪታንያ ገዢዎች ፍልስጤም ጥለዉ ከወጡበት ጀምሮ እስከ 1967 ድረስ ጋዛን የተቆጣጠረችዉ የግብፅ መሪዎች ደግሞ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሳራሕ ዋይትሰን እንዳሉት ከዚያች መከረኛ ግዛት ዉድመት፣ ከሕዝቧ እልቂት፣ ስቃይ ሰቆቃ የሚያገኙትን ትርፍ ያሰላሉ።

«ፕሬዝደት ሲሲ፣ እስራኤል ጋዛና ሊባኖስ ዉስጥ በከፈተችዉ ጦርነት የተፈጠረዉን ቀዉስ ለራሳቸዉ ጥቅም አዉለዉታል።ግጭቱን ለማቃለል እራሳቸዉን በጣም ተፈላጊ አደራዳሪ በማድረግ፣ በእዉነቱ እዚያዉ ግብፅ ዉስጥ ያለዉን አሰቃቂ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በጣም ሥር የሰደደዉን የመንግስት ሙስናን ለመደበቅ እየተጠቀሙበት ነዉ።»

ጋዛ እስከ ቤይሩት

ሐማስ አምና መስከረም ደቡባዊ እስራኤልን ወርሮ ከ1ሺሕ 1 መቶ በላይ የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎችን  ገድሏል።በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች አግቷል።ከታጋቾቹ የተወሰኑት በድርድር ሲለቀቁ 100 ያክሉ ዛሬም እንደታገቱ ነዉ።

የእስራኤል መሪዎች አምና እንደ ፎከሩት ታጋቾችን እስካሁን አላስቀቁም።ሐማስንም ብዙ መሪዎቹን ይግደሉ እንጂ ሙሉ በሙሉ አላጠፉትም።ጋዛ ግን በርግጥ ወድማለች።42 ሺሕ ነዋሪዎችዋ አልቀዋል።ወደ መቶ ሺሕ የሚጠጉ ቆስለዋል። አብዛኞቹ ሟች-ቁስለኞች፣ወትሮም በድሕነት ይማቅቁ የነበሩ ሴቶች፣ አዛዉንቶች ወይም ክፉ-ደጉን የማያዉቁ ሕፃናት ናቸዉ።

መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ከአምና መስከረም ወዲሕ የእስራኤል ጦርና ሠፋሪዎች ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ላይ በከፈቱት ጥቃት ከ770 በላይ ፍልስጤማዉያን ተገድለዋል።ከ11 ሺሕ በላይ ታሥረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ጋዛ ዉስጥ 220 ሠራተኞቹ ተገድለዋል።ዓለም አቀፉ ድርጅት ከተመሠረተ ከ1945 ወዲሕ በርካታ ሰራተኞቹ ሲገደሉ የጋዛዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።እዚያዉ ጋዛ ዉስጥ ከ170 በላይ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ዘዴ ሠራተኞች ተገድለዋል።

የእስራኤል መሪዎች የጋዛዉ እልቂት፣ ጥፋትና ዉድመት በቀጠለበት ባለፈዉ መስከረም  ሊባኖስ ያዘመቱት ጦራቸዉ ከባርጃ እስከ ቤይሩት የሚገኙ ከተማ፣ መንደር፣ መንገድ ድልድዮችን እያወደመ ነዉ።የሊባኖስ የጤና ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ የእስራኤል ጦር በከፈተዉ ጥቃት ከ2100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በፍልስጤሞች ላይ የሚፈፀመዉ ግድያ፣ እመቃና እንግልት እንዲቆም ብራስልስ ቤልጂግ ዉስጥ ሰሞኑን ከተደረጉ የአደባባይ ሰልፎች በከፊልምስል Nicolas Maeterlinck/dpa/picture alliance

የጋላንት ማረጋገጪና ሒዝቡላሕ

የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት በቅርቡ ለእስራኤል የሰሜን ግንባር ጦር አዛዦች እንደነገሩት ጦራቸዉ ሒዝቡላሕን አሽመድምዶታል።

«ሒዝቡላሕ ተሽመድምዷል።የተሰበረ ድርጅት ነዉ።ጠቃሚ የዕዝና የቁጥጥር አቅም ሳይኖረዉ ጭንቅላቱን ብቅ ለማድረግ አይሞክርም፣ በሁሉም ደረጃ ያሉ መሪዎቹን አጥቷል።በፖለቲካዉ፣ በጦሩ፣ በዉሳኔ ሰጪ አካላቱ የነበሩትን አጥቷል።ይሕን እድል መጠቀም አለብን።ግባችን የሰሜን (እስራኤል) ነዋሪዎችን በሰላም ወደየቤታቸዉ መመለስ ነዉ።»

የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር መልዕክት  አስገምግሞ ሳያበቃ ሐይፋ፣ ቴል አቪቭና ሌሎች የሰሜንና የማዕከላዊ እስራኤል ከተሞች በሒዝቡላሕ ሚሳዬልና ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ይደበደቡ ያዙ።በጋላንት ቃል «የተሽመደመደዉ» ሒዝቡላሕ ባለፈዉ ቅዳሜ  የሰደደዉ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ደግሞ ሴሳሪያ ከሚገኘዉን ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መኖሪያ ቤት አጠገብ የሚገኝ ሕንፃን መትቷል።

 

ጀሩሳሌም ፖስት የተባለዉ ጋዜጣ እንደዘገበዉ የእስራኤል መሪዎች ባንድ ጊዜ ጋዛ፣ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻና ሊባኖስ ላይ በከፈቱት ወታደራዊ ዘመቻ ወደ ሰባት መቶ የሚጠጉ የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።ለጦርነቱ ከ67 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተከስክሷል።

የአሜሪካ የርዳታና የዲፕሎማሲ ተቃርኒ አቋም

እርግጥ ነዉ እስራኤል ገንዘብ ብትፈልግ የአሜሪካ ካዝና፣ ጦር መሳሪያ ብትሻ የአሜሪካ መጋዘን ለእስራኤል ክፍት ነዉ።የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ፕሬዝደንት ባይደን አስተዳደር አምና ከመስከረም እስከ ነሐሴ ድረስ ብቻ 50 ሺሕ ቶን የሚመዝኑ የተለያዩ ቦምቦች፣ ሚሳዬሎች፣የአየር መቃወሚያዎችና ጥይቶች ለእስራኤል አስታጥቋል።ከ12 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ረድቷል።

ባለፈዉ ሳምንት ደግሞ  ዩናይትድ ስቴትስ THAAD በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉን ልዩ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ለእስራኤል አስታጥቃለች።መሳሪያዉን የሚዘዉሩ ከ90 የሚበልጡ የአሜሪካ ወታደሮችም ይዘምታሉ።የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ዴቪድ ሜንሰር ባለፈዉ ሰኞ እንዳሉት ግን የአሜሪካ ጦር መሳሪያ እንጂ ወታደር እስራኤል እንዲሰፍር መንግስታቸዉ አልጠየቀም።

«የአሜሪካ ወታደሮች እስራኤል መሬት ላይ  እንዲሰፍሩ እስራኤል ጨርሶ ጠይቃ አታዉቅም።እነዚሕ የአሜሪካ ወታደሮች የ-THAAD-ን የመከላከያ ሚሳዬል የሚተኩሱ ናቸዉ።መሳሪያዉ ኢራን እኛን ለመምታት የምታስፈራራበትን በየትኛዉም አቅጣጫ የሚወነጨፉ ሚሳዬሎችን ከየትኛዉም ርቀት ሰማይ ላይ የሚቀልብ ነዉ።»

ግዙፉ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል አንዱ ባትሪ 1 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል።ለመተኮስ 100 ያክል ወታደር ያስፈልገዋል።ኢራንና በኢራን የሚደገፉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ የተለያዩ ቡድናት  የአሜሪካ ወታደሮች እስራኤል ከሠፈሩ በሌሎች የአካባቢዉ ሐገራት የሰፈረዉን የአሜሪካ ጦርንም ጭምር እንደሚያጠቁ በተደጋጋሚ እየፎከሩ ነዉ።የሰማቸዉ እንጂ የፈራቸዉ የለም።

ከዚሕ ቀደም ባንድ ዓመት ዉስጥ 10 ጊዜ ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ የተጓዙን የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በዚህ ሳምንትም አካባቢዉን ይጎበኛሉምስል GPO/Anadolu/picture alliance

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጦር መሳሪያዉን  በመርከብ ወደ እስራኤል በላኩ በሳምንቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን በአዉሮፕላን በዚሕ ሳምንት ለመላክ አቅዷል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲሕ አካባቢዉን ሲጎበኙ ያሁኑ 11ኛቸዉ ነዉ።የጉዟቸዉ ዓላማ በሙሉ ሰላም ለማስፈን እንደሆነ በየጊዜዉ አስታዉቀዋል።

ከተፋላሚ ኃይላት አንዱን እያስታጠቁ ሌላዉን እየቀጡ «እሸመግላለሁ» አይነት ዲፕሎማሲን ዓለም ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ በግዱ እየለመደዉ ነዉ።መገዳደል፣ ደካማን የማስገበር እልሕንም ከቅኝ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ በግልፅ እንደለመደዉ ቀጥሎበታል።በቅርብ ዘመን የሠላም ዉል በመፈረማቸዉ ሳዳት፟ ካይሮ፣ ራቢን ቴልላአቪቭ አደባባይ በየወገኖቻቸዉ የተገደሉበት መካከለኛዉ ምሥራቅም ዘላቂ ሠላም መስፈኑ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW